-240 ሺህ የሚሆኑ ባለቤት አልባ ውሾች ይገኛሉ
አዲስ አበባ፡- በአዲስ አበባ ከተማ በዓመት በአማካይ 10 ሺ 800 ሰዎች በእብድ ውሻ በሽታ እንደሚጠቁና ከ20 በላይ ሰዎችም በበሽታው ሕይወታቸውን እንደሚያጡ የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡ በከተማዋ በአጠቃላይ ከ300ሺህ በላይ ውሾች እንደሚገኙና ከነዚህም ውስጥ 80 ከመቶዎቹ (240 ሺህ) ባለቤት አልባ እንደሆኑም ተጠቁሟል፡፡
በኢንስቲትዩቱ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ባዬ አሸናፊ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በእብድ ውሻ በሽታ ምክንያት በአማካይ በቀን ከ30 ሰዎች በላይ ለህክምና እንደሚሄዱ ጠቁመው፤ በዓመት ደግሞ 10 ሺህ 800 ሰዎች ከአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች በ ‹‹ሪፈር›› መጥተው ሕክምናውን እንደሚወስዱ ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ሳቢያም በዓመት በአማካይ 20 ሰዎች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ገልጸዋል፡፡
የእብድ ውሻ በሽታ በቫይረስ አማካይነት የሚከሰት ተላላፊ በሽታ ሲሆን ሰውን ጨምሮ ማንኛውንም ደመ ሞቃት እንስሳ እንደሚያጠቃ ዶክተር ባዬ ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ባለቤት አልባና ተቆጣጣሪ የሌላቸው ውሾች በከተሞች አካባቢ በብዛት መኖራቸውን ተከትሎ በሽታው እየተስፋፋ መምጣቱን የጠቆሙት ዶክተር ባዬ ፤ በሽታውን ለመከላከል የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ትኩረት ሊሰጡት እንሚገባ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአርሶ አደርና ግብርና ልማት ኮሚሽነር አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ ከአምስት ዓመት በፊት በተደረጉ የዳሰሳ ጥናቶች መሰረት በከተማው ከ 300 ሺህ በላይ ውሻዎች እንዳሉ የሚገመት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 80 በመቶ (240 ሺህ) የሚሆኑት ባለቤት እንደሌላቸው ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ግንቦት 20 ጤና ጣቢያ ሜዲካል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተስፋዬ ፉጃጋ እንደተናገሩት፤ በቀን ከሁለት እስከ አምስት ሰዎች፣ በወር ደግሞ ዝቅተኛው 60 ከፍተኛው 130 ሰዎች በታመሙ ውሻዎች ተነክሰው ለሕክምና ይመጣሉ፡፡ ጤና ጣቢያው ‹‹ሪፈር›› ከሚልካቸው ታካሚዎች መካከልም የውሻ በሽታ ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዝ ጠቅሰው፤ ጥቃቱ እና ስርጭቱ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለወረዳውና ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
የጤና ጣቢያው ዳይሬክተር እንዳብራሩት፤ በተለምዶ አሜሪካን ግቢ በሚባለው አካባቢ ኗሪዎች በመልሶ ማልማት ምክንያት ቀያቸውን ሲለቁ ውሻዎች አብረው ባለመሄዳቸው እና የቆሻሻ ክምሮች ከመብዛታቸው የተነሳ የውሻ መንጋ አካባቢውን ተቆጣጥሮታል፡፡ በዚህ ምክንያት የሕክምና ባለሙያዎች ጭምር ወደ አካባቢው ሲገቡና ሲወጡ ተነክሰዋል፡፡
የውሻዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን ለሚመለከተው አካል በተደጋጋሚ አሳውቀናል የሚሉት አቶ ተስፋዬ ፤ ነገር ግን እስካሁን ምንም ምላሽ አልተገኘም ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም በአካባቢው ሸራ ወጥረው የሚኖሩ በርካታ ቁጥር ያላቸው የማህበረሰብ ክፍሎች በከፍተኛ ስጋት ላይ መውደቃቸውን ተናግረዋል፡፡
በሽታው የሚተላለፈው 99 በመቶ በንክሻ ሲሆን ከታማሚው እንስሳት የሚወጡ ፈሳሾች ከቁስል ጋር በቀላሉ ንክኪ በሚፈጥሩበት ወቅት እና በስስ የቆዳ ክፍሎች ላይ ፈሳሹ አርፎ በቀላሉ ወደ ሰውነት በሚገባበት ጊዜ በሽታው እንደሚተላለፍ ዶክተር ባዬ ተናግረዋል፡፡
በበሽታ እንደተያዙ የሚጠረጠሩትንና ባለቤት አልባ ውሻዎችን የማስወገድ ስልጣን በአዋጅ የተሰጠው የከተማ አስተዳደሩ የአርሶ አደርና ግብርና ልማት ኮሚሽን ቢሆንም ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ መድሃኒቱ ለጤና አደገኛ መሆኑ በመረጋገጡ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ በመከልከሉ ምክንያት ይሄን ማድረግ አለመቻላቸውን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነር አሰግደው እንደገለፁት፤ የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ መኪና ጥበቃ ላይ የተሰማሩትን፣ የትላልቅ ሕንጻዎች የጥበቃ ሰራተኞችን እና ለበሽታው በጣም ተጋላጭ ይሆናሉ የተባሉትን የተለዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ ተሰርቷል፡፡ ይህ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ከግብርና ሚኒስቴርና ከሌሎች የከተማ አስተዳደሩ መስሪያ ቤቶች ጋር በመተባበር ከ300 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ የክትባት መድኃኒት ተገዝቶ ክትባቱ በዘመቻ እየተካሄደ ነው፡፡ በታህሳስ ወር ብቻ 20 ሺህ ባለቤት አልባ ውሻዎች መከተባቸውን ገልጸው፣ ባለቤት ያላቸውንም ቤት ለቤት የሚከተቡ ሲሆን እስከ ጥር 30 ድረስ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር የውሻ በሽታ ምርመራ ማዕከል ጉለሌ በተለምዶ አዲሱ ገበያ አካባቢ ተገንብቶ ያለቀ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በማይበልጥ ጊዜ ውስጥ እንደሚመረቅ ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡ የከተማው ነዋሪ ሕዝብ የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓቱን በማዘመንና አካባቢውን ንጹህ በማድረግ ከበሽታው ራሱንና ቤተሰቡን እንዲጠብቅ ኮሚሽነሩ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ሙሐመድ ሁሴን