• የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎች እንደሚመለሱም ጥሪ አቅርቧል
አዲስ አበባ፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ በደረሰው የአራት መስጅዶች ቃጠሎና ጥቃት የተጠረጠሩ ሰዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን መረዳት ችለናል ሲል የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለፀ፡፡ ክልሉ የሙስሊም ማህበረሰቡን ጥያቄዎች እንዲመልስም ጥሪ አቅርቧል፡፡
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት በሞጣ ከተማ መስጅዶችና በሙስሊሙ ማህበረሰብ ንብረት ላይ የደረሰውን ጥቃት የሚያጣራ ኮሜቴ አዋቅሮ የችግሩን መነሻና ሂደት ሲያጣራ የቆየ ሲሆን ትላንትም የጥናቱን ውጤት አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የመጀሊሱ ጊዜያዊ አስተዳደር የቦርድ አባል ሼህ ኑረዲን ደሊል በዚሁ ወቅት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለፁት፤ የክልሉ አመራሮች ከጠቅላይ ምክር ቤቱ ለተላከው አጣሪ ልዑካን ቡድን መልካም ትብብር ያደረጉ ሲሆን በመንግሥትና በፀጥታ መዋቅር ውስጥ ያሉትን ጨምሮ በጥቃቱ ተሳታፊ ናቸው የተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ ላይ መሆኑን መረዳት ችለናልም ብለዋል፡፡
በጥቃቱ አንድ መስጅድ ሙሉ ለሙሉ፣ ሁለቱ ደግሞ በከፊል መቃጠላቸውንና አንዱ መስጅድ ደግሞ በድንጋይ ውርወራ መስታወቶቹ የመሰባበር ጉዳት የደረሰበት መሆኑን የገለፁት ሼህ ኑረዲን፣ የሙስሊሞች ሱቆችና ንብረቶች መቃጠላቸውንም ቦታው ድረስ ሄደው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡
በድርጊቱም የከተማው የመንግሥት መዋቅር ጭምር እጁ እንዳለበት ማረጋገጫ እንዳለ የጠቆሙት ሼህ ኑረዲን ለዚህም ማረጋገጫ የክልሉ ልዩ ሃይል ወደ ከተማው እንዳይገባ መንገድ በድንጋይ መዘጋቱንና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥቃቱን እንዳይከላከል ከቤት አትውጣ መባሉን ከሙስሊሙ ማህበረሰብ መረዳት መቻላቸውን ገልፀዋል፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልል መንግሥት ጥቃቱን ለማጣራት ወደ ስፋራው ለሄዱ ልዑካን ቡድን ትብብር ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
በአንፃሩ የክልሉ መንግሥት ለደረሰው ጉዳት ይቅርታ መጠየቅ፣ ለጉዳቱ ተገቢውን ካሳ መክፈልና መልሶ ግንባታ ማካሄድና ለሞጣ ሙስሊም ማህበረሰብ የደህንነት ዋስትና መስጠት አለበት የሚሉ ጥያቄዎች ከቃል በዘለለ የጽሁፍም ሆነ የተግባር ይፋዊ ምላሽ አለመሰጠቱን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ክልሉ በጎ አዝማሚያ እንዳሳያቸው አውስተው ሆኖም በይፋ ምልሽ ሊሰጥባቸው ይገባል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ጌትነት ምህረቴ