“ባለን የቱሪዝም ሀብት ደረጃ ተጠቃሚ እየሆንን አይደለም”
– በዘርፉ ጥናት ያቀረቡ ባለሙያ
አዲስ አበባ:- ዩኔስኮ በዓለም አቀፍ ቅርስነት ከመዘገባቸው የቱሪዝም ሀብቶቻችን ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ተጠቃሚ መሆናቸውን የባህልና ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ። ኢትዮጵያ በዘርፉ እምቅ ሀብት ቢኖራትም በሚገባ ባለመሥራታችን ተጠቃሚ እየሆንን እንዳልሆነ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ባለሙያ ገልፀዋል።
ከአዲሰ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ የተገኘ መረጃ እንዳመለከተው የዓለም ቅርሰ የሆኑት የቱሪዝም ሀብቶቻችን ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ ካለመሆኑም በላይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በየዘርፉ ተጠቃሚ ያደርጋል።
በአዲሰ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዳይሬክቶሬት የቋሚ፣ ተንቀሳቃሽ እና የኢንታንጀብል ቅርስ ምዝገባና ቁጥጥር ቡድን ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት መምህር መክብብ ገብረማርያም ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደተናገሩት በዩኔስኮ የተመዘገቡት ቅርሶቻችን ህዝብ በደምና ባጥንቱ ጠብቆና ተንከባክቦ፤ ሳይበረዙና ሳይከለሱ፤ በቅኝ ገዥዎች አስተሳሰብ ሳይጠለፉ ከዚህ ያደረሳቸው ናቸው። በመሆኑም ተጠቃሚው የተወሰነ አካል ሳይሆን ሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ ነው።
እንደ መምህር መክብብ አገላለፅ በቱሪስት ፍሰት ምክንያት የሚገኝን የግብይት አጋጣሚ የበለጠ ለመጠቀም የሚመለከታቸው ሁሉ ከመስተንግዶና የገበያ አቅርቦት ጀምሮ ቱሪስቶች የሚፈልጉትን ሁሉ በማሟላት ከዘርፉ ከሚገኘው ኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው።
አንድ ቅርስ ከአገር አልፎ የዓለም ቅርስ ሲሆን የዓለም ዓይን ሁሉ ይስባል የሚሉት መምህር መክብብ፣ ያንን ቅርስ የመጠበቁ፣ የመንከባከበቡ፣ ስለቅርሱ ጥናትና ምርምር ማድረጉ ሁሉ የጋራ ሥራ እንደሚሆን፤ ይህም ለቅርሱ ባለቤት ያለው ሁለንተናዊ ፋይዳ ቀላል እንዳልሆነም ተናግረዋል።
በባህላዊ ቱሪዝም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪአቸውን የሠሩት አቶ ደጀን ጥላዬ በበኩላቸው “የቅርሶቻችን በዩኔስኮ መመዝገብ ከገበያም ሆነ ማንነትን ከማሳወቅ (Marketing and Branding) አኳያ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፤ በተለይም ወደ እዚህ የሚመጡ ቱሪስቶች ብድግ ብለው የሚመጡ ሳይሆኑ ዩኔስኮን በመሳሰሉ ተቋማት እውቅና ያላቸውን አካባቢዎች በመለየት ስለሆነ እውቅናው ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
ከኢኮኖሚም አኳያ ቱሪዝም ዘርፈ ብዙ በመሆኑ እሱን ተከትለው የሚፈጠሩ በርካታ ኢንዱስትሪዎች ስላሉ ህዝቡን ተጠቃሚ የማድረጉ ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
እውቅናው “ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ” አለው ከሚለው የመምህር መክብብ ሐሳብ ጋር የሚስማሙት አቶ ደጀን ሆኖም በሚገባ ባለመሥራታችን ተጠቃሚ እየሆንን አይደለም ብለዋል።
በፕሮሞሽን እጥረት፣ በታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች እንክብካቤ ማጣት፣ የተደራሽ ቦታዎች አለመብዛትና የተወሰኑ ስፍራዎች ላይ ብቻ ማተኮራችን፣ በቱር ኦፕሬተሮች አካባቢ ባሉ የተለያዩ ክፍተቶችና ሌሎችም ምክንያቶች የቱሪዝም ሴክተሩ ከሌሎች አገራት ጋር በንፅፅር ሲታይ የሚፈለገውን ያህል እንዳያድግ እንዳደረገው ገልፀዋል።
መንግሥት የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ብቻ እያተኮረ ሌሎቹን የዘርፉን እንቅስቃሴዎች ለግሉ ሴክተር መተው አለበት የሚሉት ጥናት አቅራቢው ይህ ሲሆን የቱሪዝሙ ሴክተር እንደሚያድግና የህዝብ ተጠቃሚነትም የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።አቅራቢው ይህ ሲሆን የቱሪዝሙ ሴክተር እንደሚያድግና የህዝብ ተጠቃሚነትም የተሻለ እንደሚሆን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 24/2012
ግርማ መንግሥቴ