“ውህደቱን በተመለከተ ክስ የሚያቀርቡ ሰዎች ከሃዲዎች ናቸው”
-አቶ አወሉ አብዲ የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና አለማቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ
ብልፅግና ፓርቲ በውህደቱ ውስጥ የያዘው አሃዳዊነትን በመሆኑ ህወሃት እንዳልተቀበለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ገለፁ። እንደዚህ ያለ ክስ የሚያቀርቡት ክህደት የፈፀሙ ሰዎች መሆናቸውን የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ ገልፀዋል።
አቶ አስመላሽ ከዘመን መጽሄት ጋር ባደረጉት ቆይታ እደገለፁት በውሕደቱ የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ወደ አንድ ወጥ ፓርቲ ቢመጡና ቢዋሃዱ የሚል ሀሳብ ከ7ኛው ጉባዔ ጀምሮ የተነሳ ቢሆንም የተሳሳተ አካሄድም ነበረው።
ህወሓት ውሕደት አያስፈልግም፤የሚለው ስለተጠየፈው አይደለም የሚሉት አቶ አስመላሽ አንድ ወጥ ፓርቲ እንሁን ሲባል፤ ወደዚያ የሚያመጣ ጥናት ተጠንቶና አንድ ወጥ የሆነ ፓርቲ እንድንመሠርት ያደረገ ተግባራዊ ሁኔታ ተቀይሯል ወይስ አለ? ይሄ ነባራዊ እና ፖለቲካዊ ሁኔታ ተቀይሮ እንደሆነ የምናራምደው የጋራ ዓላማ፣ ርዕዮት እና ሕገ ደንብ ምን ይሆናል? በሚሉ ጉዳዮች ተስማምተን ግልጽ በሆነ ዴሞክራሲያዊ መንገድ ሕጉን ተከትለን ልናደርገው እንችላለን በሚል ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ ደግሞ በ2010 ዓመተ ምህረት ታህሣሥም መጋቢትም ጭምር ባደረግነው ኮንፈረንስ የህወሓት አቋም ነው የሚሉት አቶ አስመላሽ እኛ ያልተቀበልነው በውሕደቱ በውስጥ ያለው አመለካከት አሃዳዊነትን የያዘ ስለሆነ ነው ብለዋል።
የብልፅግና ፓርቲ የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ አወሉ አብዲ በበኩላቸው ውህደት የፈፀመው ራሱ ኢህአዴግ ነው። ውህደቱን የፈፀሙት ፕሮግራሙን እና ዓላማውን በአግባቡ የሚቀበሉ፤ ኢህአዴግ ሕልውናውን እንዳያከስምና ሌጋሲው እንዲቀጥል የሚፈልጉ ኃይሎች ናቸው። በውህደቱ ላይ ክስ የሚያቀርቡት ሰዎች ደግሞ ከሃዲዎች ናቸው ብለዋል።
አቶ አወሉ እንደሚሉት በትላልቅ ኃላፊዎችና አንጋፋ መሪዎች ጭምር በኢህአዴግ 5ኛ ፣ 6ኛ፣ 7ኛ እና 8ኛ ብሔራዊ ጉባዔ ስለ ውህደት ሲነሳ ነበር። “እስከ መቼ ነው በዚህ የምንቀጥለው? ለምንድን ነው ግንባርነት የተፈለገው? ለምን ውህደት አንፈጥርም?” የሚሉ ሃሳቦች ይነሱ እንደነበርና በ9ኛው ጉባዔ ጥያቄው እየገፋ መምጣቱን አንስተዋል።
በ10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔም ጥናቱ ቶሎ እንዲካሄድ እና ምክረ ሐሳብ እንዲቀርብ ተወስኖ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በአስቸኳይ ጥናቱ ተካሂዶ ውህደቱ እንዲፈፀም የሚል አቅጣጫ መቀመጡን ጠቁመዋል።
በዚህ ወቅትም ሁሉም እጁን አውጥቶ አጀንዳውንና፣ አቅጣጫውን ተቀብሎ መውጣቱንም አንስተዋል። ይህንን ተከትሎም ከአዲስ አበባ እና መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም የፖለቲካ ዲፓርትመንት አካባቢ ልምድ ያላቸው ሰዎች ተሳትፈውበትና ዓለም አቀፍ ተሞክሮም ተጨምሮበት እንዲሰራ መደረጉንና በዚሁ መሰረትም ጥናቱ ተጠናቆ ወደተግባር መገባቱን ገልፀዋል።
እንደ አቶ አወሉ ገለፃ ሩብ ምዕት ዓመት አገር መርተህ መጀመሪያ ስትነሳ ይዘህ የነበረውን የብሔር ጥያቄ ካልመለስክ፤ ወይ ውሸትህን ነው፣ ወይም እራሱ ውሸት ነው። አንዱ ችግር እሱ ነው። እውነት እንነጋገር ከተባለ ጽንፈኝነት ጫፍ ላይ ወጥቷል። “በአካባቢያዊ ጉዳይ ላይ ተጠምደን በአገራዊና የጋራ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ኢትዮጵያዊነት ላይ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል፤ አገር ሊኖረን ይገባል። ያለችን አገር አንድ ናት።
አቶ አወሉ እንዳሉት ብልጽግና ፓርቲ ከዚህ በፊት በሞግዚትነት፣በጀኔራልና በኮሮኔል ሆነን የምናስተዳድረውን አስቀርቶ እጃችንን አውጥተን በትክክለኛ መንገድ ክልሎች ራሳቸውን እንዲያስተዳድሩ የሚደረግበት ስርዓት ነው። ብዝሃነትን ስለሚያስተናግድም ሌሎች ተጨማሪ የፌዴራል ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ እንዲሆኑ እየታገለ ነው።
እንደ አቶ አወሉ ገለፃ፤ ከብልጽግና ፓርቲ እሴቶች አንዱ ኅብረ ብሔራዊነት ነው። ኅብረ ብሔራዊነት እኮ በኢሕአዴግ ዘመን የውሸት ፉከራና ዘፈን ነበር። በትክክል ምላሽ ያገኘ ጉዳይ አልነበረም። አሁን ግን በእውነት እና በእውቀት የብሔር ብሔረሰቦችን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ ፓርቲ ነው የተመሰረተው ብለዋል፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር