አዲስ አበባ፡- ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሂደት በተቀመጠላቸው ጊዜና በጀት ባለመጠናቀቃቸው ምክንያት በአማካይ እስከ 107 በመቶ የደረሰ የወጪ ጭማሪ ማስከተላቸው ተገለፀ። የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረሙስና ኮሚሽን በተመረጡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ ያደረገውን የአፈፃፀም ግምገማ ጥናት ለባለድርሻዎች ትናንት አቅርቧል።
በግምገማው ውጤት ውይይት ወቅት የፌዴራል ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የኮሚሽነሩ ልዩ አማካሪ አቶ መለሰ ተገኘ እንደተናገሩት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ዘርፉ በተነፃፃሪነት ከፍተኛ በጀት የሚመደብለት ሲሆን፤ መንግሥታት ለዘርፉ ከሚመድቡት በጀት ውስጥ ከ15 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው በሙስና ሊባክን እንደሚችል መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ደግሞ ዘርፉ ለሙስና ተጋላጭ መሆኑን ያመለክታል። የኢትዮጵያ መንግሥትም ከዓመታዊ በጀቱ ውስጥ ለግዢው ዘርፍ ከሚመድበው 60 በመቶ ውስጥ 70 በመቶው ለኮንስትራክሽን ዘርፉ የሚወጣ ነው።
ይሄን መነሻ በማድረግም ኮሚሽኑ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የስኳር ኮርፖሬሽን፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እያስገነቧቸው ባሏቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የፕሮጀክት አፈፃፀም ግምገማ ጥናት ያካሄደ ሲሆን፤ በዚህም ፕሮጀክቶች በጊዜም ሆነ በገንዘብ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየታቸው ተስተውሏል። ለአብነት ኮስት ኢትዮጵያ ያከናወነው ጥናት እንዳመለከተው አጠቃላይ የግንባታ ዘርፉ ያለው አማካይ ዋጋ ጭማሪ 107 በመቶ ይደርሳል።
የኮሚሽኑን የግምገማ ጥናት ያቀረቡት አቶ ኪዳነ ምህረት፣ አቶ ሰይፈዲን ኪያር እና አቶ ወንድይራድ ሰይፉ በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ጥናቱ በ17 ግዙፍ ፕሮጀክቶች ላይ የተከናወነ ሲሆን፤ ከተጠናቀቁት 12 የግምገማ ጥናቶች ውስጥ አምስቱ (ያዩ ዩሪያ ማዳበሪያ ኮምፕሌክስ ግንባታ፣ ጋሸና-ላሊበላ-ሰቆጣ መንገድ ግንባታ፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የማስተማሪያ ሆስፒታል ግንባታ፣ የአራራት ሆቴል ኮተቤ ኮሌጅ መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት እና የሐረማያ ቲቺንግ ሆስፒታል) እንዲቀርቡ ሆኗል።
በግምገማ ጥናቱ መለየት እንደተቻለውም ፕሮጀክቶች በተለያየ ምክንያት በተቀመጠላቸው ጊዜና በጀት እየተጠናቀቁ ባለመሆናቸው አንድም ለህዝቡ አገልግሎት እንዳይሰጡ ሆኗል፤ ሁለተኛም መንግሥትን ላልተገባ ወጪ እየዳረጉት፣ ለሙስናና ለብልሹ አሠራርም በር እየከፈቱ ይገኛል።
አቅራቢዎቹ በግምገማ ጥናቱ ካቀረቧቸው መካከል ጋሸና-ላሊበላ-ሰቆጣ መንገድ ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን፤ ይህ ፕሮጀክት ከ2 ነጥብ 04 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚከናወን የ99 ነጥብ 75 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ነው። ለፕሮጀክቱ አራት ጊዜ የጨረታ ማስተካከያ የተደረገ በመሆኑ ለሙስናና ብልሹ በር የሚከፍትና በተረታ ተወዳዳሪዎች ላይ ተጽዕኖ ያሳደረ ሆኖ ታይቷል። ግልፅ የመወዳደሪያ መስፈርትም አልነበረውም። የውጭ ምንዛሬ ብክነት እንዲከሰት አድርጓል። በዲዛይን ለውጥ ምክንያትም ወደ 49 ሚሊየን ብር ለኮንትራክተሩ እንዲከፈል ሆኗል።
በተመሳሳይ 875 ሚሊየን 77 ሺ 561 ብር ሰኔ 2006 ዓ.ም ውል ተገብቶለት በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ይጠበቅ የነበረው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ቲቺንግ ሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ፕሮጀክት፤ ዛሬም ድረስ ከወሰን ማስከበር፣ ተደጋጋሚ የዲዛይን ለውጥና ሌሎች ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ እስከ ጥር 2011 ዓ.ም ድረስ አፈፃፀሙ ከ61 በመቶ መዝለል ባለመቻሉ ተጨማሪ 84 ሚሊየን ብር እንዲከፈል አድርጓል።
አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ወጪው ወደ አንድ ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር እንዲደርስ አድርጎታል። ከዚህ ባለፈ የፕሮጀክቱ በጀት በጨረታ ኮሚቴ የቀረበውን የ875 ሚሊየን ሰባት ሺህ 561 ብር ዋጋ በኮንትራት ፊርማ ወቅት ባልታወቀ ምክንያት 70 ሺ ብር በመጨመር 875 ሚሊየን 77 ሺ 561 ብር ተቀይሯል።
እንደ ጥናት አቅራቢዎቹ ገለፃ፤ በጥናቱ እንደተለየው በጊዜም በበጀትም ያልተገባ ጭማሪ መስተዋሉ ሲሆን፤ ይሄም ለሌሎች ፕሮጀክቶች መዋል የሚገባውን ፋይናንስ በመውሰድም በመንግሥት ላይም ጫና እያሳደሩ ይገኛል።
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ በህዝብ ሀብት የሚከናወኑ እንደመሆናቸው በአግባቡ ተፈትሸው ውል ሊታደስላቸውና በአግባቡ ተገንብተው እንዲጠናቀቁ የሚያስችል በጥናት ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ሊሰጣቸውና የህዝብን ሀብት ከብክነት መታደግ፤ ፕሮጀክቶቹም ወደ አገልግሎት እንዲገቡ ማድረግ ይገባል።
ቀጣይ የሚከናወኑ ታላላቅ ፕሮጀክቶችም አጠቃላይ ሂደታቸው ለህዝቡ ግልፅ የሚሆንበት ዕድል ሊፈጠር፤ ውድድርን መሰረት ያደረገ የግንባታ ጨረታን መከተል፤ ተጠያቂነትን ማስፈን፤ ዋጋ፣ ጊዜና ጥራትን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎች እንዲከናወኑ ማስቻል ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ወንድወሰን ሽመልስ