-በዓመት አስራ ሁለት ቢሊዮን ብር መዋጮ እየተሰበሰበ ነው
አዲስ አበባ፡- በሀገሪቱ ለሚገኙ ሰባት መቶ ሀምሳ ሺ የሚደርሱ ጡረተኞች በዓመት ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚከፈል የመንግሥት ሠራተኞች ማህበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ገለጸ።የማህበራዊ ዋስትና ሽፋን ካላቸው ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች በአመት አስራ ሁለት ቢሊዮን ብር እየተሰበሰበ ነው፡፡
በኤጀንሲው የምዝገባና አበል መወሰኛ ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ እምሩ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት በአሁኑ ወቅት ለጡረተኞች የሚከፈለው አጠቃላይ ዓመታዊ ክፍያ ከስድስት ቢሊዮን ብር በላይ የደረሰ ሲሆን ዝቅተኛ ወርሀዊ ክፍያ 1ሺ 258 ብር ሲሆን ትልቁ ደግሞ 153 ሺ ይደርሳል ፡፡ ከፍተኛ የጡረታ አበል የሚከፈላቸው ዜጎች ቁጥር አነስተኛ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ ካፕቴኖች ይጠቀሳሉ ብለዋል፡፡
ኤጀንሲው በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የጡረታ ማስተካከያ የሚያደርግ መሆኑን የጠቆሙት ዳይሬክተሩ ፤ሆኖም ነባራዊ ሁኔታዎችን በመመልከት እንዳስፈላጊነቱ ማስተካከያ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሰራዊትንና ፖሊስ ሰራዊትን ሳይጨምር በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚሰሩና የማህበራዊ ዋስትና ሽፋን ያላቸው ሁለት ነጥብ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ያሉ ሲሆን ከእነዚህም አስራ ሁለት ቢሊዮን ብር በዓመት እየተሰበሰበ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
በአሰባሰብ ረገድ በአዋጁ ደመወዙ ከተሰጠ በኋላ በቀጣዩ ወር እስከ 30 ቀን ድረስ ገቢ መደረግ እንዳለበት፤ ይህ ካልሆነ አምስት በመቶና የባንክ ማስቀመጫ ቅጣት እንዳለ ቢቀመጥም አንዳንድ አሰሪ መስሪያ ቤቶች ክፍያውን በወቅቱ ባለመፈጸም መንግሥትን ለቅጣት የሚዳርጉ መኖራቸውንም ጠቁመዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንደተናገሩት ያለውን ተቀማጭ ብር ወደ ኢንቨስትመንት ለማስገባት እቅድ አለ። ነገር ግን የሚሰበሰበው ገንዘብ የአደራ በመሆኑና መንግሥት ለኤጀንሲው የሚሰጠው ብር ባለመኖሩ ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት ከፍተኛ ጥንቃቄ ይጠይቃል። ይህም ሆኖ አዋጭነቱ ሲረጋገጥ ወደ ኢንቨስትመንት ለመግባት የሚጠኑ ነገሮች ይኖራሉ ሲሉ ተናግረዋል ።
ዘጠኝ አይነት የማህበራዊ ዋስትና አይነቶች ቢኖሩም በኢትዮጵያ እየተተገበሩ ያሉት ግን አራቱ ብቻ ናቸው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አንደኛ በእድሜ፣ ሁለተኛ በጤና ምክንያት እና ሦስተኛ በስራ ላይ እያሉ በገጠመ ችግር በደራጎት የሚወጡና ባለመብቱ ሲሞት ለተተኪዎች የሚሰጥ፤ እናትና አባት ልጆች እንዲሁም የትዳር አጋርን የሚያካትት መሆናቸውንም አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012
ራስወርቅ ሙሉጌታ