አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብሎም የአፍሪካ ህብረትና የበርካታ አለም አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫ ብትሆንም ዘመኑን የሚመጥን የመሰረተ ልማት እና የቱሪስት መስህብ ስፍራዎችን አልያዘችም።
ከተማዋ ካለባት የፅዳት ጉድለት እና ንፁህ አየር ችግር የተነሳ በነዋሪዎቿና ለአጭርም ይሁን ረዘም ላለ ጊዜ ሊጎበኟት በሚመጡ እንግዶቿ ስትተች ኖራለች። የወንዝ ዳርቻዎቿ የቆሻሻ ማራገፊያና ማጠራቀሚያሆነው በአካባቢው ለሚያልፍ ነዋሪ በሽታን እንካችሁ ሲሉ ከቆዩ ከራርመዋል።
ይህ የከተማዋ መለያ የሆነው የቆሻሻ ጉዳይ እና የመዝናኛ ቦታዎች እጥረት ታሪክ ሊሆን የሶስት አመታት ጊዜ የተያዘለት ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት 48 ሄክታር ስፋት ያላቸው የማዕከላዊ ፓርኮች ግንባታ እና 51 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ከእንጦጦ ተራራ እስከ አቃቂ ወንዝ የሚደርሱ ሁለት ትላልቅ ወንዞችን የማልማት ስራ ተጀምሮ ግንባታዎች በፍጥነት እየተከናወኑ ነው።
የፕሮጀክቱ ሰራተኞችም ግንባታዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና ሲሉ ተመልክተናል።
የዚሁ ፕሮጀክት አካል የሆነው የማዕከላዊ ፓርክ ግንባታ እና 12 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት በመስከረም ወር 2012 ዓ.ም በይፋ የማስጀመር ስነ ስርዓት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ እና በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ መጀመሩ ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነውን የአዲስ አበባ ወንዝ ዳርቻ አረንጓዴ ልማት ስራ ትናንት ሸራተን አካባቢ ባለው የግንባታ ቦታ ተገኝተው በጎበኙበት ወቅት በብልፅግና ዘመን ለአዲስ አበባ ከተማ ፀሀይ እየወጣላት እንደሆነ ተናግረዋል።
ይህ ፕሮጀክት ከሚጠበቀው በላይ እየተከናወነ እንደሆነ የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በመንግስት የፕሮጀክቶች ማስፈፀም ላይ እየተስተዋለ ያለውን ችግር እየቀረፈ ያለ ማሳያ ተደርጎ ሊታይ የሚችል እንደሆነም ጠቁመዋል።
ፕሮጀክቱ እንጦጦ እና አንድነት ፓርክ ላይ እየተሰራ ያለውን ስራ እንዲሁም ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ ያለውን የወንዝ ዳር ማልማት ፕሮጀክት የሚያገናኝ እና የአዲስ አበባን ገፅታ በብዙ መልኩ የሚቀይር ነው ተብሏል።
‹‹በብልፅግና ጉዞ ዘመን አንዱ ማረም የምንፈልገው ነገር የምናስበውን መፃፍ፣ የምንፅፈውን ለህዝብ መናገር እና የተናገርነውን ደግሞ ተግባራዊ አድርጎ መገኘት ነው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ አንፃር ፕሮጀክቱ አርአያ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ስራ ተጀምሮ በታለመለት ጊዜ ሲጠናቀቅ እንደማይስተዋል የገለፁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ 47 ሄክታር ገደማ ስፋት ያለውና በውስጡ ምግብ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች፣ መዝናኛ ማዕከላትና ሌሎችንም ያካተተው ይህ ስራ በሶስት ወራት ውስጥ 45 በመቶ መጠናቀቁን ገልፀዋል።
በመጪው ግንቦት ወር ተጠናቆ ሙሉ በሙሉ ክፍት እንደሚሆን የተገለፀ ሲሆን ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ ያለው የወንዝ ዳር ማልማት ፕሮጀክት ደግሞ በሚቀጥለው አመት እንደሚሰራ ተገልጿል።
አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ አበባ በማድረግ የአፍሪካ ካፒታል እንድትሆን ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የችግኝ መትከል፣ ማጽዳት፣ ፓርኮችን ማስፋፋትና መሰል ስራዎች በሚቀጥሉት ሶስት አመታት በትኩረት እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።
አዲስ አበባን ድንቅ ከተማ በማድረግ ለነዋሪዎቿ ብሎም ለጎብኝዎች የተመቸች እና ሳቢ እንድትሆን መላው የከተማዋ ነዋሪዎች እንዲሁም ወዳጆች ዛፎችን በመትከል፣ በማፅዳት እና ልማቶችን በመንከባከብ አርአያ ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል።
‹‹የነዋሪዎቿን ኑሮ ማሻሻል፣ ስራ አጥነትን መቀነስና የማልማት ስራ መስራት አዲስ አበባ የእኛ መሆኗን የምናረጋግጥባቸው መንገዶች ናቸው›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ገፅታዋን በመቀየር ተቆርቋሪነትን ማስመስከር እንደሚገባም ገልፀዋል።
በፕሮጀክቱ ለ1 ሺህ 300 ያህል ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር የተቻለ ሲሆን ከሁለት ወራት በኋላ 4 ሺህ ሰዎች እንደሚቀጠሩ ይህም የስራ እድል ፈጠራውን ስራ እንደሚያግዝ ተነግሯል።
እነዚህና መሰል ፕሮጀክቶች አዲስ አበባ በብልፅግናው ዘመን ፀሀይ እየወጣላት ስለመሆኑ ማሳያዎች ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፣ ፀሀዩን ወደ ሌሎች የክልል ከተሞች በማስፋትና ስራዎችን በመስራት የኢትዮጵያን የቱሪስት ፍሰት ማሳደግና እውነተኛ ብልፅግናን ማየት እንደሚቻልም አረጋግጠዋል።
በቻይና መንግስት ሙሉ ወጪ እየተከናወነ ላለው ይህ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቻይናን መንግስት እና በኢትዮጵያ የቻይና ኤምባሲን አመስግነዋል። ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፎች የሚከናወን ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ 32 ሄክታር ጠቅላላ ስፋት ያለው የማዕከላዊ ፓርክ ግንባታ እና አንድ ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራን በ2020 እኤአ አጋማሽ ለማጠናቀቅ ውጥን ተይዞ እየተሰራ ነው።
ሁለተኛው ምዕራፍ ቀሪውን 16 ሄክታር ማዕከላዊ ፓርክ እና 10 ነጥብ ስምንት ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ልማትን የሚያጠቃልል ሲሆን በውስጡ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሙዚየም፣ የልጆች መጫወቻዎች እና ኪነጥበባዊ የአትክልት ስፍራዎች ይኖሩታል፤ በ2021 እኤአ ይጠናቀቃል ተብሎም ይጠበቃል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወንዝ ዳርቻና አረንጓዴ ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የፕሮጀክቱ ባለቤት ሲሆን ሲሲሲሲ ፈርስት ሀይዌይ ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ድርጅት ደግሞ ግንባታውን እያከናወነ የሚገኝ ተቋራጭ ነው።
በጉብኝቱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ም/ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች እንዲሁም በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ታን ጂያን ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመንታህሳስ 23/2012
በድልነሳ ምንውየለት