አዲስ አበባ:- የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አፀደቀ።
የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 8ኛ መደበኛ ስብሰባው የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1176/2012 በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አፀድቋል።
በምክር ቤቱ የሕግ፣ የፍትህና የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተወካይ አቶ አበበ ጎዴቦ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ አስመልክተው ባቀረቡት ሪፖርት፥ የሽብር ድርጊት በሰው ህይወት፣ አካል እና ሥነ ልቦና እንዲሁም ንብረትና ማህበራዊ መስተጋብር ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አብራርተዋል።
ቋሚ ኮሚቴው በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ከጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሥራ ሃላፊዎች፣ ከሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ከተውጣጡ የፍትህ አካላት፣ ከህዝብ እና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ዝርዝር ውይይት ማድረጉን አንስተዋል።
በዚህም ረቂቅ አዋጁን አስመልክቶ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መሰጠቱን እና ለረቂቅ አዋጁ ግብዓት የሚሆኑ ሐሳቦች መገኘታቸውን አውስተዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተስተዋለ ያለውን ችግር ለማስወገድ እና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ረቂቅ አዋጁ ቢፀድቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም በምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል።
የምክር ቤቱ አባላትም የቀረበውን ሪፖርት በተመለከተ መስተካከል ይገባቸዋል ያሏቸውን ሐሳቦች አቅርበው ውይይት ከተደረገባቸው በኋላ በአንድ ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ፋና ብሮድካሲቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር