አዲስ አበባ፡- ወጣቶች በምርጫ ወቅቶች ለተወዳዳሪዎች ድምፃቸውን እንጂ ህይወታቸውን መገበር እንደማይገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለፁ።
በአዲስ አበባ ከተማ በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ዙሪያ “በህብር ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል ሲካሄዱ የነበሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች የማጠቃለያ መርሐ ግብር ትናንት በሚሊኒየም አዳራሽ ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ወጣቶች ህልማቸውን ሊነጥቁ ከተዘጋጁ ጉዳዮች በመራቅ የብልጽግና ጎዳናን መከተል ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን፤ ሰውን አጋድሎ እና አጣልቶ ሥልጣን ለመያዝ ያለመ ካለ አስተሳሰቡ ራሱ የቆሸሸ ነውና ለኢትዮጵያ አይጠቅማትም፤ ስለዚህ ወጣቶች መንቃት ይኖርባቸዋል ብለዋል።
‹በሚከሰቱ ግጭቶች ወጣቶች እየተጎዱ ነው፤ ወጣቱን ተገፋፍቶ ወደአልተፈለገ ተግባር የሚያስገቡ ሃይሎች ሲሞቱ አይስተዋልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ወጣት ስለሆናችሁ ለማናችንም ቢሆን ካርዳችሁን እንጂ ህይወታችሁን አትስጡ ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ፥ “የብልጽግና አስተሳሰብን እና አሠራርን በቀጣይ 50 ዓመታት ማሸነፍ ከባድ ነው፤ ማንም እኔን ቢያሸንፍ ከብልጽግና ሐሳብ ወዲያ ግን ኢትዮጵያን ለወራትም ቢሆን ማስተዳድር ይከብደዋል›› ብለዋል።
“ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራው ብልጽግናን በመክሰስ ሳይሆን፤ ከብልጽግና በመማር እና የብልጽግና እሳቤዎችን በማሻሻል ብቻ ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ፤ ወጣቶች ድህነትን መጠየፍ ብቻ ሳይሆን በመሥራት እና ለብልጽግና በመትጋት ለውጥ ማምጣት እንደሚገባቸውም መክረዋል።
“ብልጽግና ለትውልድ እንጂ ለምርጫ አይሠራም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ “የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብልጽግናን ከወደዳችሁ በድምፃችሁ ደግፉን፣ ከጠላችሁን ደግሞ በድምፃችሁ ቅጡን፤ ነገር ግን በምርጫ ምክንያት የዜጎች ሕይወት ማለፍ የለበትም” ሲሉ ተናግረዋል።
ብሔራዊ ፌደራላዊ ሥርዓት ከመገንባት አኳያ ውህደቱ ሁሉን አካታች መሆኑን እና የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ይረዳ ዘንድ አስፈላጊ መሆኑን የተናገሩት ወጣቶች ደግሞ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጻፏቸው መጽሐፎች እና በመደመር ፍልስፍና ውስጥ ለወጣቶች ትኩረት በመስጠታቸው፣ አዲስ አበባን እንድትለማ ላደረጉት ጥረት እና የዓለም የሰላም ኖቤል ተሸላሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ የሚገልጽ ስጦታ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አበርክተዋል።
በመድረኩ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤ የብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ጨምሮ 12 ሺህ የሚደርሱ የከተማዋ ወጣቶችም ታድመዋል::
“በህብር ወደ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ ወጣቶች፣ ሴቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራምና ሕገ ደንብ ዙሪያ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት እና የምክክር መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸው ይታወሳል።
በሌላ ዜና ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ተወዳዳሪ አገር በቀል የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪ ቃል በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ በተካሄደው አገር አቀፍ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ንቅናቄ ላይ ተገኝተው በአደረጉት ንግግር፤ ‘‘70 እና 80 ፒካፕ አለኝ እያለ የሚቆጥር ኮንትራክተር የኢትዮጵያን ብልጽግና ሊያረጋግጥ አይችልም’’ ብለዋል፡፡ በቀጣይ 10 ዓመታት በኢትዮጵያ ዕድገት ውስጥ የግንባታ ዘርፉን ሚና ለማሳደግ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩ ኩባንያዎችም ከስርቆት በፀዳ መልኩና በጥራት ለሀገር ዕድገት እንዲሠሩም ዶክተር አቢይ አህመድ ጥሪያቸውን አቅርበዋል፡፡ዘገባውን ለማዘጋጀት ኢቢሲን እና ኤፍቢሲን በዋቢነት ተጠቅመናል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ድልነሳ ምንውየለት