አዲስ አበባ:- የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ለጨርቃጨርቅ ኢንዱስትሪው ትኩረት የሰጠ ቢሆንም የጥሬ ዕቃ፣ የውጭ ምንዛሪ፣ የመሰረተ ልማት አቅርቦት፣ ኮትሮባንድና ሌሎች ማነቆዎች ዘርፉን እየፈተኑት መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና አልባሳት አምራቾች ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ዋና ፀሐፊ አቶ አጋዚ ገብረየሱስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው ከግብርና በተለይም ከጥጥ ምርት አቅርቦት ጋር የተያያዘ በመሆኑ የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ትኩረት ከሰጣቸው ግብዓቶች መካከል ይጠቀሳል። 80 በመቶ የጥሬ ዕቃ ግብአት ከውጭ መግባቱ፣ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት ዕጥረት፣ እያደገ ከመጣው ኢንዱስትሪ ጋር የሚጣጣም የዳበረ የሥራ ባህልና የሰለጠነ የሰው ኃይል አለመኖር፣ የኮትሮባንድ የገበያ ድርሻ 53 በመቶ መድረስ ዘርፉን ፈትኖታል ብለዋል።
ምርት ወደ ውጭ ለሚልኩ ከቀረጥ ነፃ ማበረታቻ መኖሩን የጠቆሙት አቶ አጋዚ በወጭ ንግዱ ላይ ያሉት ደግሞ አብዛኞቹ አቅም ያላቸው የውጭ ኩባንያዎች ናቸው። በተመሳሳይ በሀገር ውስጥ ገበያ ተለማምደው በውጭ ንግድ ላይ ለመሰማራት ጥረት ለሚያደርጉ ሀገር በቀል አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች አቅም መፍጠሪያ ማበረታቻ መኖር እንዳለበት አመልክተዋል።
ኢንዱስትሪው በፖሊሲ ያለው ድጋፍ፣ ለዜጎች ሰፊ የሥራ ዕድል መፍጠሩ፣ የዓለም ገበያውም በማደግ ላይ ወዳሉ ሀገሮች ፊቱን ማዞሩ የዘርፉ እድሎች መሆናቸውን የጠቆሙት አቶ አጋዚ እነዚህን ዕድሎች ለመጠቀም የበለጠ መደገፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ዘርፉ የሥራ ዕድል በመፍጠርና የውጭ ምንዛሪን በማስገኘት ሚናው የሚናቅ ባይሆንም በሚፈለገው ልክ በኢኮኖሚው ላይ አስተዋፅኦ እንዲኖረው በውጭና በገቢ መካከል ያለውን የንግድ ጉድለት ማጥበብ እና ሌሎችንም ክፍተቶች መቅረፍ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ማህበሩ በሚፈጠሩ መድረኮችና በተለያዩ አጋጣሚዎች ክፍተቶቹን በማሳየት ዘርፉ ለስኬት እንዲበቃ ጥረት እያደረገ መሆኑን በመጠቆም፣ የሚነሱት ችግሮች ተመሳሳይና ቶሎ መፍትሄ ያለማግኘታቸው ጉዳይ ግን እንደሚያሳስበው ገልጸዋል።
ማህበሩ እስከዛሬ በአባልነት ያልያዛቸውን በተለይም ቁጥራቸው አንድ መቶ የሚደርሱ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችንና ሌሎችንም አባል ለማድረግ የስትራቴጂ ጥናት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት አቶ አጋዚ በአሁኑ ወቅት 87 አምራች ኢንዱስትሪዎችን አባላት አሉት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 30/2012
ለምለም መንግሥቱ