‹‹አዋጁ ዜጎችን ለሞት እየዳረገ ያለውን ሃሰተኛ መረጃና የጥላቻ ንግግርን ለመገደብ ነው››
– ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ
አዲስ አበባ፡- የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተዘጋጀው አዋጅ ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን እንዳይጎዳ፣ እንዳያጣብብና እንዳይገድብ ጥንቃቄ እንዲደረግ ባለድርሻ አካላቶች አሳሰቡ። የአዋጁ ዓላማ ዜጎችን ለጥቃት የሚያጋልጡ፣ ለበርካቶች መፈናቀልና ሞት ምክንያት እየሆነ ያለውን የሃሰተኛ ስርጭትና የጥላቻ ንግግርን መገደብ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ገልጿል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የጥላቻ ንግግርና የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው ረቂቅ አዋጅ ላይ ትናንት ይፋዊ የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ፤ የህጉ አርቃቂዎች ሃሳብን የመግለጽ መብትን ለማስጠበቅና ስጋትና አደጋ ነው የተባለውንም ለመቆጣጠር ሚዛን ለማስጠበቅ ጥረት ማድረጋቸውን እንደተገነዘቡ ተናግረዋል።
ሁለት የተለያዩ ጽንሰ ሃሳቦችን በአንድ ህግ ለማስተዳደር መሞከሩ ተጽእኖ መፍጠሩን ጠቁመዋል። የተለያዮ ጽንሰ ሃሳቦች የሆኑ፣ በይዘት፣ በትርጉማቸውና በአተገባበራቸው አከራካሪ ጽንሰ ሃሳቦች መሆናቸውንም አንስተዋል። የህግ አቀራረቡ ተለያይቶ መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል።
ሃሰተኛ መረጃ ማሰራጨት ጽንሰ ሃሳብ በኢትዮጵያና በሌሎች አገሮች ታሪክም ነጻ መገናኛ ብዙሀን ሃሳብን በነጻ የመግለጽ መብትን ለመገደብ እንደመሳሪያ ያገለገለ ጽንሰ ሃሳብ መሆኑን አስታውሰው፤ ሲተገበር ከፍተኛ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት አሳስበዋል።
በአዋጁ የወንጀል ጥፋተኛነትና ተጠያቂነት የሚረጋገጥበትን የኢትዮጵያን የወንጀለኛ መቅጫ ድንጋጌዎችን ከአንቀጽ 42 እስከ 47 የተመለከተውን የወንጀል ተጠያቂነት እንደሚያረጋግጥ ማስቀመጡ ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
አንቀጾቹ ከህገ መንግስቱ ጋር የሚቃረኑ፣ ምናልባትም የወንጀል ህግ አልያም የሚዲያ ህጉን መሻሻል ተከትሎ የሚቀየሩ በመሆናቸው እንደገና ስራ ላይ መዋል እንደሌለባቸው ተናግረዋል። ምናልባትም እየተዘጋጀ ካለው የሚዲያ አስተዳደር ህግ ጋር የሚታይ በመሆኑ አንቀጾቹ በአዋጁ ሊካተቱ እንደማይገባቸው ዶክተር ዳንኤል ጠቁመዋል።
የጥላቻ ንግግር ጽንሰ ሃሳብም አከራካሪ መሆኑን ጠቁመው፤ ሃሳብን የመግለጽ መብትን ማክበር አስደንጋጭ፣ የሚያስቆጣ፣ የሚያናድድ፣ የሚያበሳጩ ሃሳቦችን ጭምር መታገስን እንደሚያካትት ተናግረዋል።የሌሎችን ሰዎች መብትና ጤንነት፣ የአገርን ደህንነት ለመጠበቅና ለመሳሰሉ ምክንያቶች መብቱ ገደብ እንደሚጣልበት አስታውሰዋል።
ጠበቃና የህግ አማካሪ አቶ አምሀ መኮንንም ህጉ ሌላ ጦስ እንዳያስከትል በአግባቡ መታየት እንደሚገባው፣ የትኛው የጥላቻ ንግግር እንደሚያስቀጣ ተዘርዝሮ አለመቀመጡንም ነቅፈዋል። አቶ ዮሃንስ እንየውም በተመሳሳይ አንድ መረጃ ውሸት ወይም እውነት መሆኑን የሚያረጋግጠው አካል በሌለበት ህጉን መተግበሩ አስቸጋሪ እንዳይሆን ተናግረዋል።
ሌሎች አስተያየት ሰጪዎችም ‹‹አፋኝ የነበረውን የጸረ ሽብር ህጉን የሚያስታውስ ነው፣ የወንጀለኛ ህጉ እያለ ሌላ ህግ ማውጣት አስፈላጊ አይደለም›› ብለዋል። የተቀመጠውን ቅጣትና የገንዘብና የእስራት ቅጣት የተመጣጣኝ መርህን ይጥሳል ሲሉም ተቃውመውታል።
የዴሞክራሲ ምህዳሩን ከማስፋት አንጻርም ጠንቅ እንዳይሆን ጥንቃቄ እንዲደረግም ጠቁመዋል። ‹‹የሽግግር ወቅት እንደመሆኑም መንግስትን የሚተቹ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ሊጎዳ ይችላል›› የሚል ስጋትም ተነስቷል። ከአለም አቀፍ ድንጋጌዎች ጋር እንዲጣጣም ማድረግ እንደሚገባም አሳስበዋል።
ከተሰብሳቢዎች ለተነሱት ጉዳዮች ማብራሪያና ምላሽ የሰጡት ምክትል ጠቅላይ ዐቃቤ ህጉ ዶክተር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ፤ ህጉ ሃሳብን የመግለጽ መብትን ይጥሳል፣ ያጣብባል በሚል ከተወያዮች የተነሱትን ስጋቶች አስመልክተው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የሚጣለው ገደብ ከህጉ ዓላማ እንዳያልፍ ጥንቃቄ መደረጉን ተናግረዋል።
ሃሳቡ መንግስትን የሚተቹ የተለየ ሃሳብ ያላቸውን ሰዎች ማጥቃት ወይም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ማፈን ቢሆን ኖሮ አዋጁ የወንጀል ህግ አንቀጽ 486 እንደማይሽረው ጠቁመዋል። ለትርጉም ተጋላጭ ሆኖ ሰፍቶ የተቀመጠ በመሆኑ እነርሱን በመጠቀም ክሶችን መመስረት ይቻላል ብለዋል ዶክተር ጌዴዎን።
አዋጁ አንቀጽ 486 ሽሮ ልዮ ሁኔታን በመደንገግ ሃሳብን በነጻነት የመግልጽ መብትን የተሻለ ጥበቃ ለማድረግ መሞከሩን ተናግረዋል። የአዋጁ ዓላማ ዜጎችን ለጥቃት የሚያጋልጡ፣ ለበርካቶች መፈናቀልና ሞት ምክንያት እየሆነ ያለውን የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግርን መገደብ መሆኑን ጠቁመዋል። በተቃራኒውም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ለማስጠበቅ ሚዛን ባስጠበቀ መንገድ እንዲተገበር መደረጉን ተናግረዋል።
የጥላቻ ንግግር ሲባል በጣም አደገኛ የሆኑ፣ ጉዳታቸው ከፍተኛ የሆኑ በተለይም ከብሄርና ከሃይማኖት ጋር የተያያዙ የጥላቻ ንግግሮች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን ጠቁመዋል። ሃሰተኛ የመረጃ ስርጭት ሲባልም ማንኛውም ስህተት ያለውን መረጃ ሳይሆን ሆን ተብሎ የሚሰራጭ ጥቃት ወይም ሁከት የማድረስ እድሉ ከፍተኛ የሆነ የሃሰተኛ መረጃ ስርጭትን መሆኑን አብራርተዋል።
ከአስፈላጊነት ጋር ተያይዞ የተነሳውን በማስመልከትም ምላሽ የሰጡት ዶክተር ጌዴዎን፤ ከወንጀለኛ ህጉ አንቀጽ 486 እና ሌሎች በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ የተቀመጡ ድንጋጌዎች እያሉ አዋጁን ማውጣት ያስፈለገው፤ ተግባራዊ ሲደረግ የወንጀል ህግ በቀጥታ ያስቀመጠው ክልከላ ከሌለ አመሳስሎና ለጥጦ መተርጎም ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ ህጉን ማውጣት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት። ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ ህግ ጋር የሚጣጣም መሆኑን ተናግረዋል። ይበልጥ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን ለይቶ ጥበቃ ያደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
የፕሬስ፣ የኪነ ጥበብ ስራን የምርምር፣ የትምህርት፣ የሃይማኖት ነጻነትን እንዳይጥስ ጥንቃቄ መደረጉንም ነው የተናገሩት። ተመሳሳይ አዋጅ በተለያዩ አገራት በመኖራቸው አለም አቀፍ ገጽታ ላይ ተጽዕኖ እንደማይኖረውም ገልጸዋል። ከአንቀጽ 42 እስከ 47 የወንጀል ህጉ የተወሰደው አንቀጾች አስመልክቶም መልሶ ከሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር መመልከት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመንታህሳስ 23/2012
ዘላለም ግዛው