የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገቢዎች የበጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ተሻሽሎ በቀረበው ኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ላይ የባለድርሻ አካላትን ሀሳብ ለመረዳት ለግማሽ ቀን ባዘጋጀው መድረክ ላይ አብዛኛው ተሳታፊ በታክስ ማሻሻያው ላይ ቅሬታ አልነበረውም። ‹‹ታክሱ በዝቷል እንደገና ይፈተሽ›› የሚለው ሀሳብ ነበር ሚዛን የደፋው።
በውይይቱ የሁለት ወገን ክርክር የሚመስሉ አስተሳሰቦች ግን ተንጸባርቀዋል። በጤናው እና በማህበራዊ ዘርፍ ተወክለው የተሳተፉት በተለይ በአልኮል መጠጥና በትንባሆ ላይ የተጣለው ታክስ ሲያንስ እንጂ አይበዛም በማለት፣ ቀድሞ መከላከል በሚቻል የጤና ችግሮች የሚሰቃዩ ዜጎች መኖራቸውን በመጥቀስ ተከራክረዋል።
በአምራች ኢንዱስትሪውና በአገልግሎት ዘርፉ ላይ ያሉት ደግሞ የታክስ ማሻሻያው ከፍተኛ መሆን ኢንቨስትመንትን ያዳክማል፣ ከገበያም ያስወጣል የሚል ስጋት ተነስቷል።
‹ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ›ን የወከሉት አቶ ወንዱ በቀለ በአሁኑ ጊዜ 50 በመቶ የሚሆነው ህዝብ አስቀድሞ መከላከል በሚቻል በሽታ እንደሚሰቃይ፣ 70 በመቶ ወጣት በአደገኛ ሱስ ውስጥ እንደሚገኝ፣ ሴቶችና ህፃናት ለጥቃት የሚጋለጡት በአልኮል መጠጥና በሲጋራ ሱስ በተጠመዱ ሰዎች እንደሆነ ይገለፃል።
መንግሥትም ከሚበጅተው በጀት ጤናው ዘርፍ ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚይዝ በጥናት መረጋገጡን በማስረዳት ከችግሩ አሳሳቢነት አንጻር ታክሱ ከፍ ማለቱ ተገቢነት እንዳለው አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ማህበርን ወክሎ የተሳተፈውም ከፍተኛ የሥራ አጥ ባለበት ሀገር ሱሰኝነትን ማበረታታት ተገቢነት እንደሌለው በመጠቆም፣ በአሁኑ ጊዜ በትምህርት ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ትንባሆ ተጠቃሚ መኖሩንና በአነስተኛ ዋጋም እየቀረበላቸው መሆኑን አመልክተዋል።
ወጣቱን ከሱስ ለመታደግ ታክሱን ከፍ ማድረግ ተገቢነት እንዳለው አስተያየቱን ሰጥቷል። አስተያየት ሰጭው በመኪና ላይ የተጣለውን ታክስ ግን አልተቀበለም። ወጣቱ መኪና እንዲኖረው እንደማያበረታታም የግሉን ሀሳብ አስቀምጧል።
ህዝብን ወክለው የተሳተፉት የኩላሊት ታማሚ ግለሰብም እንደገለጹት ታሽጎ ለገበያ በሚቀርብ ውሃ ላይ የጣለው ታክስ እንደርሳቸው ኩላሊት ታማሚ ለሆኑ ፈተና ነው።እስከ አንድ ወር ድረስ ውሃ በሚጠፋበት ሀገር ውስጥ ለሚኖር እና የውሃ ጥራቱም ለጤና ሥጋት በሆነበት ሁኔታ የታማሚውን ችግር ማባባስ እንደሆነ አስረድተዋል።
በቢራ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉትን ወክለው የተሳተፉት አቶ ሲሳይ ዘሪሁን በበኩላቸው በቀረጥ ጭማሪው ይስማማሉ። የእርሳቸው ቅሬታ የመጠኑ ከፍተኛ መሆኑ ነው። ዘርፉ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በመቶ ሺ የሚቆጠሩ አከፋፋዮችን፣ ከ10ሺ የሚልቅ ሰራተኛ ይዞ የሚንቀሳቀስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ተጽዕኖው ከፍተኛ ነው ብለውም ያምናሉ።
ኢንዱስትሪውን በማይጎዳ መልኩ ካልታየ ተጠቃሚው ደህንነቱ ወዳልተጠበቀ የመጠጥ ምርት እንዳይሄድ፣ በዚህም መንግሥት ከዘርፉ የሚሰበስበው ቀረጥ እንዳይቀንስበትና ችግሩ እንዳይባባስ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ከኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ የተወከሉት ተሳታፊ በማሻሻያው ተደራራቢ የቀረጥ ክፍያ ይቀራል ብለው ሲጠብቁ በተቃራኒው መጨመሩ እንዳስደነገጣቸው ገልጸዋል። ተቋማቸው በዕቅድ የያዘውን የኢንቨስትመንት ማስፋፊያ እንደሚገታውና ተቋሙ አሁን ባለው እንቅስቃሴ ብቻ ከተገታ ደግሞ ዕድገት እንደማይኖር በመጠቆም መንግሥት እንዲያጤነው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትን ወክለው የተሳተፉት አስተያየት ሰጭ፣ ቀደም ሲል ከማምረቻ ዋጋ ይጣል የነበረውን ቀረጥ፣ በማሻሻያ ረቂቅ አዋጁ ከመሸጫ ዋጋ ላይ እንዲቆረጥ መደረጉ እንዲሁም ቀደም ሲል ቀረጥ የማይጣልባቸው በማሻሻያው መካተታቸው አግባብ እንደሆነ በመጠቆም፣ በመኪኖች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ቀረጥ ሲጣል በሀገር ውስጥ አዲስ መኪና ማስመጣት የሚችሉና የሚገጣጥሙ ምን ያህል እንደሆኑ ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚያስፈልግ ሀሳብ ሰጥተዋል። በአጠቃላይ ማሻሻያው ተጠቃሚውንም አምራቹንም በማይጎዳ መልኩ መሆኑን መረጋገጥ ያስፈልጋልም ብለዋል።
የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር እዮብ ተካልኝ ከሌሎች የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በመሆን ከተሳታፊዎቹ ለተነሱት ጥያቄዎችና ሀሳቦች ማብራረሪያ ሰጥተዋል። ከተሳታፊዎቹ የተገኙትን ግብአቶች መሰረት በማድረግ የሚስተካከሉትን በማስተካከል መልሰው ለቋሚ ኮሚቴው እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።
የገቢዎች በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ለምለም ሀድጎ በውይይቱ ማጠቃለያ እንደገለጹት ረቂቅ አዋጁ የሁሉንም ፍላጎት እንዲያሟላ አይጠበቅም ፣ሆኖም ግን ከመጽደቁ በፊት ውይይት እንደሚያስፈልግ ግንዛቤ ተይዟል።ገቢ ለመሰብሰብ ተብሎ ህብረተሰቡን የሚጎዳ ነገር ካለ ወይም ህዝብን የሚጎዳ ነገር ካለ ደግሞ መታለፍ እንደሌለበት አስገንዝበዋል።
አዲስ ዘመንታህሳስ 23/2012
ለምለም መንግሥቱ