አዲስ አበባ፡- በአገሪቱ የፍርድ አሰጣጥ ሥርዓት ፍትሀዊ፣ ግልፅ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ የፍርድ ቤት የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር እንዲኖር የሚወስዱት ጊዜ ተገማች መሆን እንዳለባቸው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስታወቀ።
የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ረቂቅ መመሪያን ለማፅደቅ ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞች ጋር በተዘጋጀው ውይይት ላይ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ አሸነፈች አበበ እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ዘመናዊ የፍትህ አሰጣጥ ሥርዓት በህግና በተቋም ተደራጅቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ቢያስቆጥርም የጉዳዮች ፍሰት አስተዳደር ባለመተግበሩ አንድ የፍርድ ቤት ጉዳይ ከተገቢው ጊዜ በላይ እየወሰደ ነው፡፡
በፍትሐብሔር ህጉ ላይ ጉዳዮች እንዴት እልባት ማግኘት እንዳለባቸው ቢመላከትም የጉዳዩ ፍሰት አስተዳደር ተግባራዊ ባለመደረጉ የዜጎች የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት ሂደትን አስተጓጉሎታል።በተጨማሪም የጊዜና የገንዘብ ኪሳራም እያስከተለ ይገኛል ብለዋል፡፡
እንደ ምክትል ፕሬዚዳንቷ ገለጻ፤ ፍርድ ቤቶች ይህንን ችግር ለመፍታት አሰራራቸውን በማሻሻልና በማዘመን የዳኝነት ሥርዓቱን በማጠናከር የተገልጋዮችን እርካታ ማሳደግ አለባቸው።በዚህም ፍርድ ቤቶች የጉዳዮች ፍሰትን ተገማች፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው እንዲሆኑ ለማድረግም ይሰራል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሰላማዊት ግርማ በበኩላቸው፤ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ፍፃሜ እስኪያገኝ ድረስ ያለው ሂደት ግልፅ ባለመሆኑ የፍርድ ሂደቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳረፈ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጉዳዮች ፍሰት በተገቢው ጊዜ እንዲያልቅና ሳይዘገዩ ውጤታማነትን እንዲያመጡ ለማድረግ ከባለ ጉዳዮች ጋር በመቀራረብ መስራት፣ ዳኞች ለሙያቸው ቁርጠኛ እንዲሆኑ ማድረግ፣ ከዘልማዳዊ አሰራር መውጣት፣ ከማንኛውም ማህበረሰብ ተጽዕኖ ነፃ መሆንና የአሰራርና የአደረጃጀት ሂደትን ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
‹‹የአንድ ሀገር የፍትህ አሰጣጥ ስርአት የሚለካውና የህግ አሰጣጥ ፍሰት አለ የሚባለው አንድን የክስ ጉዳይ በጊዜ ገደብ ግልፅና ከአድሎአዊ አሰራር በፀዳ መልኩ ውሳኔ መስጠት ሲቻል ነው›› የሚሉት ደግሞ በአለም አቀፍ ባንክ የቢዝነስ ሪፎርም ባለሙያ የሆኑት ፋንቱ ፋሬሳ ናቸው።እርሳቸው እንደገለጹት፤ ዳኞች ይህን ለማድረግ የክሱ ክርክር ከመጀመሩ በፊት ማጥናትና ግንዛቤ መያዝ አለባቸው።
ኢትዮጵያ ውሳኔ ለሚሹ የፍርድ ቤት ጉዳዮች በፍጥነት ውሳኔ ከመስጠት አኳያ ከተለያዩ ሀገሮች ጋር ስትወዳደር ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 26/2012
ሞገስ ፀጋዬ