አዲስ አበባ፤ “ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ጉባዔውን ሲያጠናቅቅ ያወጣው የአቋም መግለጫ ከድሮ የበላይነቴ ለምን ለቀቅኩ የሚል እንድምታ ያለው፤ የመገለልና ባዕድ ስሜት እንደተሰማው የሚያሳይና ለጦርነት እንደተዘጋጀ የሚያመለክት ነው” ሲሉ በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
በክልሉ የሚንቀሳቀሰው የአረና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤ ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለመጀመሪያ ጊዜ ያካሄደውን አስቸኳይ ጉባዔ ሲያጠናቅቅ ባወጣው የአቋም መግለጫ ውህደቱን አልቀበልም፣ ከኢህአዴግ የጋራ ሀብት እካፈላለሁ እና በውስጥ እንቅስቃሴዎች እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱን እንደሰሙ ጠቁመው፤ ‹‹ሁኔታው ወደግጭት የሚያስገባ ይመስላል›› ብለዋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ የህወሓት መሪዎች ኢህአዴግ በመፍረሱ ከፍተኛ ቁጭት እንደተሰማቸው ያሳያል፡፡ያስተላለፉት መልዕክትም የመገለል እና ባዕድ ስሜት እንደተሰማቸው የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም ወደ ግጭት ሊያድግ እንደሚችልና እነርሱም ለጦርነት እንደተዘጋጁ የሚያመለክት አንድምታ አዝሏል›› ብለዋል አቶ አምዶም፡፡
እንደኃላፊው ማብራሪያ፤ መልዕክቱ ለትግራይ ህዝብ ጥሩ ዜና አይደለም፡፡ ህብረተሰቡ ከችግሩ መውጣት አለበት፣ ካለበት ችግርም የሚያወጣው ይፈልጋል፡፡ ድርጅቱ የጦርነት ፕሮፖጋንዳ መንዛቱም ለኅብረተሰቡ ጥሩ ነገር የለውም፡፡
‹‹ሁልጊዜም ምክንያትና ሰበብ የሚያደርጉት እኛን ነው:: ዛቻ ይደርስብናል፣ ጉዳትም እያደረሱብን ይገኛሉ ፤ሰላማዊ ታጋዮች በመሆናችንም ይጎዱናል፤ ይህ ግን ጥሩ አይደለም›› ያሉት አቶ አምዶም፤ ‹‹ህግም ህገ መንግሥቱም መከበር አለበት›› ብለዋል፡፡ ድርጅታቸው አረና ዘንድሮ ለሚደረገው ምርጫ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ በመጠቆምም፤ የህወሓት አቋምም መስተካከል እንዳለበት መክረዋል፡፡
የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ ህወሓት ከብልጽግና ተነጥሎ ራሱን የቻለ ፓርቲ ሆኖ መንቀሳቀስ መብቱ መሆኑን ተናግረው፣ ድርጅቱ ከዚህ በላይ አስተሳሰብ መያዙን ይጠቅሳሉ፡፡ ድርጅቱ የብልጽግና ፓርቲን እየወነጀለና እየከሰሰ መሆኑን በመጠቆም ውንጀላው የውጭ ሃይሎችን ጣልቃ ገብነት የሚፈቅድ ድርጅት አድርጎ እስከመክሰስ የደረሰ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
ሂደቱ ግጭትን የሚፈልግ አይነት ነው፡፡ መግለጫውን ህወሓት የትግራይ ህዝብ ተከብበሃል፣ ጠላት አለህ፣ ታጠቅና ክተት በማለት ከሚነዛው ፕሮፖጋንዳ ጋር አይይዘን ብናየው ከድሮ የበላይነቴ ለምን ለቀቅኩ፣ የሚያስለቅቀኝም ብልጽግና ነው የሚል እንድምታ አለው፡፡ ከዚህም ባለፈ የጸብ አጫሪነት፣ ወደ ግጭት የመግባትና ወደ ጦርነት የመግባት ፍላጎት ያለው ድርጅት መሆኑንም ያመለክታል ሲሉ አብራርተዋል፡፡
‹‹ህወሓት ትግራይ ውስጥ የበላይ ሆኖ ባለፉት 27 ዓመታትም የኢህአዴግ መሪ ሆኖ ኢትዮጵያን በግጭት፣ በድህነትና በኋላቀርነት ጠፍንጎ የያዘ መሆኑ ይታወቃል›› የሚሉት ዶክተር አረጋዊ፤ አሁን ያንን የበላይነቱን ሲያጣ ትግራይ ውስጥ መመሸጉን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የትግራይ ህዝብ ከለላ እንዲሆንለት በማሰብም ተከብበሃል ስለዚህም ለጦርነት ክተት በማለት ሌት ተቀን እየጮኸ ነው። ሌሎች ድርጅቶች ሁኔታው ትክክል እንዳልሆነ ለህዝቡ ለማስረዳት ሲሞክሩ ባንዳ፣ ከሃዲ በማለት እያሰረና እየደበደበ ይገኛል›› ሲሉም ገልጸዋል፡፡
መግለጫው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በሚያደርጉት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ላይም ትልቅ ጫና እንደሚፈጥር ዶክተር አረጋዊ ጠቅሰው፤ የለውጥ አየር እንዳናስተጋባ ተደርገናል ብለዋል፡፡ ድርጅቱ ህዝቡ በሚፈልገው ድርጅት ስር ተሰባስቦና ተደራጅቶ የሚፈልገውን እንዲደግፍ፤ የማይፈልገውን እንዲተው የሚችልበትን ሁኔታ እንዳያገኝ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ ‹‹በእኛ በተፎካካሪዎች ላይ ትልቅ ችግርና ጫና እያሳደረብን ነው:: ተጽእኖው ከእኛ አልፎ በህዝብ ላይ ነው፡፡ በሚቃወሙት ላይ የሚሰነዝራቸው ስሞች አሳፋሪና ዘግናኝ ናቸው፡፡ በመሆኑም ተጽዕኖው ቀላል አይደለም፡፡››ብለዋል፡፡
‹‹ምንም ቢሆን የጀመርነውን እንቅስቃሴ አናቆምም:: ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እስኪመሰረት፣ የኢትዮጵያም ሆነ የትግራይም ህዝብ የራሱን ዕድል በራሱ ወሳኝ እንዲሆን፣ ድምጹን በነጻነት በካርድ እንዲወስን ያለው ያለመገሰስ መብቱ ተግባራዊ እንዲሆን ትግላችን ይቀጥላል፡፡ ለተነሳንለት የዴሞክራሲ ስርዓት መገንባት አላማ ወደ ኃላ አንልም፡፡ ህወሓት ኢህአዴግ ሆኖ ሲያካሂደው እንደነበረው አይነት ምርጫ ተብዬ እንዲደረግ አንፈቅድም፡፡ ሁኔታው መለወጥ አለበት፡፡››ሲሉ አብራርተዋል፡፡
ዶክተር አረጋዊ አንዳሉት፤በመላው ኢትዮጵያ የለውጥ አየር ሊተነፍስ የቻለው ህዝቡ ጠንክሮ ስለታገለ ነው:: በመሆኑም የትግራይ ህዝብ በተለይም ወጣቱ ትግራይ ውስጥ ዴሞክራሲ እንዲሰፍን መታገል ይኖርበታል፡፡ ትግራይ ሁለት አይነት ተፎካካሪ ድርጅቶች አሉ፡፡ ግማሾቹ የህወሓት ተቀጽላዎች ናቸው፡፡ በህወሓት ላይ የሚሰነዝሩት ስሞታ የለም። ይህንን የትግራይ ህዝብ ለይቶ ሊያውቅና ድጋፍና ዕድልም ሊነሳቸው ይገባል ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 29/2012
ዘላለም ግዛው