አዲስ አበባ፡- የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን በ2012 በጀት ዓመት የአምስት ነጥብ አራት ቢሊየን ብር የመንገድ ግንባታ ስምምነት ከሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ጋር ተፈራረመ፡፡
በኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ ዶክተር ግርማ አመንቴ በስምምነቱ ወቅት እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የ5 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ስምምነት መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
ስምምነት ከተፈጸመባቸው ሰባት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ሁለቱ ቀደም ሲል ውላቸው ተሰርዞ አዲስ ጨረታ ወጥቶባቸው ለሌላ ኮንትራክተር የተላለፉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ የመንገዱ አጠቃላይ ርዝማኔ 281 ነጥብ 16 ኪሎ ሜትር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 15 ኪሎ ሜትሩ የአስፋልት ንጣፍ እንደሆነ ተገልጧል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ለረዥም አመታት ትግል ሲያደርግባቸው ከነበሩ የልማት ጥያቄዎች አንዱ ፍትሃዊ የመንገድ ተጠቃሚነት እንደሆነ የገለጹት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ መንገድ የክልሉን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከሚያረጋግጡ መሰረተ ልማቶች አንዱ ነው ብለዋል፡፡
መንገድ በሌለበት እራስንም ሆነ አካባቢን ማሳደግ አዳጋች እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ የፌዴራል መንግስት ከሚያስገነባቸው መንገዶች በተጨማሪ የክልሉ መንግስትም ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ በጀት ይዞ ወደ ስራ መግባቱን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል ውል ገብተው በስምምነታቸው መሰረት መፈጸም ባልቻሉ ተቋራጮች ላይም እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ተናግረው አሁንም ጨረታውን አሸንፈው የተፈራረሙ ተቋራጮች መፈረም ብቻ ሳይሆን በገቡት ቃል መሰረት ስራቸውን በተባለው ቀን አጠናቀው ማስረከብ እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
የቀበሌ፣ የወረዳና የዞን ባለስልጣናትም ከተቋራጮች ጎን በመሆን ድጋፍና ክትትል አንዲደርጉ መክረዋል፡፡ የመንገዱ ተጠቃሚ የሆነው ህብረተሰብም የባለሀብቱን ንብረት እንደራሱ ሀብት እንዲጠብቅና በማንኛውም ጉዳይ ተባባሪ እንዲሆን ዶክተር ግርማ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኦሮሚያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ደጀኔ ፍቃዱ በበኩላቸው እንደገለጹት የዕለቱ መድረክ ከስምምነቱ በተጨማሪ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ለመንገድ ልማት የሰጠው ትኩረት፣ የመንገድ ልማቱን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ችግሮች የተነሱበት፣ ከህዝና ከባለድርሻ አካላት ምን ይጠበቃል? በሚሉት ላይም ምክክር የተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በዕለቱ የተደረጉት የስምምነት ፊርማዎችም የግንባታ፣ የማማከርና የዲዛይን ጥናት ሲሆኑ በአጠቃላይ 23 ስምምነቶች ተፈጽመዋል፡፡
እስከ አሁን የተጠናቀቁት አብዛኛዎቹ የመንገድ ግንባታዎች በውላቸው መሰረት የመጠናቀቅ ችግር እንዳለባቸው የተናገሩት ዳይሬክተሩ የጥራትም ሆነ የጊዜ ገደባቸውን ለመቆጣጠር እንዲቻል በአዲሱ ስምምነት የሚገነባውን የመንገድ ርዝማኔ በመወሰን እየከፋፈሉ ለማስገንባት የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል አዲሱን ስምምነት ሳይጨምር ቀደም ሲል የተጀመሩ 27 የመንገድ ፕሮጀክቶች በስራ ላይ ይገኛሉ ፡፡ እነዚህም በ9 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር የተከፈለና ገና የሚከፈል በጀት የተያዘላቸው ናቸው ተብሏል፡፡ በተያዘው ዓመት መጨረሻ9 ፕሮጀክቶች ተጠናቀው ወደ ሥራ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመንታህሳስ 23/2012
ኢያሱ መሰለ