- የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለችግሮቹ ዘላቂ መፍትሄ እሰጣለሁ ብሏል
አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት እድለኞች ቤቶቹን ሳይረከቡ ከባንክ ጋር ተዋውለው ክፍያ መጀመራቸው ከአቅም በላይ ለሆነ ወጪ እንደዳረጋቸው ቅሬታቸውን ገለጹ። የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በበኩሉ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተወያይቶ ችግሩን እንደሚፈታ አስታውቋል።
በቦሌ በሻሌ የጋራ መኖርያ ቤት ከሚገኙ የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የአንዱ እድለኛ የሆኑት አቶ መሐመድ ስለምንዳ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ ባልተጠናቀቁበትና ቁልፍ ባልተረከቡበት ሁኔታ ከባንክ ጋር እንዲዋዋሉ በመደረጋቸው ለተጨማሪ ወጪ ተዳርገዋል። ከቤት ችግራቸው ሳይላቀቁ እና የቤት ቁልፍ ሳይሰጣቸው ለተደራራቢ ወጪ መዳረጋቸው ሳያንስ ስለአሰራሩ የሚያስረዳቸው አካል ማጣታቸው ደግሞ ቅሬታቸውን እንዳባባሰባቸው ይናገራሉ።
አቅደው ላልተዘጋጁባቸው ተደራራቢ ክፍያዎች እንደዳረጋቸው ያነሱት አቶ መሐመድ፤ በመኖሪያ ቤት ኪራይ ክፍያ፣ በመስሪያ ቦታ ኪራይ ክፍያ እና በባንክ ክፍያዎች የሰላም እንቅልፍ ማጣታቸውን ገልጸው፣ በዚህ የተነሳ ኑሮ እንደከበዳቸው በምሬት ተናግረዋል።
በዚሁ የጋራ መኖሪያ ቤት ባለእድል የሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ስዩም በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ከባንክ ጋር ተዋውለው ክፍያ የጀመሩ ሲሆን የቤቶቹ ግንባታ ግን ገና ብዙ የሚቀረው ነው።
የቤቶቹ ግንባታ የደረሰበትን ደረጃ በተመለከተ አቶ ቴዎድሮስ ሲናገሩ፤ “ከቦታ ቦታና ከብሎክ ብሎክ የተለያየ ነው። አልፎ አልፎ ቀለም የተቀቡ አሉ። የዚህ ምክንያት ምናልባትም የሚሰሩት ተቋራጮች (ኮንትራክተሮች) የተለያዩ በመሆናቸው ሊሆን ይችላል” ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
እጣው ከወጣላቸው ጊዜ ጀምሮም እየተመላለሱ የደረሰበትን እንደሚመለከቱ የገለጹት አቶ ቴዎድሮስ፤ እስካሁንም ግንባታው ከነበረበት እንዳልጨመረና ከነጭራሹ ሥራው እንደቆመም ገልጸዋል።
በዚህ ደረጃም ቢሆን የቤቶቹ እጣ እንዲወጣ መደረጉ እንደችግር የሚታይ አይደለም ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ ነገር ግን ከባንክ ጋር ተዋውሎ ክፍያ መጀመሩ ተገቢ አለመሆኑን ገልጸዋል። “የቤቶቹ ግንባታ ያለበት ደረጃ እና ቁልፍ የማስተላለፍ ሂደቱን በተመለከተ ለማህበረሰቡ በግልጽ እውነታውን ማሳወቅ ይገባ ነበር። ምክንያቱም በሕዝብና በመንግስት መካከል መጠራጠሮች እንዳይፈጠሩ ያደርጋል” ብለዋል።
ሌላዋ ባለእድል ወይዘሮ ኑራ ሚፍታህ በበኩላቸው፤ ከባንክ ጋር መዋዋላቸውን አስታውሰው፣ ቤቱ ገና ብዙ የሚቀረው በመሆኑ ለመጠናቀቅም ረዥም ጊዜ ሊወስድ የሚችል እንደሆነ ተናግረዋል።
ከባንክ ጋር ሲዋዋሉ የተረከቡት ምንም ነገር ባለመኖሩ ጥያቄ አንስተው እንደነበረ የሚናገሩት ወይዘሮ ኑራ፤ “እኛ ከማዋዋል በስተቀር አይመለከተንም፤ ቤቶች ልማትን ጠይቁ” እንደተባሉ እና ቤቶች ልማትም “በሕዳርና በታህሳስ ወር ቤታችሁን ትረከባላችሁ” ብሏቸው እንደነበር አክለው ተናግረዋል።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት ከትናንት በስቲያ የ40/60 ቤቶች ተዘዋውረው በጎበኙበት ወቅት የኮሚቴው አባል አቶ ዶጊሶ ጎና እንዳሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ትክክለኛና ተገቢነት ያለው ጥያቄ ማንሳታቸውን ገልጸው፤ ቤቶቹ በተገቢው ተሰርተው እንዲጠናቀቁ የከተማ አስተዳደሩ በቂ ግብዓት ማቅረብ ነበረበት ብለዋል። በተቋራጮችና በአማካሪዎች በኩል ሌሎች ችግሮች ሊኖሩ ቢችሉም በሚያሠራው አካል በኩል ግን ይሄን ያህል የገዘፉ ችግሮች መከሰት አልነበረባቸውም ብለዋል።
አቶ ዶጊሶ እንዳሉት ቋሚ ኮሚቴው እጣ የወጣላቸው እድለኞች ቤቱን መረከብ አለባቸው ብሎ ያምናል። ከባንክ ጋር ውል ገብተው ለተደራራቢ ወጪዎች መዳረጋቸው ግን አግባብነት የለውም ሲሉ ተናግረዋል።
“የግንባታ ሥራ በመንግስት በኩልም የተለያዩ ተቋማትን ቅንጅት የሚጠይቅ በመሆኑ ተናበው ሊሰሩ ይገባል፤ ለምሳሌ አስኮ የ40/60 ፕሮጀክት ከተጀመረ አንስቶ የውሃ አቅርቦት የላቸውም። የመሰረተ ልማትና የጊቢ ዝግጅቶቹም አልተሟሉም። በእነዚህና በሌሎች ተደራራቢ ችግሮች የተነሳ ባለእድለኞች ላይ መጉላላቶች ደርሰዋል። ሁሉንም ፕሮጀክቶች በአካል ተገኝተን ከለየን በኋላ የሚመለከታቸው ባለድርሻ መስሪያ ቤቶች የበላይ ኃላፊዎች በተገኙበት አቅርበን በመወያየት ዘላቂ መፍትሔዎች ለማበጀት ጥረት ይደረጋል” ሲሉ አቶ ዶጊሶ አብራርተዋል።
ከቤት እድለኞች የቀረቡ ቅሬታዎችን ይዘን የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ይሰጥበት ዘንድ በተደጋጋሚ ቢሯቸው ተገኝተን ጥረት ያደረግን ቢሆንም ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ማካተት አልቻልንም። የ40/60 ቤቶች የሁለተኛው ዙር እድለኞች ከ11 ወራት በፊት በእጣ ይፋ መደረጋቸው ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ሙሐመድ ሁሴን