አዲስ አበባ፡- ሁለተኛው ሀገር አቀፍ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ኤግዚቢሺንና ባዛር በአማራ ክልል ባህርዳር ከተማ ከጥር 2 እስከ 4 በባህርዳር ከተማ እንደሚከበር የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ካባ ኡርጌሳ እንደገለጹት ‹‹የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ለሀገራዊ ብልጽግና›› በሚል መልዕክት የሚከበረው ይህ ኤግዚቢሺንና ባዛር ከሁሉም ክልሎች በሞዴልነት የተመረጡ የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ አንቀሳቃሾች ፣ባለሀብቶች፣ የልማት ደጋፊዎችና በየደረጃው ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ይከበራል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ ተገምግመው ውጤታማ የሆኑ 85 የገጠር ኢንተርፕራይዞች ሁሉንም ክልሎች በመወከል እንደሚቀርቡና ምርቶቻቸውንና አገልግሎታቸውን ለተጠቃሚዎች የሚያስተዋውቁበት መድረክ አንደሚሆን የገለፁት ዶክተር ካባ ኢንተርፕራይዞቹ በምርት ጥራት፣በስብጥር፣በቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በመሳሰሉት መመዘኛዎች የተመረጡ ናቸው ብለዋል።ኤግዚቢሽንና ባዛሩ የገጠር ሥራ እድል ፈጠራን የሚያበረታታና አዋጭነትን ለማጎልበት የሚረዳ አመልክተዋል።
የመርሐ ግብሩ ዋና ዓላማ የገጠር ሥራ ዕድል አንቀሳቀሾች ምርታቸውንና አገልግሎታቸውን ለተጠቃሚዎች በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ፣ የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉና አቅማቸውን እንዲያሳድጉ ማስቻል እንደሆነም ገልጸዋል።የገጠር ኢንተርፕራይዞች ምርቶችና አገልግሎቶች በጥራትና በስብጥር የደረሱበትን ደረጃ ለህብረተሰቡ ማሳየትና ዘርፉን ማነቃቃት ለቀጣይ ሥራ አጋዥ እንደሆነም ዶክተር ካባ ተናግረዋል።
መድረኩ የገጠርና የከተማ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቀሾችን በማቀራረብ ተመጋጋቢነት ባላቸው የስራ ዘርፎች ትስስራቸውን አጠናክረው ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡ ይረዳል ተብሏል።ብቁና ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዝ አንቀሳቃሾች ጤናማ የውድድር ስሜት እንዲፈጠርባቸው ያደርጋል።
የገበያ ፍላጎትና አቅርቦትን አመጣጥኖ ለማቅረብም ይረዳል ብለዋል።አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና ስራዎች ቀርበው እንዲታዩ በማድረግም ፈጠራንና የፈጠራ ባለሙያዎችን ዕውቅና ለመስጠትና ለማበረታታት ይጠቅማል።ነባርና የአዳዲስ ኢንተርፕራይዞች ከሚከተሏቸው የአሰራር መንገዶች አንጻር ልምዳቸውን በመቀመር እይታቸውን እንዲያሰፉ ይረዳቸዋል።
የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ በውስን ገንዘብ ውጤታማ የሆኑ አንቀሳቃሾች አንደሚገኙበትና ምርታቸውን ወደ ውጭ ለመላክ የሚያስችል መሻሻል የታየባቸው እንዳሉም ዶክተር ካባ ገልጸዋል።ከውጭ ሀገር የሚመጡ ምርቶችንም ተክተው የሚያመርቱ መኖራቸው መድረኩ ዘርፉን ለማበረታታት አቅም እንደሚሆን ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።
የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ የበርካታ ዜጎችን የሥራ ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አቅም እንዳለው የተናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው መንግሥት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት በመጠቀም ወጣቱ ከምንጊዜውም በላይ እራሱን ለሥራ ማዘጋጀት እንዲገባው አሳስበዋል።
ዘንድሮ በባህር ዳር ከተማ የሚደረገው የገጠር ሥራ ዕድል ፈጠራ ኢግዚቢሽንና ባዛር ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን አምና በኦሮሚያ ክልል አዳማ ከተማ በርካታ ልምዶች የተገኙበት መርሐ ግብር ተካሄዶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012
ኢያሱ መሰለ