- የኢጣሊያ መንግሥት ታሪካዊ ቤቶችን ለማደስ ቃል ገብቷል
አዲስ አበባ፡- ከአክሱም ሐውልቶች መካከል 24 ሜትር ርዝመት ያለውና ‹‹ቁጥር ሦስት›› በመባል የሚታወቀው ሃውልት ጥገናው በጥር ወር 2012 ዓ.ም መጨረሻ ላይ እንደሚጀመር የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስታወቀ።
የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ጥገናውን ለማከናወን ከሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መካከል አብዛኞቹ በመጠናቀቃቸው የሃውልቱ ጥገና በጥር ወር መጨረሻ ላይ ለማስጀመር ዝግጅት እየተደረገ ነው። ከጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ ለጥገናው የሚያስፈልጉ እቃዎች ከውጭ ይገባሉ።
እንደርሳቸው ገለፃ፣ ሃውልቱን ለመጠገን የሚያስችለው ጥናት በአገር በቀሉ ኤም ኤች ኢንጂነሪንግ እና በኢጣሊያው ስቱዲዮ ክሮቺ ድርጅቶች በ2010 ዓ.ም ቢጠናቀቅም፣ ሃውልቶቹን በዓለም አቀፍ ቅርስነት የመዘገባቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ተቋም (ዩኔስኮ) ጥናቱን ለመገምገምና ተጨማሪ ምክረ ሃሳቦችን ለመስጠት የወሰደው የስምንት ወራት ጊዜ ስራው ቶሎ እንዳይጀመር አድርጎታል።
ዩኔስኮ ስለእድሳቱ የሰጠው ምክረ ሃሳብ ተጨምሮ ጥናቱ በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም ተጠናቋል። በ1999 ዓ.ም ከኢጣሊያ የተመለሰውን ሃውልት የተከለውና በዘርፉ የካበተ ልምድ ያለው ላታንዚ የተባለው የኢጣሊያ ድርጅት የሃውልቱን ጥገና እንዲያከናውነው አማካሪ ድርጅቶቹ ምክረ ሃሳብ በማቅረባቸው ከመንግሥት ግዢና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመነጋገር በነሐሴ 2011 ዓ.ም ስምምነት ተፈፅሟል።
‹‹ለጥገናው የሚያስፈልገው ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት ይሸፈናል። ለጥገናው ያስፈልጋል ተብሎ በእቅድ የተያዘው ገንዘብ ሦስት ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ዩሮ ቢሆንም ጥገናውን የሚያከናውነው ድርጅት በሁለት ሚሊዮን ዩሮ እንደሚያጠናቅቀው ስምምነት ፈፅሟል›› ብለዋል።
‹‹ቁጥር ሁለት›› በመባል የሚታወቀው የአክሱም ሃውልት በ1999 ዓ.ም ከኢጣሊያ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሲተከል በሌሎቹ ሐውልቶች ላይ መነቃነቅና ንዝረት እንዳይፈጠር ተብሎ በገመድ የተወጠረው ‹‹ቁጥር ሦስት›› ሃውልት የቆመው በመቃብር ስፍራዎች ላይ በመሆኑና አፈሩም በውሃ እየታጠበ በመምጣቱ የመዝመም አደጋ እንደተጋረጠበት ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የኢጣሊያ መንግሥት በአክሱም የሚገኙ ታሪካዊ ቤቶች ታድሰው የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባቱንም ዶክተር ሙሉጌታ ተናግረዋል።
የአክሱም ሃውልቶች በ1972 ዓ.ም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የተመዘገቡና በየዓመቱ በርካታ ቁጥር ያላቸውን ጎብኝዎችን የሚያስተናግዱ ዓለም አቀፍ ቅርሶች ሲሆኑ፣ በተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ችግሮች ተደቅነውባቸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
አንተነህ ቸሬ