ሰው እንደ አሸን የሚፈላ በሚመስልባት መገናኛ አካባቢ በየካ ክፍለ ከተማ የመሬት አስተዳደር ቅጥር ግቢ በምትገኝ አንዲት በቆርቆሮ በተሰራች የፎቶ ኮፒ ማሽን ቤት አያሌ ሰዎች ተኮልኩለዋል። መረጃቸውን ፎቶ ኮፒ ለማድረግ የተሰለፉት ሰዎች በመስኮት እየሰጡ ገንዘብ በመክፈል ኮፒ የተደረገላቸውን ይቀበላሉ።
ተገልጋዮቹን ከሚያስተናግደው ፈርጠም ያለ ወጣት ግርጌ ልጅ አቅፈው ኩርምት ብለው የተቀመጡ ወጣት ሴቶች ይታያሉ። ፈርጣማው ወጣት ዋቂጅራ ቀጀላ ይባላል። ለአምስት ዓመታት በጎዳና ላይ ሕይወትን ገፍቷል። በጤናው ዘርፍ ተምሮ ያገኘውን የምስክር ወረቀት ይዞ ሥራ ለመቀጠር የተለያዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶችን በር ቢያንኳኳም ያገኘው ምላሽ ግን ተስፋ አስቆራጭ እንደነበር ይገልፃል።
ሥራ ሲጠፋ ለእለት ጉርስ የሚሆን ገንዘብ ለማግኘት በጉልበት ሥራ ላይ ይሠማራል። ነገር ግን ተምሮ ሥራ መፍታቱና ከእኩዮቹ በታች መሆኑ የፈጠረበት ጭንቀት የአዕምሮ ሕመምተኛ አድርጎ ለጎዳና ተዳዳሪነት ዳርጎታል።
በጎጃም በረንዳ አካባቢ በጎዳና ሕይወቱን እየገፋ የነበረው ወጣት ዋቂጅራ፤ ለአራት ዓመታት የአዕምሮ ሕሙማን መድሐኒት ሲወስድም ቆይቷልⵆ ከስምንት ወራት በፊት የህይወቱን አቅጣጫ የሚለውጥለትን ዕድል አገኘ። ከተማ አስተዳደሩ በጎዳና ላይ የወደቁ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በሠራው ሥራ ወደ ካምፕ መግባት ከቻሉ ወጣቶች መካከል አንዱ ሆነ። በዚያም መንግሥት ባመቻቸለት የሥነልቦና ምክርና የሕክምና አገልግሎት ወደ ቀድሞ ጤንነቱ መመለስ ችሏል።
በዚህ ብቻ አላበቃም ወጣት ዋቂጅራ ፤ እርሱና መሰል ጎደኞቹ 15 ሆነው ተደራጅተው የፎቶ ኮፒ የሥራ ዕድል ተፈጠረላቸው። እንደ ቀድሞው ጎዳና ላይ ውሎ ጎዳና ሳያድር ቤት ተከራይቶ ነገን ተስፋ አድርጎ እየኖረ ነው። ከሚያገኘው ገቢ ቁጠባ መጀመር ችሏል። ነገር ግን የተሰጣቸው ፎቶ ኮፒ ማሽን አንድ ብቻ በመሆኑ በሚፈለገው ደረጃ ስራቸውን መስራት አልቻሉም።
ለእርሱ እና ለጓደኞቹ መንግሥት ተጨማሪ ድጋፍ ቢያደርግላቸው ቁጠባቸውን አሳድገው የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደሚያስችላቸውና ወደ ሌላ ሥራ ሽግግር ለማድረግ በር እንደሚከፍትላቸው ይጠቁማል።
ከወጣቱ ግርጌ ልጅ ይዘው ኩርምት ብለው ከተቀመጡት መካከል ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ወደ አዲስ አበባ እህቶቿ ጋር ለመኖር የመጣችዋ ታደለች ተስፋዬ አንዷ ነች። ጥንቃቄ በጎደለው ግንኙነት እርግዝና ስላጋጠማት ከቤተሠቧ ጋር ጠብ ውስጥ በመግባቷ ከትውልድ ቀዬዋ ወደ አዲስ አበባ ገብተው ጎዳና ተዳዳሪ ከሆኑ ል ጆች ጋር ሕይወ ትን መጋፈጥ ጀምራለች።
በመዲናዋ ጎዳና ላይ የወደቁ ዜጎች ሲነሱ ዕድል ገጥሟት ወደ ካምፕ ብትገባም፤ በማገገሚያ ካምፑ ሲሰጥ የነበረውን የሙያ ስልጠና የደረሰች ነፍሰጡር በመሆኗ መከታተል አልቻለችም። ሆኖም ከጓደኞቿ ጋር በፎቶ ኮፒ ሥራ ላይ ተሰማርታ ተደራጅታ ሕይወቷን እየመራች ትገኛለች። በአሁኑ ወቅት የተሻለ ሁኔታ ላይ በመገኘቷ ተጣልታ ከተሸሸገቻቸው ቤተሰቦቿ ጋር እየተገናኘች እንደሆነ ትናገራለች።
ሌላው የቡድኑ አባል ወጣት ቃልኪዳን ሉሌ ሲሆን፤ በባህር ዳር ከተማ በተለያዩ ተንቀሳቃሽ ንግዶች ላይ ለ10 ዓመት ሲሰራ ቆይቶ ወደ አዳማ ከተማ በማቅናት ቤቱን ሸጦ በኮንትሮባንድ ንግድ ላይ ይሠማራል።
ሆኖም በደረሰበት ተደጋጋሚ ኪሳራ እጁ ላይ ያለውን ገንዘብ ሲያጣ የአዕምሮ በሽተኛ በመሆኑ ወደ ጎዳና ይወጣል። ለሁለት ዓመታት በጎዳና ላይ ህይወቱን ሲገፋ ቆይቶ፤ የከተማ አስተዳደሩ ጎዳና የወደቁ ዜጎችን ሲያነሳ እርሱም አንዱ የጎዳና ላይ ተነሺ የመሆን ዕድል አጋጠመው።
እንደወጣት ቃልኪዳን ገለፃ፤ የካ ክፍለከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ስልጠናዎችን እና ድጋፎችን ሲሰጣቸው ቆይቷል። በተጨማሪ አንድ የኖሮወይ ግብረሰናይ ድርጅት የሙያ ስልጠናና የስምንት ሺ ብር ድጋፍ የሰጣቸው በመሆኑ ክፍለ ከተማው ከስድስት ወር በፊት የፎቶ ኮፒ ማሽን ገዝቶላቸውና የመስሪያ ቦታ አመቻችቶላቸው ወደ ሥራ መግባት ችለዋል።
በሥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ዕድገት ቢታይም መልካም ጅማሯቸውን ወደተሻለ ደረጃ ለማሳደግ ሌሎች ተጨማሪ ማሽኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸው የሚጠይቀው ወጣቱ፤ በክፍለ ከተማው አመቻችነት ካገኘው ገንዘብ ባሻገር የተሰጡት የስነልቦና ሥልጠናዎች አስተሳሰቡን እንዲቀየር ከፍተኛ ሚና መጫወታቸውን ይናገራል።
በየካ ክፍለ ከተማ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ማያ ታደሰ እንደገለጹት፤ የከተማ አስተዳደሩ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ በልዩ ቁርጠኝነት ጎዳና ላይ ይኖሩ የነበሩ ዜጎችን ወደ ማገገሚያ ተቋማት በማስገባት መደበኛ ህይወትን እንዲጀምሩ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ይገኛል።
በማገገሚያ ተቋማቱም የሙያ ስልጠና፣ የህክምና ድጋፍ እንዲሁም የስነልቦና የምክር አገልገሎት በመስጠት ብቁ በማድረግ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ወደ መደበኛ ህይወት እንዲገቡ የማድረግ ሥራ በሰፊው እየተሰራ ነው። ለአብነት ከባለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ ከተማ አስተዳደሩ ጎዳና ላይ የወደቁ ዜጎችን ያነሳ ሲሆን፤ በየካ ክፍለከተማ በሚገኘው ግሎባል ማገገሚያ ካምፕ አንድ ሺህ አንድ መቶ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለእርዳታ ገብተው እንደነበር ይገልፃሉ።
ለእነዚህ ጎዳና ተዳዳሪዎች የስነ ልቦና የሙያ ስልጠና በመስጠት መስራት የሚችሉትን ተደራጅተው እንዲሰሩ በማድረግ፤ ሥራ የሚፈልጉትን የሥራ ዕድል በመፍጠር፤ ወደ ቤተሰብ መቀላቀል ያለባቸውን እንዲመለሱ በማገዝ፤ ከባድ የአካል ጉዳት ያለባቸውንና አቅመደካሞችን እንዲሁም ህጻናትን ቋሚ የዕርዳታ አገልግሎት ወደሚያገኙበት ግብረሰናይ ደርጅቶች በማስገባት አሁን ላይ በክፍለ ከተማው ማገገሚያ ካምፕ የሚገኙት 71 ተረጂዎች ብቻ መሆናቸውንም ያመለክታሉ።
የከተማው ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ልጆቹን የሚረዳ ለማፈላለግ ባደረገው ጥረት፤ ኤንአርሲ (ኖሮዌዥያን ሬፊውጂ ካውንስል) የሚባል ግብረሰናይ ድርጅት በማግኘቱ ለ15ቱ ልጆች ለእያንዳንዳቸው ስምንት ሺህ ብር ድጋፍና ስልጠና አድርጎላቸዋል። ያገኙትን ገንዘብ በአንድ ላይ በማድረግም የፎቶ ኮፒ ማሽን ገዝተው ሥራ መጀመራቸውን አብራርተዋል፡፡
እንደወይዘሮ ማያ ገለጻ፤ ወጣቶቹ የገንዘብ ድጋፍ ቢደረግላቸውም የመስሪያ ቦታ ማግኘት አስቸጋሪ ሆኖ ነበር። የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ የወጣቶቹን ችግር በመረዳትና ለክፍለ ከተማው ካቢኔ በማቅረብ በክፍለ ከተማው ህንጻ ላይና በመሬት አስተዳደር ቢሮ ግቢ ውስጥ ቦታ ተሰጥቷቸው ስራቸውን እንዲሰሩ ፈቅዶላቸዋል።
ስራውም ወጣቶቹን ውጤታማ አድርጓቸዋል የሚሉት ወይዘሮ ማያ፤ በየወሩም ከወጪ ቀሪ የሚያገኙትን ገንዘብ በደመወዝ መልክ እየወሰዱና ቁጠባም እየጀመሩ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የማህበራዊ ደህንነት ልማት ማስፋፊያ ዳይሬክተር አቶ እንደሻው አበራ በበኩላቸው፤ ከተማ አስተዳደሩ ከጥር 25 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ ጎዳና ላይ የወደቁ ዜጎችን ለማንሳት ከአጋር ድርጅቶች ጋር ስምምነት አድርጓል፤ በዚህም ስድስት ሺህ 205 ዜጎችን በሁለት ዙር ወደ ማገገሚያ ካምፕ እና በቋሚነት ወደሚረዱበት ተቋም እንዲገቡ የማድረግ ሥራ ተሰርቷል በማለት ይናገራሉ።
ወደ ማገገሚያ ካምፕ የገቡ ጎዳና ተዳዳሪዎችን የተለያዩ የስነ ልቦና እና የሙያዊ ስልጠና በመስጠት በፍላጎታቸው ተደራጅተው እንዲሰሩ በማድረግ፤ የሥራ እድል በማመቻቸት፤ ወደ ቤተሰብ መቀላቀል የሚፈልጉትን እንዲቀላቀሉ በማድረግ እና አካል ጉዳተኛና አቅመ ደካማ የሆኑትን ደግሞ በቋሚነት በሚረዱበት ግብረሰናይ ድርጅት እንዲታቀፉ ሆኗል፡፡
በአሁኑ ወቅት በማገገሚያ ካምፖች ሲረዱ ከቆዩት ሶስት ሺህ 434 ጎዳና ተዳዳሪዎች ውስጥ በከተማ አስተዳደሩ ማገገሚያ ካምፕ የሚገኙት 351 ብቻ መሆናቸውን ገልጸው፤ መንግሥት የጎዳና ተዳዳሪዎችን ህይወት ለማሻሻል በስፋት በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
ሶሎሞን በየነ