ወቅቱ የበዓላት ሰሞን ነው። የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ጭምር በድንኳን ጎጆዎችና በሐበሻ አልባሳት ደምቀዋል። የገናና የጥምቀት በዓላት መጣሁ መጣሁ ማለት ቀድመው የሚያበስሩ ይመስላሉ። ነፍሳችሁ በሐሴት ይሞላል። የማህበረሰባችን የደስታ ፍልቅልቅ ስሜት ሁሌም ሊያዩት ይናፍቃል፤ ያጓጓልም። ምነው ሁሌም በዓል በሆነ ያሰኛል። በዚህ ድባብ ውስጥ ሆነን ሽሮ ሜዳ ተገኘን።
እኛም በዚሁ ስፍራ ተገኝተን በጥበብ አልባሳት የተንቆጠቆጡት የባህል ሱቆች የባህሉን ድባብ ከኢትዮጵያዊ ወግና ባህል ጋር አዋህደው የግብይት ሥርዓቱን እንዴት እያስኬዱት እንደሆነ፣ የሚስተዋለውን የገበያና የሸማች አቅም ሁኔታ እንዲሁም የባህል አልባሳቱን እየጎበኘን ነው።
“ከአምስት ዓመት በፊት ጀምሮ ጥምቀት ሲደርስ ጥበብ እገዛለሁ። በማንኛውም ጊዜ አስቤበት መግዛት ትዝ ብሎኝ አያውቅም። ምናልባትም በልጅነቴ እናቴ ልብስ የምትገዛልኝ ሁሌም ለጥምቀት እንደነበረ ትዝ ይለኛል” ያሉት በሽሮ ሜዳ የባህል አልባሳት መሸጫዎች በሸመታ ላይ ያገኘናቸው ወይዘሮ ኤልሳቤጥ አለሙ ናቸው።
ወይዘሮ ኤልሳቤጥ እንደሚሉት፤ በየዓመቱ የገበያው ሁኔታ ብቻ ሳይሆን የዲዛይኑም ሁኔታ ከሚጠበቀው በላይ ይለያያል። የሚገዙትን የጥበብ ቀሚስ አይነት ከቤታቸው ወስነው መጥተው ገዝተው አያውቁም። እዚያው መርጠው ቀልባቸው የወደደውን ነው የሚገዙት።
አምና የገዙት የአበሻ ቀሚስ ዋጋው 4800 ብር ሲሆን ዘንድሮ ደግሞ 5300 ብር ነው የገዙት። ‹‹አውጥተው እስኪ እየው፣ ምርጥ ነው፤ እጃቸውን ክፉ አይንካው›› ሲሉ መርቀዋል። ‹‹ካየኋቸው ብዙ የጥበብ ሱቆች ውስጥ ዋጋቸው ብዙም የሚራራቅ አልገጠመኝም። ግን እኮ ሰው ብዙ አይለብስም። የአበሻ የጥበብ ቀሚስ ከሚለብሰው የ‹ቻይና ሱሪ የሚለብሰው በዝቷል›› ይላሉ ወይዘሮ ኤልሳቤጥ።
‹‹በደመቁት የሐበሻ ቀሚሶች መካከል ተገኝቶ የማይደምቅ የለም›› የሚለው ‹‹አበበና ጓደኞቹ የባህል አልባሳት መሸጫ› ውስጥ በመሸጥ ላይ ያገኘነው አቶ ባህሩ ቀለመወርቅ ነው። አቶ ባህሩ እንደሚለው፤ በበዓላት ሰሞን የባህል አልባሳት መጠነኛ ጭማሪ ማሳየታቸው የተለመደ ነው።
ዘንድሮም እስከ ሁለት ሽህ የሚደርሱ ጭማሪዎች በነባር የጥበብ ቀሚስ ዲዛይኖች ላይ የሚስተዋል ሲሆን ካለፉት ዓመታት አንፃር ብዙም አልጨመረም። ጤፍ የጨመረውን ያህል ግማሽ ጭማሪ የሐበሻ ልብሶች ላይ አለመታየቱን በንፅፅር የሚናገረው አቶ ባህሩ፤ በበዓላት ወቅት ብዙ አዳዲስ ዲዛይኖች ስለሚወጡ የእነሱ ዋጋ በጣም ከፍተኛው እስከ 30 ሺህ ብር እንደሚደርስ ተናግሯል። በማንኛውም ጊዜ እስከ አስራ አምስት ሺህ ብር ድረስ የሚገዙ ኢትዮጵያውያን አሉ።
ነገር ግን ሰው የጥበብ ቀሚስንም ሆነ በአጠቃላይ የሐበሻ አልባሳትን የመግዛትም ሆነ የመልበስ ባህሉ አነስተኛ ነው። አሁን አሁን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መነቃቃቶች ይታያሉ። ለምሳሌ ባህላዊ የቡና (የጀበና ቡና) ቤቶች እየተበራከቱ በመምጣታቸው የሐበሻ ቀሚስም በአስተናጋጆች በኩል እየተለመደ ይመስላል። የባህል ኤግዚቢሽንና ባዛሮችም ጥሩ የትውውቅ አጋጣሚዎችን ይፈጥራሉ። ወደዘርፉ የሚገቡ በፈለጉት መንገድ የሐበሻ አልባሳትን የሚያዘጋጁ ወጣት ዲዛይነሮችም መኖራቸውን ወጣት ባህሩ አስረድቷል።
‹‹ኢትዮጵያ የተዘጋጁ የባህል አልባሳት ችርቻሮ›› ሱቅ ውስጥ ደንበኞቿን በማስተናገድ ላይ ያገኘናት ወይዘሮ አለምነሽ ከበደ እንደተናገረችው፤ የባህል አልባሳት ሥራ ወቅታዊ ነው። የማህበረሰቡ የመጠቀም (የመልበስ) ልምድም እንደዚያው ወቅታዊ ነው። ለዚያ ሰሞን ግን አለ የተባለውን ምርጥ ሥራ ይዘን ለመቅረብ ጥረት እናደርጋን። አዳዲስ ፋሽን የሐበሻ ቀሚሶችን ከ20 እስከ 25 ሺህ ብር እና ዝቅተኛው ደግሞ እስከ ሁለት ሺህ ብር ድረስ እንደሚሸጡ ተናግረዋል።
ወይዘሮ አለምነሽ እንደሚሉት የዲዛይኖቹ ብዛት በጣም በርካታ ነው። ሆኖም አዘውትሮ ስለማይለበሱ ሰዎች የሚስባቸውን ይመርጣሉ። የሚወዱት የቀለም ምርጫም አለ። በዋጋ ላይ የሚታዩት ጭማሪዎችም የተለመዱ ናቸው።
በሌላ በኩል እነዚህ አልባሳት የኢትዮጵያዊ መገለጫዎቻችን በመሆናቸው በጋራ ማስተዋወቅ አለብን ይላሉ። መንግሥትም ከዚህ በተሻለ ደረጃ ዘመናዊ የስፌት ማሽኖችን በማቅረብ የጥልፍና የሽመና ባለሙያዎችን አሠራር ማሳደግ ቢችል ዋጋቸው ተመጣጣኝ ይሆናል፤ ባህላችንም ሳይደበዝዝ ይቀጥላል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ሙሐመድ ሁሴን