አዲስ አበባ፡- በ2012 በጀት ዓመት በምግብ ዋስትና ፕሮግራም አማካኝነት በአገሪቱ በተመረጡ 11ከተሞች ከሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የከተማ ግብርና፣ የመጸዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ የደረቅ ቆሻሻን የማንሳት፣ የመንገድና ሌሎች የማህበራዊ ልማት ስራዎች እየተካሄዱ እንደሚገኙ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና አስተባባሪ አቶ ደበበ ባሩድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ11 ከተሞች በምግብ ዋስትና ፕሮግራም አማካኝነት 400ሺ በላይ ሰዎችን በማሳተፍ በሁለት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የተለያዩ የማህበራዊ ልማት ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
ከሚሰሩት በማህበራዊ መሰረተ ልማቶች መካከልም የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች ግንባታ፣ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ጥገና፣ የአቅመ ደካማ ሰዎችን ቤት መጠገን ፣ መንገድና ድልድይ ግንባታዎች እንዲሁም ቆሻሻን የማስወገድ ስራዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል፡፡
ለማህበራዊ ልማት ስራዎቹን ለማፋጠንም 40 መኪናዎች፣ 120 ሞተር ሳይክሎችና 26 የቆሻሻ ማስወገጃ ተሽከርካሪዎች ግዥ በመፈጸም ለክልሎቹ የማሰራጨት ስራ መሰራቱንም አመልክተዋል፡፡
የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከ2011 ዓ.ም በጀት ዓመት በ11 ከተሞች በአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የከተማ ግብርና ልማት፣ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች፣ የመንገዶች፣ የድልድዮች ግንባታዎችና ቆሻሻን የማስወገድ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸው ለአብነትም 15ሺ817 የህዝብ መጸዳጃ ቤቶች መገንባት፣ 201ሺ 041 ቶን ደረቅ ቆሻሻ ከገበያ፣ ከህዝብ መዝናኛና ከቤቶች አካባቢዎች መስወገድና በከተማ ግብርና ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ ማልማት መቻሉ ተናግረዋል፡፡
እንደ አስተባባሪው ገለጻ፤ የካፒታል በጀቱን በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋልና ቶሎ ወደ ስራ የመግባት ችግሮች ቢስተዋሉም ችግሮቹን ለመፍታት የቅርብ ክትትልና አገዛ በመደረግ ላይ ነው፡፡
የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተግባራዊ እየተደረገባቸው ያሉት 11ዱ ከተሞች፤ አዳማ፣ ሐረር፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ ደሴ፣ መቐሌ፣ ሀዋሳ፣ አሶሳ፣ ሰመራ፣ ጋምቤላና ጅግጅጋ መሆናቸው ታውቋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ጌትነት ምህረቴ