አዲስ አበባ፤ የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጁ ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት የሚዘረጋ ፣ ሰፊ የሥራ ዕድልን የሚፈጥርና ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል ማድረግ እንደሚገባ ተወያዮች ገለጹ።
የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባካሄደው የህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ የውይይት መድረክ ላይ ተወያዮች፤ የኢንቨስትመንት አዋጁ ከመጽደቁ በፊት አንዳንድ ጉዳዮች በጥሞና መታየት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ቀላልና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት የሚዘረጋና የሚያድግ የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲፈጠር የሚያስችል እንዲሆንም ጠይቀዋል።
አነስተኛ ካፒታል ተብሎ ለውጭ ባለሃብቶች 200 ሺ ዶላር መቀመጡም ተገቢነት የሌለው በመሆኑ እንዲስተካከል ብሎም መሬትን ለሚጠይቅ ባለሃብት እስከ 60 እና 90 ቀናት በሚል የተወሰነው የጊዜ ሰሌዳ ፍጥነትን የሚገድብ በመሆኑ መስተካከል ይገባዋል ብለዋል።
አዋጁ ለውጭ ዜጎች የሥራ ቅጥርና ፈቃድ መፍቀዱ የኢትዮጵያውያን የስራ ዕድል እንዳያጠብ የሚል ስጋትም አንስተዋል። ባለሃብቶቹ ከተፈቀደላቸው ውጪ ኢትዮጵያውያንን በመቅጠር እንዲያሠሩ ግዴታ የሚጥል ግልጽ ድንጋጌ እንዲካተት ጠይቀዋል።
በተነሱት ጉዳዮች ላይ አስተያየትና ማብራሪያ የሰጡት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮምሽነር አቶ አበበ አበባየሁ፤ ለባለሃብቶች አነስተኛው ተቀማጭ 200 ሺ ዶላር መባሉ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል። ከእዚህ በላይ እንደመነሻ ቢቀመጥ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት አመቺ አይደለችም የሚል አስተሳሰብ ሊፈጥር እንደሚችልም ተናግረዋል። ለውጭ ባለሃብቶች አነስተኛ ካፒታል ማስቀመጥ ያስፈለገውም የባለሃብቱን ፍላጎትና ተነሳሽነት ለመለካት መሆኑን ነው የገለጹት።
የመሬት ጥያቄ ሲመጣ እንደየዘርፉ እስከ 60 እና 90 ቀናት እንዲያሳውቅ የተቀመጠውም ተጠያቂነት ለማስፈን መሆኑን ተናግረው፤ የውጭ አገር ሰራተኞች ቅጥርን አስመልክቶም፤ ባለሃብቶች ለትርፍ የሚመጡ እንደመሆናቸው የአስተዳደር ዘርፉን ከራሳቸው እንዲቀጥሩ ዕድል የሚሰጥ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከተቆጣጣሪነት፣ ከአሰልጣኝነትና ከሌሎች የቴክኒክ ሥራዎች፤ ከዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ከኦፕሬሽንና ከፋይናንስ ኃላፊ እንዲሁም ከከፍተኛ የማኔጅመንት አባላት ውጪ ያሉ ሥራዎችን ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን አሰልጥነው እንዲቀጥሩ የሚያስችል ስርዓት እንደሚዘረጋም ተናግረዋል።
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ፤ ኢትዮጵያ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ የሚያስችል ህግ እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባ፣ በኢንቨስተር ስም አገር ውስጥ ያላግባብ ገብተው ጉዳት እንዳያደርሱ ማጤንና በኢኮኖሚው ላይ ያለውን ችግር የሚፈታ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የሥራ ዕድል ፈጠራው ላይ ክፍተቶች እንዳሉ በመጠቆም፤ በርካታ የተማረ የሰው ሃይል አገር ውስጥ በመኖሩ አዋጁ ከወውጣቱ በፊት ለውጭ ባለሃብቶች የሚፈቀድና የሚከለከለው በአግባቡ ሊታይ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ሰብሳቢዋ በኢንደስትሪ ፓርኮች ባደረጉት የመስክ ምልከታ አገር ውስጥ ተመርተው ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ላይ 30 ዶላር ዋጋ ተለጥፎባቸው መመልከታቸውን አስታውሰው፤ በዓለም አቀፍ ገበያ ምርቶቹ እስከ 300 ዶላር ድረስ ሲሸጡ መመልከታቸውን መስክረዋል። በእዚህ ጉዳይም ጥንቃቄ እንዲደረግ አሳስበዋል።
የተንዛዛ የአሰራር ስርዓት በመዘርጋትም የውጭ ባለሃብቱ ተማርሮ እንዳይመለስ ቀላልና ቀልጣፋ የአሰራር ስርዓት ማካሄድ የሚያስችል ህግ እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ኢንቨስትመንቱ በኢኮኖሚው ዘርፍ እየተካሄዱ ካሉ ለውጦች ጋር እንዲናበብ ማድረግ በማስፈለጉ ህጉን ማሻሻል እንዳስፈለገ ተጠቁሟል። የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች በግሉ ዘርፍ ሊሳተፉ የሚችሉባቸውን የኢንቨስትመንት ሥራዎች በመከለስ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ዕድገትና ተወዳዳሪነት፣ በሥራ ፈጠራ እንዲሁም በቴክኖሎጂና ክህሎት ሽግግር ሚናውን እንዲወጣ ማድረግም የአዋጁ መውጣት ዓላማ መሆኑ ተጠቁሟል።
የኢንቨስትመንት አስተዳደርና ቁጥጥር ሥርዓቱን ማዘመን፣ የኢንቨስትመንት ማነቆ ለሆኑ ጉዳዮች መፍትሔ በመስጠት የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረግና የባለሀብቶች ቅሬታ የሚስተናገድበት ግልጽና ውጤታማ ሥርዓት ማበጀትም ለሕጉ መሻሻል ምክንያቶች ሆነው ተቀምጠዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
ዘላለም ግዛው