• 210 ሚሊዮን ብር የሚገመት አደንዛዥ እጽ በቁጥጥር ስር ውሏል
አዲስ አበባ፦ በአምስት ወራት ውስጥ ብቻ 1ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችና ገንዘቦች በመላ ኢትዮጵያ መያዛቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ።
በጉምሩክ ኮሚሽን የጉምሩክ ህግ ተገዥነት ዘርፍ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ባሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት ብቻ የአንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ግምት ያላቸው እቃዎች እና የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችን መያዝ ተችሏል። በተለይ ከገቢ ኮንትሮባንድ ውስጥ የ210 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ አደንዛዥ እጾች ተይዘዋል።
እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ፤ ከተያዙ ወጪ ኮንትሮባንዶች ደግሞ ብልጫ ዋጋ ያለው በህገወጥ የገንዘብ ዝውውር አማካኝነት የተያዙ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች ናቸው። 74 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የምንዛሬ ተመን ያላቸው የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችም በድንበር ኬላዎች እና ኤርፖርቶች ላይ ተይዘዋል።
ባለፈው ዓመት ሙሉ ጊዜ የተያዘው ኮንትሮባንድ አንድ ነጥብ ስድስት ቢሊዮን ብር የሚገመት ንብረት መሆኑን ያስታወሱት አቶ አሸናፊ፤ በዘንድሮው ዓመት አምስት ወራት ብቻ ግን የአመቱን አፈጻጸም የሚቃረብ ቁጥር መመዝገቡ የኮሚሽኑ ኮንትሮባንድ የመያዝ አቅም መጠናከሩን እንደሚያሳይ ገልጸዋል። በሌላ በኩል ግን የኮንትሮባንድ ፍሰቱ መጨመሩን የሚያሳይ ጠቋሚ መረጃ ሊሆንም እንደሚችል ተናግረዋል ። በአጠቃላይ ግን በቦሌ ኤርፖርት ጉምሩክ በኩል የተያዙ ዕቃዎች እና ገንዘቦች ጨምሮ ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ፣ ሞያሌ እና ሀዋሳ ጉምሩክ ጣቢያዎች እንደ የደረጃቸው ከፍተኛ ኮንትሮንድ የተያዘባቸው ኬላዎች መሆናቸውን አስረድተዋል።
እንደ አቶ አሸናፊ ገለጻ፤ ኮሚሽኑ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በመተባበር ከሰባት መቶ የማያንሱ የኮንትሮባንድ መከላከል ፖሊሶችን በማሰማራት እና ኬላዎችን በማብዛት የሰራው ስራ ውጤታማ እያደረገው ይገኛል። ከዚህ ቀደም አንድ ኮንትሮባንድ ሲያዝ ለእጀባ እና ለተለያዩ የህግ ስራዎች የፌዴራል ፖሊስን በደብዳቤ የሚጠየቅበት አሰራር ነበር። አሁን ግን በየጊዜው የሚያዙ ኮንትሮባንዶችንም የጉምሩክ ፖሊሶች እንደ መደበኛ ስራቸው በመቁጠር ከእጀባ ጀምሮ እየተከታተሉ ወደህግ ቦታ በማድረስ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ይገኛሉ። መደበኛ የጉምሩክ ፖሊስ መቋቋሙም ወንጀሉን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ተጨማሪ አቅምን ፈጥሯል። ከዚህ በተጨማሪ መከላከያ ሰራዊት እና ሌሎች በየአካባቢው የሚገኙ የጸጥታ ኃይሎች ለኮንትሮባንድ ቁጥጥር ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ይገኛል።
በሌላ በኩል የጉምሩክ ኮሚሽን በበጀት አመቱ ማጠቃለያ ከ98 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ ያቀደ ሲሆን፤ ባለፉት አምስት ወራት ብቻ 44 ቢሊዮን 618 ነጥብ8 ሚሊየን ብር በላይ ሰብስቧል። እንደ ኮሚሽኑ መረጃው ገቢው ከዕቅዱ 103 በመቶ ከመሆኑ ባለፈ ባለፈው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት ከተሰበሰበው የ29 ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር ገቢ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ብልጫ አሳይቷል። ከዘንድሮ አመት ገቢ በሞጆ ቅርንጫፍ የተሰበሰበው 16 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር እና በአዲስ አበባ ቃሊቲ ጉምሩክ የተሰበሰበው 14 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛሉ።
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
ጌትነት ተስፋማርያም