ሐዋሳ፡- ‹‹ብልፅግና ፓርቲ ማንነትን ይጨፈልቃል በሚል የሚነገረው መሰረት የለውም›› ሲሉ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ርስቱ ከአዲስ ዘመን ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ እንደገለፁት፤ በቅርቡ ከምርጫ ቦርድ የእውቅና ሰርተፊኬት ያገኘው የብልፅግና ፓርቲ አሃዳዊነትን ያሰፍናል እንዲሁም ማንነትን ይጨፈልቃል በሚል የሚነገረው መሰረት የለውም፡፡
‹‹ውስጣችን ከነበረ መለያየትና አንዱ አንዱን ጥሎ ለማለፍ ከማሰብ የሚመጣ ካልሆነ በስተቀር በምንም መንገድ ብልፅግና ፓርቲ አሃዳዊነትን አያመጣም፡፡›› ሲሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጠቅሰው፤ ‹‹የፓርቲው ስብስብ እኛው ነን፤ ስብስቡ ከሁሉም ብሄር ብሄረሰብ የተውጣጣ በመሆኑ አዲስ የመጣብን አካልም የለም፡፡
ቀደም ሲልም የነበረው ያው ብሄር ብሄረሰብ ነው፤ ያ ብሄር ብሄረሰብ ደግሞ ስለራሱ ማንነት ከማንኛውም በላይ የሚቆረቆር ሆኖ ሳለ ለመጨፍለቅ የሚመጣን ፓርቲ በምንም አይነት መልኩ አይቀበለውም፡፡›› ብለዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን አንዱ የጎደለን ቢኖር ባለፈው ስርዓት ውስጥ በማንነት ላይ እንደሰራነው ሁሉ በኢትዮጵያ አንድነት ላይ የሰራነው ደካማ መሆኑ ነው፡፡ የእኔ ሰፈር፣ አካባቢ፣ መንደር በሚል የገነባነው ማንነት ላይ ብቻ ነው›› ሲሉ ጠቅሰው፣ ‹‹እሱ የትም አያደርሰንም፤ ይልቁንም ብኩን ያደርገናል›› ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ ገለጻ፤ የአማራው አቅም የደቡብ አቅም ነው፤ የደቡቡ አቅም የአማራው አቅም ነው፡፡ የኦሮሞው አቅም የደቡቡ ነው፤ የሌላውም እንዲሁ፡፡ አገርን መገንባትና ወደፊት መውሰድ የሚቻለው እንዲህ አይነት መንፈስ በመፍጠር ነው፡፡
‹‹በብዙ መንገድ የተሳሰርን ህዝቦች በመሆን አብረን እየኖርን ነን፡፡ ማንነት እንደ ተጠበቀ ሆኖ አትዮጵያ የምትባል የጋራ አገር አለችን፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ሁላችንም በኢትዮጵያዊነታችን እኩል ሆነንና በየትኛውም ስፍራ ተንቀሳቅሰን በእኩል የምንዳኝበት፣ የምንታይበት እንዲሁም በእኩልም ክብር የምናገኝበትን አገር መገንባት አለብን፡፡ የብልፅግና ፓርቲ እሳቤውም ይኸው ነው::›› ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እንደተናገሩት፤ እሳቤው ይህ ከሆነ ጨፍላቂ ነው፤ አፋኝ ነው ተብሎ የሚወራው ለፖለቲካ ትርፍ ካልሆነ በስተቀር በምንም መንገድ አሃዳዊነትን ያመጣል ተብሎ አይታሰብም፡፡
በመሰረቱ ሊሆንም አይችልም፤ የፓርቲው ህገ ደንብም እንደዛ አይልም፡፡ ፓርቲው የብሄር ብሄረሰቦችን ቋንቋ፣ ታሪክ፣ እሴት፣ ባህልና ማንነትን አክብሮ በጋራ ደግሞ ኢትዮጵያን እንገንባ የሚል አስተሳሰብ ያያዘ ነው፡፡
በፓርቲው ዙሪያ በማወያየቱ በኩል ሁሉም ዘንድ መድረስ መቻሉን ጠቅሰው፣ ጥሩ ነገር የመኖሩን ያህል ስጋትም ጎን ለጎን መኖሩን ከውይይቱ መረዳት እንደተቻለም ተናግረዋል፡፡
ደቡብ ባለፉት 28 ዓመታት የተከተለው ስርአት አንዱ የሚኮራበትና ዋጋ የሰጠውና እውቅናም ያገኘበት፣ ማንነቱ የታወቀበት፣ ታሪኩና ቋንቋው እንዲያድግ የተደረገበት መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ክልሉ አብሮ መኖርን የተለማመደ መሆኑን ጠቅሰው፣ አብሮ መኖርን እንደሚፈልግ ገልጸዋል፡፡
ሰሞኑን በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ ጉብኝት በማድረግ ውይይቶችን ማድረጋቸውን ለአብነት በመጥቀስም፣ ሁሉም ‹የእኔ መሪ ››ብሎ እንደተቀበላቸውም ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ህዝብ የዚህ አይነት ልምድ እንዳለው አስታውቀው፣ በዚህ ልምዱና አብሮነቱ ላይ አዲሱ የብልፅግና ፓርቲ ተፅዕኖ ይፈጥር ይሆን በሚል ጥርጣሬም ስጋትም ከመኖር ባሻገር በጥያቄ መልክ የሚነሳ ነገር አለ::›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
አስቴር ኤልያስ