አዲስ አበባ፡- ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የሦስትዮሽ ውይይት እያካሄዱ ነው። በውይይቱ የሦስቱ ሀገራት የውሃ ሚኒስትሮች በተገኙበት ሲሆን ትኩረቱም በግድቡ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅ ዙሪያ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ የአባይ ውሃ ለኢትዮጵያ ድህነትን ማጥፊያ እና የህልውና ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል ሲል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘግቧል፡፡
ውይይቱም በሰከነና በመግባባት መንፈስ በማካሄድ መቋጨት እንደሚገባ ዶክተር ስለሺ ጠቅሰው፥ ኢትዮጵያ አሁንም የግብፅንም ሆነ የሱዳንን ህዝብ የመጉዳት ፍላጎት እንደሌላት አስረድተዋል።
ሀገሪቱ በፈረንጆቹ 2015 የተፈረመውን የመርህ ስምምነት አክብራ እየተንቀሳቀሰች መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፥ የግድቡን ግንባታ የተመለከቱ ከ150 በላይ ሰነዶችን ለግብፅ እና ሱዳን መስጠቷ ግልፅነቷን ያሳየ መሆኑንም አንስተዋል።
ይህም እስካሁን ለተካሄዱ ድርድሮች በር መክፈቱን አንስተው፥ በድርድሩ ከዚህ ቀደም የተደረጉ የውሃ ክፍፍል ስምምነቶች ዋጋ የላቸውም ብለዋል። በድርድሩ ለቴክኒካዊ ጉዳዮች ቴክኒካዊ መፍትሄ ለመስጠት ጥረቱ መቀጠሉንም አብራርተዋል።
የግብፁ የውሃ እና መስኖ ሚኒስትር ዶክተር ሙሃመድ አብዱል አቲ በበኩላቸው፥ ባለፉት ሦስት ድርድሮች በተለያዩ ጉዳዮች መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። በግድቡ ውሃ መያዣ ጊዜ እና በድርቅ መከላከያ መንገዶች ዙሪያ ተስማምተናል ያሉት ሚኒስትሩ፥ ስምምነት ያልተደረሰባቸውን ጉዳዮች ዛሬ እና ነገ እንፈታቸዋለን ብዬ አምናለሁም ብለዋል በንግግራቸው።
የሱዳን የውሃ ሚኒስትር ፕሮፌሰር ያሲር ሙሃመድ አባስም እስካሁን በገነባነው ላይ ተመስርተን ስምምነት ላይ እንደርሳለን የሚል እምነት አለኝ ብለዋል። በህዳሴው ግድብ ዙሪያ እየተካሄደ ያለው ድርድር እስከ ፈረንጆቹ ጥር 15 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። ትናንት የተጀመረው ይህ ስብሰባ የዓለም ባንክ እና የአሜሪካ መንግሥት ተወካዮች በታዛቢነት የተገኙ ሲሆን ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012