- ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተጠቁሟል
አዲስ አበባ፦ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት 90 ከመቶ የሚሆኑት የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች በትክክል እንደማይቆጥሩ ገለጸ። ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑንም አመልክቷል።
በአገልግሎቱ የአውቶሜሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ደመቀ ሮቤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ቆጣሪዎቹ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ በመሆኑ ከሚያነቡት ይልቅ የማያነቡት እንደሚበልጡም ተናግረዋል።
አገሪቱ በቴክኒካልና ኮሜርሻል /የንግድ/ ብክነት የተነሳ በአጠቃላይ ከሚመረተው ሀይል ከ20 በመቶ በላይ ታጣለች ያሉት አቶ ደመቀ፤ ተቋሙም በትንሹ ከመቶ ብር ሃያ ብር ያጣል ብለዋል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ባለው የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ላይ ሌላ ፈተና መሆኑንም አመልክተዋል።
እንደ አቶ ደመቀ ገለፃ፤ አገልግሎቱ ካሉት 3 ሚሊዮን ደንበኞች በካርድ በቅድመ ክፍያ የሚሰራ ቆጣሪ ያላቸው ደንበኞቹ 600ሺ ብቻ ሲሆኑ ይህን ቁጥር በአጭር ጊዜ ውስጥ በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ነው። ሽያጩንም በሞባይል ባንኪንግ አማካኝነት በየትኛውም ቦታ ተደራሽ ለማድረግ እየሰሩ ሲሆን በዘንድሮው ዓመትም ተግባራዊ ይደረጋል፡፡
በካርድ የሚሰሩት የቅድመ ክፍያ ቆጣሪዎች እስካሁን በሽያጭ ማዕከል ብቻ ስለሚቀርቡ ለገጠር ደንበኞቻቸው ተደራሽ አልሆነላቸውም የሚሉት አቶ ደመቀ፤ በቀጣይ ክፍያው በሞባይል ባንኪንግ ሲጀመር ግን አገልግሎቱ ለሁሉም ደንበኞች ምቹ ይሆናል ብለዋል። በመሆኑም በካርድ የሚሰራውን ቆጣሪ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነ ጠቁመዋል።
በዓለም ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ቆጣሪ ስማርት ሜትር የሚባል መሆኑን ያነሱት አቶ ደመቀ ይህን ተግባራዊ ለማድረግ በአገር ውስጥ እንዲመረት ጥረት እየተደረገ መሆኑንና በቀጣይ በአገር ውስጥ አምርቶ ተግባራዊ ለማድረግ መታቀዱን ጠቁመዋል።
ስማርት ሜትር ቆጣሪ በማከፋፈያ ጣቢያ ደረጃ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ፣ በመቀሌ፣ በባህርዳር፣ በሃዋሳ፣ አዳማና ሌሎች ከተሞች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን፤ ከሃይል ማመንጫ ምን ያህል ወደ ተጠቃሚ እየደረሰ እንደሆነ ለማወቅ እየተጠቀሙበት እንደሆነ አቶ ደመቀ ጠቅሰዋል።
በተጠቃሚዎች ቤት አሁን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ግን ከ2 ሺ እስከ 3ሺ ብር ስለሚጠይቅ ተግባራዊ ለማድረግ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል።
ይህ ቆጣሪ የኤሌክትሪክ ክፍያን ለመቆጣጠር፣ ስርጭትን ለመስጠትም ሆነ ለማቋረጥ፣ የሃይል መጠን ለመቀነስና ለመጨመር፣ የሀይል ሌብነትና ብክነትን ከማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር፣ እና ሌሎች አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችሉ 30 አይነት መለኪያዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት አቶ ደመቀ፤ ለአንዱ ቆጣሪ እስከ 2500 ብር እንደሚወጣም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ