• 50ሺ የምርጫ ጣቢያዎችን፤
• 300ሺ የምርጫ አስፈጻሚዎችን፤
• 50 ሚሊዮን መራጮችን ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት እየተደረገ ነው
አዲስ አበባ፡- ለስድስተኛ ጊዜ ለሚካሄደው የ2012 ዓ.ም ሀገራዊ ምርጫ 50ሺ የምርጫ ጣቢያዎችን፣ እስከ 300 ሺ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና 50 ሚሊዮን መራጮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ታሳቢ ያደረገ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን ምርጫ ቦርድ አስታወቀ። በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም የገንዘብ ድጋፍ ለመራጮች ምዝገባ የሚውሉ የህትመት ሥራ በዱባይ በመከናወን ላይ እንደሆነም ገልጿል።
የቦርዱ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች አማካሪ ወይዘሪት ሶሊያና ሽመልስ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ሀገራዊ ምርጫን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ ለማካሄድና ተአማኒ እንዲሆን ቦርዱ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በየደረጃው በማከናወን ላይ ይገኛል። በዚህም 50 ሚሊዮን መራጮች ይመዘገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል። በመሆኑም ከ250ሺ እስከ 300 ሺ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ለመመልመል ታቅዷል። 50ሺ የምርጫ ጣቢያዎችም ይዘጋጃሉ። ቦርዱ በአማራ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና ሐረሪ ክልሎች የምርጫ አስፈጻሚ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ቅጥር ለመፈጸም ምልመላ አጠናቅቋል።
እንደ ወይዘሪት ሶሊያና ገለጻ፣ ከቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹ አንዱ ለመራጮች ምዝገባ የሚውሉ የህትመት ሰነዶችን ማመቻቸት አንዱ ሲሆን፣የተባበሩት መንግሥታት የልማት ድርጅት ለምርጫው የቴክኒክና የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ በገባው ውል መሰረት ከቦርዱ ጋር የ40ሚሊዮን ብር ስምምነት ፈጽሟል።
የህትመት ሥራው በዱባይ እንዲከናወን የተወሰነው ባለፉት በተካሄዱት ምርጫዎች ከምርጫ ሰነድ ጥራት ጉድለት ጋር ተያይዞ ይታዩ የነበሩ ክፍተቶችን በማስቀረት ዓለም አቀፍ የምርጫ ደረጃን ለማሟላት ሲባል ሲሆን፣በሌላ በኩል በጥራት፣በመጠን፣በዋጋና በጊዜ ሰነዶቹን አትሞ የሚያቀርብ ተቋም በሀገር ማግኘት ባለመቻሉ ነው ብለዋል።
በቅርቡ በሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በተካሄደው ምርጫ በተመሳሳይ ቀለም የታተመና በሚፈለገው መጠንም ለማግኘት የነበረውን ችግር ወይዘሪት ሶሊያና ለአብነት ጠቅሰዋል።የመራጮች እና የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቁጥር ከታወቀ በኋላ ደግሞ ለድምጽ መስጫ የሚውል ሰነድና ኮሮጆ በቀጣይ የሚከናወን መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜግነት ከሌላቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተያያዘ ስለሚነሳው ጉዳይም ወይዘሪት ሶሊያና ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ እያንዳንዱ ፓርቲ ያለውን በሺዎች የሚቆጠር አባል ዜግነት ለማረጋገጥ አስቸጋሪ ቢሆንም ፓርቲዎቹ የአባላት ምዝገባ የሚያካሂዱት የምርጫ ህጉን አክብረው በመሆኑ ችግሩ ይኖራል ብለው አያምኑም።ሆኖም ቦርዱ ከህግ ውጭ ተፈጽሞ ከሆነና ከደረሰበት ማስተካከያዎችን እንደሚወስድ አመልክተዋል።
በአዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ላይ በአንዳንዶች ስለሚነሳው ቅሬታም እንደገለጹት ህጉን ሁሉም በተመሳሳይ ይቀበለዋል ብሎ መገመት ባይቻልም አዋጁ የሚያከራክር አንቀጽ የለውም ብለዋል።ቦርዱ ምርጫው የሚካሄድበትንና የሚጠናቀቅበትን እንዲሁም በወቅቱ መደረግ የሚገባቸውን ለህዝብ ይፋ እንደሚያደረግ ገልጸዋል።በቦርዱ ተመዝግበው የእውቅና የምስክር ወረቀት የተሰጣቸው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች 74 መሆናቸውንም ገልጸዋል።
አዲስ ዘመንታህሳስ 23/2012
ለምለም መንግሥቱ