- ‹‹የአንድን ተቋም የግዥ አፈጻጸምና የንብረት አስተዳደር በመንግሥት የግዥ ህግና መመሪያ መሰረት መፈጸሙን ኦዲት ለማድረግ በአማካኝ 16 ቀናቶችን ይወስዳል። እንዲሁም አንዳንድ ጊዜ የኦዲቱን ስራ በተያዘለት እቅድ መሰረት ለማከናወን ሲባል ደግሞ፤ ከስራ ሰዓት በፊትና በኋላ ያሉትን የእረፍት ጊዜያችንን ሰውተን የኦዲቱን ስራ የምንከውንበት ወቅት አለ። ነገር ግን በወር ለትራንስፖርት አበል የሚታሰብልኝ 75 ብር ብቻ በመሆኑ፤ አንድን ተቋም ኦዲት ለማድረግ ወደ ተቋሙ በምንመላለስበት ጊዜ አበሉ ስለማይበቃኝ ከወር ደመወዜ ለትራንስፖርት አወጣለሁ።
እንዲሁም ከወር ደመወዜ አምስት አስር ቆጥቤ እንደጓድኞቼ ተምሬ እራሴን መለወጥም ቀርቶ ለጸጉሬ ቅባት ገዝቼ እራሴን ለመጠበቅ የሚያቅተኝ ወቅት አለ። በአጠቃላይ በወር ለትራንስፖርት ተብሎ የሚከፈለኝ አበል የዘመኑን የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ያላገናዘበ በመሆኑ፤ ‹ከወረቱ ስንቁ ላቀ› ሆኖብኝ ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ተዳሪጊያለሁ›› በማለት ያጫወተችኝ በመንግስት ግዠና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ የኦዲት ባለሙያዋ ወይዘሪት ወንዜ ቢራራ ናት።
ባለሙያዋ እንዳብራራችው፤ በወር 75 ብር የትራንስፖርት አበል የሚለው መመሪያ የወጣው ‹‹በጃንሆይ›› ዘመነ መንግስት መሆን አለበት ስትል ተሳልቃ፤ በአሁኑ ወቅት ባለው የትራንስፖርት ታሪፍ መሰረት በቀን ወደ አንድ በመዲናዋ ወደ ሚገኝ የፌዴራል መስሪያቤት ደርሶ ለመመለስ ቢያንስ 20 ብር ያስፈልጋል። ስለዚህ አንድን የፌዴራል ተቋም ኦዲት ለማድረግ በአማካኝ 16 ቀናቶች የሚወስድ በመሆኑ፤ የትራንስፖርት አበሉ ለአምስት ቀን እንኳን ስለማይበቃ የኦዲት ስራውን በአግባቡ ለመከወን ግዴታ ከወር ደመወዝዋ በማንሳት ለትራንስፖርት እንደምታወጣ ትናገራለች።
በዚህም በተለይ በወሩ የመጨረሻ ቀናቶች ገንዘብ እንደሚያጥራት ገልጻ፤ ወደ ተለያዩ የፌዴራል ተቋማት በመሄድ መስራት የሚገባትን የቤት ስራ ከመስራት ይልቅ ቢሮ ላይ ጊዜዋን እንደም ታሳልፍ ትናገራለች።
በዚህም የተቋማቶቹ የግዥ አፈጻጸምና የንብረት አስተዳደር በወቅቱ ኦዲት ስለማይደረግ፤ የአገር ንብረትና ሀብት እንዲባክን መንገድ እየከፈተ መሆኑን ወይዘሪት ወንዜ ትገልጻለች።
በኤጀንሲው የኦዲትና ክትትል ጀማሪ ባለሙያዋ ወይዘሪት ማስተዋል ስሜነህ በበኩሏ፤ የፌዴራል ተቋማትን ኦዲት ለማድረግ በወር 75 ብር አሁን ባለው የትራንስፖርት ታሪፍ መሰረት ለወር ቀርቶ ለሳምንት የማይበቃ በመሆኑ፤ እንደ ስራ ባልደረባዋ ሁሉ ከወር ደመወዝዋ ለትራንስፖርት ወጪ እንደምታደርግ ትናገራለች።
አበሉ ስራዋን በአግባቡ መከወን እንዳላስቻላት የምትናገረው ባለሙያዋ፤ በተለይ በወሩ የመጨረሻ ቀናቶች እጇ ላይ ገንዘብ ስለማይኖር ወደ ተቋማቱ በማቅናት የኦዲት ስራዋን መከወን እንደማትችል ትገልጻለች።
በተጨማሪም በክልል የሚገኙ የፌዴራል ተቋማትን ኦዲት ለማድረግ ኦዲተሮች ወደ ክልል ከተሞች በሚሄዱበት ጊዜ በቀን የሚከፈላቸው የውሎ አበል በደመወዝ እርከን ለአንድ ባለሙያ ዝቅተኛው 111 ብርና ከፍተኛው ደግሞ 220 ብር በመሆኑ፤ ባለሙያዎች ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንደሚጋለጡ የሚናገሩት ደግሞ በኤጀንሲው የኦዲትና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ዘለቀ ታፈሰ ናቸው።
እርሳቸውም እንዳብራሩት፤ ኦዲት ለማድረግ በሚሄዱባቸው የክልል ከተሞች ለአንድ ቀን አዳር የአልጋ ክፍያ በአማካኝ 200 ብር መሆኑን ጠቁመው፤ ነገርግን ለአንድ ባለሙያ የሚታሰብለት የውሎ አበል ደግሞ ዝቅተኛው 111 ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 220 ብር ነው። ይህ የውሎ አበል አሁን በአገሪቱ ባለው የኑሮ ውድነት ለአንድ ቀን አዳር የአልጋ ክፍያ እንኳን የማይበቃ በመሆኑ፤ ሁሌም ወደ ክልል ከተሞች ባለሙያዎች ሲወጡ ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይዳረጋሉ።
በተለይ ደግሞ ሴት ባለሙያዎች እንደ ወንዶች አብዛኛውን ጊዜ አልጋ በጋራ ስለማይዙ የሚከፈላቸውን የውሎ አበል ለአልጋ ብቻ ከፍለው በባዶ ሆዳቸው ስራ የሚሰሩበት ሁኔታ በመኖሩ ችግሩ ለሴት ባለሙያዎች አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸው፤ ይህም አንድን ባለሙያ ስራውን በአግባቡ እንዳይሰራ ከማድረጉ ባሻገር ለሙስና የሚጋብዝ በመሆኑ፤ መንግስት ዘመኑ ያልዋጀውን የመንግስት ሰራተኞች የውሎ አበል መመሪያ ሊከልሰው እንደሚገባ ዳይሬክተሩ ያሳስባሉ።
ለትራንስፖርትም ሆነ ወደ ክልል ከተሞች ሲወጡ ለባለሙያዎች የሚታሰበው የውሎ አበል የዘመኑን የኑሮ ውድነት ያላገናዘበ በመሆኑ ባለሙያዎች መስሪያ ቤቶችን ተመላልሰው ኦዲት ለማድረግና በአግባቡ ስራቸውን በሄዱበት ከተማ ለመከወን የሚያስችል አለመሆኑን የሚናገሩት ደግሞ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ማርታ ሉይጂ ናቸው።
እርሳቸውም በተደረገ ጥረት የዋና ኦዲተሮች የትራንስፖርት አበል እንደተስተካከለ ጠቁመው፤ የባለሙያዎች የትራንስፖርት እና ወደ ክልል ከተሞች ሲወጡ የሚታሰብላቸው የውሎ አበል እንዲስተካከልላቸው ለሚመለከተው መስሪያቤት ጥያቄ መቅረቡን ይገልጻሉ።
ጥያቄው ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ ተቋሙ እጁን አጣጥፎ እንዳልተቀመጠ ዳይሬክተሯ ገልጸው፤ ችግሩን ለመቅረፍ ድጋፍ ከሚያደርጉ ድርጅቶች ጋር በመነጋገር ኦዲተሮች በመዲናዋ የሚገኙ የፌዴራል መስሪያ ቤቶችን ኦዲት ለማድረግ ሲዘዋወሩ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ሁለት መኪኖች በዚህ ወር በድጋፍ መገኝቱን ይጠቅሳሉ።
የሚከፈላቸው የትራንስፖርት አበል አነስተኛ ከመሆኑም ባሻገር ባለሙያዎች ታክሲ ተጠቅመው ስራቸውን በሚሰሩበት ወቅት ከአንዱ ታክሲ ወደሌላኛው ታክሲ በመውጣትና በመውረድ ስራቸውን ሳይሰሩ በመንገድ ጊዜያቸውን የሚያባክኑበት ሁኔታ መኖሩን ዳይሬክተሯ አውስተው፤ በመዲናዋ ኦዲተሮች ተቋማትን ኦዲት ለማድረግ ወደ ተቋማት በሚሄዱበት ወቅት አሁን ላይ በድጋፍ የተገኙትን እና ነባር የተቋሙን ተሽካርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ በማድረግ ባለሙያዎች ሳይወጡና ሳይወርዱ በወቅቱ ስራቸውን እንዲያከናውኑ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ።
ከሐምሌ 1 ቀን 2004 ዓ.ም ተግባራዊ በሆነው የውሎ አበል መመሪያ ፣ በዘጠኙ የክልል ዋና ከተሞች ዞን ወረዳ እና ቀበሌ እና እንዲሁም በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች የክልል መንግስት ሰራተኞች የቀን ውሎ አበል ዝቅተኛው 111 ብር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ 225 ብር ነው፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012
ሶሎሞን በየነ