በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የሚታየውን አለመረጋጋት ግምት ውስጥ በማስገባት አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው በተያዘለት መርሐግብር መካሄድ አለበት ሲሉ አንዳንዶቹ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው መራዘም አለበት የሚል አቋም አላቸው፡፡ በአንጻሩ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ መርሐ ግብር ለማካሄድ ሽር ጉድ እያለ ይገኛል፤ በዚህ ስጋትና ተስፋ በተጋረጠበት ምርጫ 2012 የመገናኛ ብዙኃን ሚና ምን ሊሆን ይገባል?
ደበበ ኃይለገብርኤል የህግ ቢሮና የናሽናል ኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ የተባሉ ተቋማት “የአገራችን መገናኛ ቡዙኃን ሚና ለዳበረ ዴሞክራሲያዊ ሂደት በኢትዮጵያ” በሚል በቅርቡ ከስድስት ብሮድካስት የመገናኛ ብዙኃን ላይ 88 ዘገባዎችን በናሙናነት በመውሰድ የዳሰሳ ጥናት አካሂደው ነበር፡፡ ጥናቱ በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ የተከሰቱ ግጭቶችን የሚዲያ ተቋማት በምን መልኩ ዘገቡት የሚለውን ያሳየ እንደነበር በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል መምህር ፍሬዘር እጅጉ ይናገራሉ።
መምህር ፍሬዘር እንደገለፁት፤ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው መገናኛ ብዙኃኑ የግጭት ዘገባዎችን ሲዘግቡ ወገንተኝነት፣ ስሜታዊነትና ጽንፈኝነት የሚታይባቸው ነበሩ። እንዲሁም ለተፈጠሩ ችግሮች መፍትሄ ከመጠቆም አንጻር አሉታዊምና አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው አመላክቷል፡፡ በተለይ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ተቋማዊ መፍትሄ እንዲያገኙ አቅጣጫ ከመስጠት በተጨማሪ መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግና ለዜጎች ወቅታዊ መረጃዎችን በመስጠት በጎ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳበረከቱ በጥናቱ ተመላክቷል።
በአንጻሩ የሚፈጠሩ ችግሮችን ተባብሮ በመስራትና በመቻቻል መፍታት ያስፈልጋል በሚለው ላይ በስፋት እንደመፍትሄ ወስደው እንዳልሰሩ በጥናቱ መመላከቱን የገለፁት መምህር ፍሬዘር ገልጸው፤ ከዚህ አንጻር መገናኛ ብዙሃኑ ስለትናንትና ግጭት ዘገባዎቻቸው ሲያነሱ፤ እርቅና አንድነትን በሚያመጣ መልኩ አላወሱትም ብለዋል። ከዚያ ይልቅ ውስጣዊ ክፍፍልን በሚፈጥር መልኩና ትናንት በጭቆና ውስጥ ነበርን የሚል ብያኔ በመስጠት የተጠመዱበት ሁኔታ ነበር ይላሉ።
በአጠቃላይ ጥናቱ እንደሚያሳየው መገናኛ ቡዙኃኑ ገለልተኛ ተቋም ሆነው ተወዳዳሪና ተገዳዳሪ የሆኑ የተለያዩ አመለካከቶችን ባለማስተናገዳቸው የተለያዩ ቡድኖች፣ አንጃዎች፣ ብሄሮችና ፖለቲካ ፓርቲዎች መታገያና ፕሮፓጋንዳ መንዣ ሜዳ መሆናቸውንና የአገርን ህልውናና የህዝብን ጥቅም እንዳላስቀደሙ በዕለት ተዕለት ትግበራቸው አሻራቸው በግልጽ መቀመጡን ገልጸዋል።
መምህር ፍሬዘር እንደገለፁት፤ አንድ ምርጫ ግልጽ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የአንበሳውን ደርሻ ከሚጫወቱ ተቋማት መካከል የመገናኛ ቡዙኃን ሚና አይተኬ ነው። መገናኛ ብዙኃኑ በምርጫ ወቅት በብዙ መልኩ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ቢችሉም፤ በምርጫው የመጀመሪያ ግባቸው ገለልተኛ ሆነው ከጽንፈኝነትና ስሜታዊነት ተላቀው ትክክለኛና አስተማማኝ መረጃን ለዜጎች በማቅረብ መረጃ ያነገበ ዜጋ መፍጠር ይገባቸዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ፤ የመገናኛ ቡዙኃ ን ለህብረተሰቡ ያላቸውን ወገንተኝነትና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸውን ቁርጠኝነት ከሚያሳዩበት ወርቃማ አጋጣሚዎች ግንባር ቀደሙ የምርጫ ወቅት ነው ይላሉ።
ስለዚህ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ነጻና ግልጽ ሆኖ ሀሳቦች በነጻነት ተወዳድረው ህዝብ ያመነበት መንግሥት ወደ ስልጣን እንዲመጣ፤ የመገናኛ ብዙኃኑ ከወገንተኝነት እራሳቸውን አላቀው፣ የሚነቀፈውን በመንቀፍ የሚበረታታውን በማበረታታት፣ ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮችን ከሚመለከተው አካል ተገቢውን ማብራሪያ በመጠየቅ ለማህኅበረሰቡ ግልጽ በማድረግ ማኅበረሰቡ ምርጫው ላይ እምነት እንዲኖረው እና በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ይናገራሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በካሪኩለም እና ኢንስትራክሽን ትምህርት ክፍል ተባባሪ ፕሮፌሰር እንጉዳይ አደመ በበኩላቸው፤ አሁን በአገሪቱ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የመገናኛ ብዙኃኑ በሁለት ጎራ የቆሙ ሲሆን፤ በአንድ ወገን የቆሙት መንግሥት ምንም አይነት ህፀፅ እንደሌለበት በጎ በጎውን ያወራሉ። በሌላኛው ጽንፍ የቆሙት ደግሞ እንከንን ብቻ በማራገብ የመከፋፈል ሥራ ይሠራሉ።
ስለዚህ መጪውን ምርጫ በተመለከተ በሁለት ጽንፍ የቆሙት የመገናኛ ብዙኃን ተቀራርበው በመስራት ፍታሃዊ ሆነው የምርጫ ሂደቱን መዘገብ አለባቸው። በዘገባውም የአገርን ህልውና የህዝብን ጥቅም ማስቀደም ይገባቸዋል ይላሉ። በሚዘግቡበት ወቅትም ጥላቻንና ግጭትን በሚያጭር ሁኔታ ሳይሆን ህዝብና ህዝብን በሚያቀራርብ መልኩ መዘገብ እንደሚገባቸው ፕሮፌሰሯ አሳስበዋል።
በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብትና ተጠያቂነት እንዲሰፍን መገናኛ ቡዙኃኑ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የሚናገሩት መምህር ፍሬዘር ፤ በምርጫ ሂደቱ አጨቃጫቂ ጉዳዮች ሲኖሩ እራሳቸውን ገለልተኛ አድርገው ነገሩን ከስር ከመሰረቱ መርምሮ እውነታውን ለህዝብ በማሳወቅ እና አለመግባባቶች በሰከነ ሁኔታ የሚፈቱበትን መንገድ ማመላከት አለባቸው ይላሉ። መገናኛ ቡዙሃኑም በራቸውን ለአንዱ ክፍት ለሌላው ዝግ ሳያደርጉ ፤የሁሉንም የፖለቲካ ሀይሎች ሀሳብ ማስተናገድ የሚጠበቅባቸው መሆኑን መምህር ፍሬዘር ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ጌታቸው ድንቁ በበኩላቸው፤ የመገናኛ ብዙኃን ከምረጡኝ ቅስቀሳ ጀምሮ ምርጫው ተጠናቆ በህዝብ የተመረጠ መንግሥት ወደ ስልጣን እስኪመጣ ድረስ ያለውን ሂደት ደረጃ በደረጃ ለኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠት ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ አለባቸው።
በሌላ በኩልም ከዚህ ቀደም ምርጫ ላይ ተሳትፈው የማያውቁና ወደ መራጭነት የዕድሜ ክልል ለሚቀላቀሉ ወጣቶች ስለምርጫ ስርዓትና ህግ ግንዛቤ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል።
በምርጫ ቦርድና በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን አዋጅ አንቀጽ 44 እና 43 ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው፤ በምርጫ ወቅት የመገናኛ ብዙኃኑ ነጻ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምዶችን እየመደቡ እጩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳቦቻቸውን ለኅብረተሰቡ እንዲሸጡ ድምጽ ሆነው ማገልግል አለባቸው።
ባለፉት አምስት አገራዊ ምርጫዎች ላይ በከፍታም በዝቅታም ውስጥ እያለፉ የተሻለ የምርጫ ዘገባ በመስራት የተሻለ ምርጫ እንዲካሄድ ልምድ ያዳበሩ አንጋፋ መገናኛ ብዙሃን መኖራቸው ይታወሳል።
ከምርጫው ከኋላ እየተከተሉ አቃቂር ማውጣትና ጉድለቶቹን ማራገብ ሳይሆን፤ ከፊት እየቀድሙ አቅጣጫ እየሰጡ ሂደቱን መምራትና አደናቃፊ ሁኔታዎችን ከወዲሁ በመቅረፍ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲካሄድ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ እንደሚገባም ዶክተር ጌታቸው አሳስበዋል።
ምሁራኑ እንደሚሉትም፤ መገናኛ ቡዙሃኑ በምርጫ ሂደቱ በከፍተኛ የኃላፊነት ካልዘገቡ ትናንሽ ግጭቶች ጎልተው ወደ ቀውስ በመቀየር አገር ሊናጋ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው። በአንጻሩ ምርጫው ተቋማቱ ለአገርና ለህዝብ ጥቅም ዘብ መቆማቸውን የሚያሳዩበት ወርቃማ ዕድል በመሆኑ፤ ይህንን አደራ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መወጣት ከቻሉ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ በመቀየር የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዋልታን የሚተክሉበት አጋጣሚ ላይ እንደሚገኙ ምሁራኑ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
ሶሎሞን በየነ