ስኬታማ ሰዎች ለሚሰሩት ሥራ ጥብቅ ሥነ ሥርዓት አላቸው፤ የሚገዛቸው የማያመቻምቹት ሥርዓት ነው፤። ሲሠሩ ሊሠሩ የሚገባቸውን ነገር ይሠራሉ እንጂ፣ የሚፈልጉትን ነገር አይሠሩም። እንዲህነታቸውም ነው፤ ከነበሩበት ከዚህ ግባ የማይባል ደረጃ፣ ወደ መልካምና ወደልህቀት ደረጃ ያሸጋገራቸው። ለዚህም ነው፤ ለሽልማት ሳይሆን ለሥራው ስኬት ስለሚሠሩ፤ እነዚህን ሰዎች ሽልማት የተባለ ሁሉ የሚከተላቸው።
ስኬትን ባጋጣሚ አናገኛትም፤ ከቶውንም። ታላቅ የተባለ ነገር ትልቅ ድካምና መስዋዕትነትን የሚጠይቅ መሆኑን አትርሱ። ወደግባችሁ ለመድረስ የምታደርጉት ጥረት እልህ አስጨራሽና ተደጋጋሚ መንገዶችን ፈትሾ በመውደቅና መነሳት ውስጥ የሚገኝ ነው። ይህ ዓላማ ታዲያ፣ ካንተ፣ ጊዜህን፣ ጥረትህን፣ ጽናትህንና ጉልበትህን፣ ይጠይቅሐል። ራስን በሥርዓት መግዛትም፣ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ፣ ትልቅ እገዛ አለው።
እናም መልካም ዜና ግን አለን። ግላዊ ሥነ ሥርዓትህን (ዲሲፕሊንህን) አንተው ማዳበር ትችላለህ። ማንኛውም ሰው ከሥርዓትና ከእውቀት ጋር አልተወለደም። ይህ የባለራዕዩ ወይም የባለ አላማው ምርጫ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። ወደግቤ ለመድረስ ልከፍል የሚገባኝን ማናቸውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፤ ማለት ነው፤ ያለበት።
ወደአላማህ ለመገስገስ ብርቱ ውሳኔ ካለህ የሚከተሉትን ነጥቦች በልብህ ያዛቸው። (መልዕክት ሲልኩን፣ ልብ በል እንዲሉ እናቶቻችን!!)
1ኛ/ በሥራህ ላይ ዋነኛው ነገር ምን እንደሆነ ለይ፡- ልትሠራ የምትፈልገው ዋነኛው ነገር ምን እንደሆነ ካወቅክ ፤ በየጥቃቅኑ ነገር ላይ ጊዜ አታባክንም። ጊዜን ሊበሉ ከሚችሉ ከጉዳዩ ጋር ካልተያያዙ ነገሮችም ራስህን ታርቃለህ። ያኔም ዋነኛውንና አስፈላጊውን ነገር ብቻ አድምተህ ለመሥራት ዝግጁ ትሆናለህ። በእግር ኳስ ጫዋታ ላይ ከአቋቋምህ አንፃር፣ ኳሱ ወደአንተ ከመምጣቱ በፊት ምን እንደምታደርግ ቀድመህ ታስባለህ እንጂ፤ ኳሱን ላንተ ካቀበሉህ በኋላ ምን ላድርገው ብለህ መጨነቅ የብልህ ተጫዋች የአጨዋወት አካልም፤ ስልትም አይደለም። ስለዚህ ምንን እንደምታስቀድም ቀድመህ እወቅ።
ይህንን ወደ አንድ ድርጅት ዓላማ ከፍ አድርገህ ስታስበውም በዋነኛው ጉዳይ ላይ ማተኮር ወደ ውጤት የመገስገሻ ጥበብ ነውና በሥራህ ላይ ቅድሚያ ልትሰጠው የሚገባውን ነገር ለይተህ እወቅ።
2ኛ/ ይቅርታ ወይም አዝናለሁ፤ ለማለት አትዘጋጅ። የምትሠራቸውን ሥራዎች ባለመሥራትህ ወይም በጊዜው ባለማድረስህ በትንሽ ትልቁ አዝናለሁና ይቅርታ ይደረግልኘ ለማለት የተዘጋጀ ነፍስ አይኑርህ። ሥርዓታዊነት ወደስኬታችን የሚወስደን አውራጎዳና በመሆኑ ይቅርታን የመውጫው መንገድ ልታደርገው አይገባም። የምትሠራውን ሥራ የምትሠራው መሠራት ስላለበት እንጂ፤ ላለመሥራት ምክንያት በማበጀት አይደለም።
ስለማምለጫ የምታስብ ከሆነ የሚከተሉትን ማምለጫዎች እያሰብክ እንደሆነ አስባለሁና ባታደርገው ይመረጣል።
• አሁን ሁኔታው አይመችም፤ በሚቀጥለው ዓመት ሁኔታው ሲረጋጋ ብቀጥለው ይሻላል።
• ብቻዬን እንዴት እችለዋለሁ።
• ጉልበት ላሰባስብና እሞክረዋለሁ።
• ሌሎች ሥራዎች ውጥር አድርገውኛል።
• በጡረታ ዘመኔ እሠራቸዋለሁ።
• በጉዳዩ ላይ ብዙ ልምድ የለኝም።
• በጣም ያስፈራል እኮ።
• እንዴት እንደሚጀመር አላውቅበትም። ወዘተ…
ራሴ ከላይ ከጠቃቀስኳቸው ሰበባ ሰበቦች፣ ብዙዎቹን ተጠቅሜባቸዋለሁ፤ ግን አንዳቸውም የሚያኮሩ፤ ሆነው አላገኘኋቸውም። “ለመሆኑ እንዲኖረኝና እንድደርስበት የምፈልገውን ነገር ከመሥራት ይኼ ይከለክለኛል ወይ?” ለማለት ከቻልን በእርግጥ የምንወደውንና የምንፈልገውን ነገር እንሠራዋለን።
3ኛ/ “ላድርገው እንዴ?” ከማለታችሁ በፊት ማድረግ ጀምሩ። አንዳንዴ ልታደርጉ ውስጣችሁ አለቅጥ የሚመላለስ ሐሳብ ካለ አታመንቱ፤ ወደሥራው ግቡ እንጂ ላድርገው ወይስ… ማለት ከጀመራችሁ አላድርገው ማለትም ስላለ፤ ተቃራኒውና አታድርገው የሚለው ሐሳብ ሊወርሳችሁ እንዲችል ዕድል አትስጡት። ስለዚህ መንፈሳችሁ ለሥራ በተነሳበት በትግሉ ሰዓት መሥራት ጀምሩ፤ ቀጥሉ እንጂ መንታ ልብ አትሁኑ።
እያንዳንዱ ሰው ሊያልፈው የማይችለው የራሱ ደካማ ጎኖች አሉት። የግድ ግን ሊያርማቸውና ሊሻገራቸው ይገባል። ደካማ ጎኑን እሽሩሩ እያለ የሚያስታምም ከሆነ ወዴትም እልፍ ብሎ መሥራት አይጀምርም ።
• ጨለማውን አልፌ ሄጄ ዕቃዬን ከጎረቤት ቤት ላምጣና ሥራዬን ልጀምር ወይስ ይቅር?
• የገለጽኩትን መጽሐፍ ማለቢያ አላደረግሁለትም ነበርና አሁን አላስታውሰውም ሌላ ጊዜ አነበዋለሁ።
• ርቀቱም አይቻልም።
• እኔ ወንድ አይደለሁም፤ ከሰው ቤት ገብቼ አሠራሩን አሳዩኝ ለማለት ይቸግረኛል።
• ሰውየው ከሰው የሚያግባባ ባህሪ የለውም፤ አሉ…ወዘተ ብሎ ከሚሄዱበት ስፍራ መቅረት ለሥራው ራስን ዝግጁ አለማድረግና በራስ ፍርሃት መታጠር ነው።
• በአጠቃላይ እንዴት እንደማይሠራ ማሰብ የመሥራት ትልቁ ጠላት መሆኑን አትርሱ።
ስለዚህ ሥራን ላለመሥራት የሚቀርቡትን ደካማ እና ጎታች ሐሳቦችህን ስታስብ የሚከተሉትን ነገሮች አብረህ አስብ።
• ባለመሥራትህ የሚያስከፍልህን ዋጋ አስብ።
• ለዛሬ ተገቢ ነው፤ ብለህ የምታስበውን ነገር ለመሥራት ተነስ።
• ደካማ ነኝ ብለህ በምታስብባቸው የባህሪ ጎንህ ሌላን ሰው በመወከል ሥራውን ለማከናወን ሞክር።
ስለዚህ ሥራህን ለመሥራት በተዘጋጀ ልብና በቆረጠ መልክ ራስህን አርቅ (“ር”ን ጠበቅ አድርጋችሁ አንብቡ) እንጂ፤ ሰበባ ሰበብ በመስጠት ከዓላማህ ራስን አታስተጓጉል። ምንም ያህል ራስህን በሥርዓት ያስገዛህ አድርገህ ብታስብም ደካማ ጎኖችህን ተቀብለህ በሚገባ ለጥቅምህ አውላቸው እንጂ፤ የማደናቀፊያ ቋሚ እንቅፋቶች አድርገህ እሽሩሩ አትበላቸው፤ አታባብላቸው። ያኔም የዓላማ አስፈፃሚነት ዋነኛውን ሚና ተጫውተሃል ማለት ይቻላል።
4ኛ/ እንቅፋቶችህ እንዲያደናቅፉህ ፈቃድ አትስጣቸው።
ስኬታማ ሰዎች፣ ዋጋ በሚሰጧቸው ዋነኛ ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርገው ሲሠሩ ደካሞች ግን በየትናንሹ ነገር ተጠልፈው ይቀራሉ። እየተራመድክ እያለ ከጎን የሚወነጨፉ ፍላፃዎችን ዝቅ ብለህ በማሳለፍ ትሄዳለህ እንጂ፤ ለተወረወረው ጦር ሁሉ መልስ መስጠት ስትጀምር ዋነኛውን ዓላማህን ትስታለህ፤ እንቅፋቶቹ ጥፍርህን እንዲነቅሉትና መራመድ እንዳትችል አቅም ታቀብላቸዋለህ።
አየህ፣ እጅግ አስፈላጊ በሆኑት ሥራዎችህ ላይ ትኩረት ስትሰጥ በሁካታ ሊጠልፉህ ለሚያስቡና፤ ትናንሽ ሥራዎች ሊሰጡህ ለሚችሉ ሰዎችና አጋጣሚዎች ዕድል በመንፈግ ጥለሐቸው ትወጣለህ። ምክንያቱም በቀኑ መጨረሻ የምትፈልገውን አዝመራ ያጨድከው አንተ መሆንህን ትረዳለህና። በተቃራኒው ግን በየትናንሹ ጉዳይ ስትዋጥ፣ ዋነኛው ዓላማ ይረሳና በቀኑ መጨረሻ ባዶ እጅህን ወደ ኦና ቤትህ ትገባለህ፤ ያኔም መነጫነጭ ትጀምራለህ፤ ክስ ታበዛለህ፤ ጣትህን ሌሎች ላይና ወዳጆችህ ላይ ሁሉ ትቀስራለህ። በአጭሩ በእንቅፋቶቹ ትወረሳለህ፤ ስለዚህ እንቅፋቶችህን እንዳሉ አውቀህ ግን በብልሃት በማለፍ ወደኣላማህ መገስገስን አትርሳ።
እና በሳምንቱ ማለቂያ ላይ ያመጣኋቸው ለውጦች ምንድናቸው? ያለፍኳቸው እንቅ ፋቶችስ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ያኔም የሥራህን ልክነትና ስህተት ትገነዘባለህ። ሥራህን የዋጠውን እንቅፋትና ውጠህ የተወጣሃቸውን እንቅፋቶች ታመዛዝናለህ። እርግጠኛ ነኝ፤ ለማይገቡ ጥቃቅን ነገሮች ዕድል ፋንታ ከመስጠት ይልቅ ዋነኛውን ጉዳይ አስቀድመህ ሠርተሃል።
5ኛ/ በጊዜ አጠቃቀምህ ጠንቃቃ ሁን።
በአላማው ላይ ጥንቁቅ የሆነ ሰው ለጊዜ ተገቢውን ጥንቃቄ እንደሚወስድ አልጠራጠርም። ጊዜ ከተጠቀሙበት ትልቅ ሀብት ነው። ፈረንጆች ጊዜን “ወርቅ” ሲሉ፣ የእኛ ሐመሮች “ጊዜ ህይወት” ነው፤ ይላሉ። እነርሱ ከከብቶቻቸው ጋር የተቆራኘ ነገር በጣም ያሳስባቸዋልና፤ የትኛዋ ላም መቼ ተጠቅታ መቼ እንደምታረግዝና እንደምትወልድ ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ለከብቶቻቸው ግጦሽ ሲወጡ በየትኛው ስፍራ መቼ፣ ውሃ፣ ለምለም መኖ፣ በምን ርቀት እንደሚገኝ ጠንቅቀው ይገነዘባሉና። ቀጠሮ ሰጥተውህ ስትዘገይ “ምራቃቸውን ጢቅ ብለው” ነው፤ ጥለውህ የሚሄዱት (ምራቁ የሚደገፍ ባይሆንም) እነርሱ፣ ቁምነገራሞችም ስለሆኑ ሰው ጊዜን በቁም ነገር እንዲያስብበት ይፈልጋሉ።
ጊዜህን በሚገባ መጠቀም ካሻህ የሚከተሉትን መሰረታዊ ነገሮች እንድታስብ አሳስብሃለሁ።
• በዚህ ጊዜ ውስጥ ይህን ሥራ አጠናቅቀዋለሁ ብለህ ወስን። አንድን ሥራ ለመሥራት ስትነሳ የጊዜ ቀመር ይኑርህ ። በጊዜህ ላይ ለመወሰን ካንተ የተሻለ ሰው ላንተ የለም።
ለምሳሌ ያህል የሬዲዮ ጋዜጠኛ ከሆንክ፣ የተዘጋጀሁበትን ርዕሰ ጉዳይ ከቃለ-መጠይቅ ተደራጊው ጋር፡-
• በሁለት ሰዓት ውስጥ ጨርሳለሁ፤ ብለህ ወስን።
• በአንድ ሰዓት ውስጥ ኤዲት አደርገዋለሁ።
• መግቢያና መውጫ መሸጋገሪያ በ30 ደቂቃ ውስጥ እጨርስለታለሁ።
• በሚቀጥለው አንድ ሰዓት ውስጥ አየር ላይ አቀርበዋለሁ፤ ወይም በተገቢው ሰዓት ለኤዲተሩ አቀርበዋለሁ።
• በግማሽ ሰዓት ውስጥ ግብረ መልስ ተቀብዬ አርመዋለሁ፤
• ለፕሮግራም አቅራቢ አየር ላይ ከግማሽ ሰዓት በፊት እንዲያውል አስረክበዋለሁ፤ ብለህ ወስን ።
ለሁሉም ሥራ ፍፃሜ ቀንና ሰዓት ማስቀመጥ ተገቢ ነው። በቀኑ መጨረሻ እና በሳምንቱ ማለቂያ ላይ የሥራህን ውጤት መገምገም ያንተና ያንተ ፋንታ እንጂ የማንም አይደለም። ታዲያም የምትገመግመው፤ ሥራህን እንጂ ሌላ አይደለም፤ የዕቅድህን ያህል ከተራመድክ መልካም ነው፤ ካልሆነ ግን የተግዳሮቶቹን ምንነት ካወክ በኋላ መሻገሪያ በማበጀት ለሚቀጥለው ሳምንት በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ሥራህን በብቃት ለማከናወን ወስን። የፍፃሜ ቀን ያልተቋጨለት ሥራ ማለቂያው ቆሞ አይጠብቅም፤ ተኝቶ ይቀራል እንጂ።
ተገቢ የሥራ አፈፃፀም ግምትና ተጨባጭ ጉጉት ሥራን ወደፊት ለማራመድ ማግኔታዊ ኃይል አላቸው። አንድ፣ በሥራ ሥነ-ሥርዓት ለሚያምን ሰው እነዚህ ሁለት ነገሮች አስፈላጊ ናቸው።
6ኛ/ ጨክነህ ሥራህን ቀጥል።
አንዳንዴ ሥራህ ላይ ምላጭ የሚያስውጥ አሳዛኝና ምቾት የማይሰጡ ነገሮች ሊገጥሙህ ይችላል፤ ይሁንና ሐሞትህን ኮስተር አድርገህ ጨክነህ ቀጥል እንጂ፤ ለፈተናህ እጅህን አትስጥ። የአንድ አሸናፊ ሰው ማንነት የሚለካው በሥራው ላይ የሚያጋጥሙትን አካላዊና አዕምሯዊ ችግሮች ተጋፍጦና አሸንፎ ለመውጣት በሚያሳየው ብቃት ነው።
በየንጋቱ ስትነሳ ዛሬ ልሠራ የሚገባኝን ነገር ሳልሠራው አላድርም፤ በል። ቃልህንም አክብር። በማንም አታሳብብ፤ ሰበቦችህን ሁሉ ጠርገህ ጥለህ በቀኑ መጨረሻ በተሠራው ሥራ ደስ ይበልህ፤ እንጂ በቁጥር አንድና ሁለት የጠቀስናቸው ምክንያቶችን ምክንያትህ ለማድረግ አታስብ። ባትሠራ የወደከው አንተ መሆንህን አትርሳ፤ ብትሠራ ያሸነፍከው ያንተን ድካም መሆኑንም አስተውል። ራስህን ካልገዛህ ሥራህንና ሃላፊነትህን መግዛት አትችልም ።
ዕድሜህ በጨመረ ቁጥር ህልምህ እንደሚያድግና ልታሳካው የምትችለው ነገር እንደሚጨምር አትዘንጋ፤ በቆየህም ቁጥር ሳትሠራ የቆየሃቸው ነገሮች እየተወሳሰቡ እንጂ፤ እየቀለሉ ስለማይመጡ ሁሉንም በጊዜው ውስጥ ሥራው። መቶ ዓመት እንኳን ብትኖር ዘመኑ የሚጠይቅህ ሥራ እንዳለ አትርሣ።
7ኛ/ ፍቅር ይኑርህ ።
ለምትሠራው ሥራ ከሁሉም በላይ ፍቅር ይኑርህ። ፍቅርህን የምታሳየው ሁሉን ነገርህን በሥራህ ላይ በማሳየት ነው፤ ፍቅርህን የምትገልፀው እንጂ፤ ሥራዬን እወደዋለሁ እያሉ በመናገር አይደለም። መናገር መልካም ቢሆንም ፍቅር በተግባር የሚገለፅ መሆኑን መዘንጋት አይገባም ።
ይህ ለሥራ ያለን ፍቅር ደግሞ በተግባር ለሌሎቹ የሥራ ባልደረቦቻችን የሚገለፅ መሆን ነው ያለበት። ኣላማን ወይም ግብን ለመምታት የዓላማ ማስፈፀሚያ የሆኑ ሰዎችን ችላ ማለት የለብንም። አምራቹን በሬ አፉን አስረን፣ ምርቱን ብቻ ለመሰብሰብ መነሳት የለብንም። እንዲያውም ዋነኛውን ሥራ ለማስፈፀም ዋነኛው የሰው ሃይላችን መሆኑን አንዘንጋ። ለእነርሱ የሚኖረን ፍቅር ምትክ እንደሌለው ማወቅ አለብን።
ዓመት በዓላትን ምክንያት በማድረግ መጠነኛ ሽልማት አድርግላቸው። ድንገተኛ ጉብኝት በቤታቸው አድርግ፤ ያኔም በተግባር አለኝታነትህን ይገነዘባሉ እንጂ፣ የምታጣው ነገር አይኖርም። በቸርነት የደኸየ፣ በፍቅርም የባከነ ንብረትም ዕድሜም የለም።
በሌላ በኩል፣ የቀኑን የ24 ሰዓት ሥራ ለመሥራትና ለመከወን ተዘጋጅ እንጂ፣ ለ25ኛው ሰዓት ሥራህን አታበድር። ያንዱ ሰዓት ብድር የሌላን ሰዓት ብድር ያቆያል እንጂ አይከፍለውም። ስለዚህ በሰዓቱ ሥራበት፤ ጥርስህን ነክሰህ ቆይበት ፤ ሥራህን በፍቅር ስትሠራው ህመምህን አታዳምጠውም፤ በውዴታ ስታከናውነው ፈተናውን አታከብደውም። በቀን ውስጥ ተጨማሪ ሰዓት የለህም።
ግለ ዲሲፕሊን ወይም ሥነ-ሥርዓት ማለት ጊዜና ዋነኛው ሥራ ከሠሪው ጋር የተገናኙበት ነጥብ (ምስማክ) ማለት ነው። እና በሚገባ ተጠቀምበት፤ ያኔም የጊዜህና የሥራህ ጌታ ነህ ማለት ነው። ማንም ሰው ታዲያ፣ ያኔ “ማነህ ባለሥርዓት” ብሎ አይጠይቅህም፤ “በሕግ አምላክ!” ብሎ ሊፋረድህ አይነሳም። ዋነኛው ሥራ በሥርዓት በታነፀ ሰው አማካይነት፣ በተገቢው ጊዜ ተጠናቋልና።
ግለ-ሥርዓትህን፣ (ዲሲፕሊን) ለማዳበር ሀብታም መሆን አይጠበቅብህም። በሀብታም ቤተሰብ ውስጥም ማደግ ምክንያት አይሆንም። ራስን ለሥራው ማዘጋጀት እንጂ። ከመሰናበቴ በፊት በዓለም ላይ እጅግ ስመ-ጥር በነበሩት በዴቪድ ሮክፌለር የአንድ ሰሞን ታሪክ ልደምድምላችሁ። (ሰኔ፣ 1915 ተወልዶ ሚያዝያ፣ 2017 ያረፈው ታዋቂ ቢሊየነር ነው) እና አንድ ጊዜ ፣ አንድ ወዳጅ ቢጤ ሰው ይመጣና፤ አንተን የመሰለ ጠንቃቃ ሰው ከየት ተነስተህ የት እንደደረስክ ሊገባው፣ ያልቻለው ጎረምሳው ልጅህ ገንዘብህን በየምሽት ዳንኪራው ቤት እንደጉድ እየዘራው ነው፤ ሲል ነገረው። አየህ አለው፤ ሮክፌለር… አየህ፣ እርሱ የሀብታሙ ዴቪድ ሮክፌለር ልጅ ሲሆን እኔ የደሀው ዴቪድ ልጅ ነበርኩ። ከምን እንደተነሳሁ የማውቅና የገንዘብ ማግኛ ዘዴዎችን ብቻ በመከተል ዘመኔን የጨረስኩ ሲሆን እርሱ ደግሞ፣ ሀብት ላይ ነውና የተወለደው፣ የገንዘብ ማጥፊያ መንገዶችን ቢያስብ አትፍረድበት። እርሱ ገንዘብ ላይ ተወለደ፤ እኔ ደግሞ ቤሳ ቤስቲን ከሌለው ገበሬው አባቴ ጎጆ ውስጥ ተወለድኩ፤ ልዩነታችን እርሱ ነው፤ አለው ይባላል። ድህንትን እንደማይወለዱት ሁሉ ጠንቃቃነትንም በልደት አያገኙትም፤ በኑሮ ውጣ ውረድ ውስጥ እንጂ።
ግለ-ዲሲፕሊን የህይወት ግብን ጠንቅቆ ከማወቅ የሚመነጭ እንጂ ከሀብታምም ከደሀም ቤተሰብ በተወለዱና በከተሜነት እንዲሁም በምክር ብዛት አይገኝም። ከምክሩ በላይና ከፈታኙ ስሜት በላይ በመቆም የሚገኝ እውነት እንጂ፤ ለጊዜ ጠንቃቃ፣ ለሥራ ጠንቃቃ፣ ለአነጋገር ጠንቃቃ፣ ለአኗኗር ጠንቃቃ፣ (ዲሲፕሊን) ያለው ሰው መሆን ለራስ ድንቅ ሰብእና መገንባት ነው። በመጨረሻም፣ ጣሊያኖች፣ ሲገናኙም ሆነ ሲለያዩ “ቻው!” እንደሚሉት ሁሉ፣ ለዚህ ሳምንት ቻው፣ ብዬ ተሰናበትኳችሁ!!
መልካም ሳምንት እስከ ሳምንት!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 25/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ