• 127 ክሶች ለስነ ምግባር ኮሚቴ ቀርበዋል
አዲስ አበባ፡- ማህበረሰቡ ስለጤና ያለው ግንዛቤና እውቀት እያደገ በመሆኑ በጤና ሥነ ምግባር ችግር ምክንያት የቅሬታ አቅራቢዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አንድ ጥናት አመለከተ፡፡
የፌዴራልና ስነምግባር ጸረሙስና ኮሚሽን ከጤና ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር ትናንት ባካሄደው አገር አቀፍ አውደ ጥናት፤ በህክምና አሰጣጥ የሥነ ምግባር ጉድለት ደርሶብናል ብለው አቤቱታ ያቀረቡ ሰዎችን ቅሬታ መሰረት በማድረግ የተሰራ የሥነ ምግባር ጉድለት የሚያሳይ ጥናት ቀርቧል፡፡
ጥናቱን ያቀረቡት የልብ እና የሳንባ ማቀፊያ የቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትና የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር ምክትል ፕሬዚደንቱ ዶክተር ብርሃኑ ነጋ እንደገለጹት፤ በጥናቱ መሰረት በጤና ሥነ ምግባር ችግር ምክንያት የቅሬታ አቅራቢዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡
የህክምና ስህተት በሁሉም አገር ያለ፣ መጋነን የሌለበት ግን ሊታረም የሚገባው መሆኑን ጠቁመው፤ ችግሮች የሚፈጠሩት የአሰራር ሥርዓት ባለመዘርጋት፣ በአቅርቦት ችግር እና የህክምና ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ ተከታታይነት ያለው ስራ ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ችግሩ ቀድሞም የነበረ ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸው፤ የቅሬታ አቅራቢዎች ቁጥር መጨመር ማህበረሰቡ ስለጤና ያለው ግንዛቤና እውቀት መጨመሩንና ተጠያቂነት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡
እ.ኤ.አ ከ2011 እስከ 2017 የጤና ባለሙያዎች የአሰራር ሥርዓት ምን እንደሚመስልና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክቶ አጠቃላይ የዳሰሳ ጥናት መደረጉን አንስተዋል፡፡ በዚህ መሰረትም 127 ክሶች ቀርበው በፌዴራል ሥነ ምግባር ኮሚቴ መታየታቸውንና ከእነዚህ መካከልም 125 የሚሆኑት ላይ ውሳኔ መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
72 የሚሆኑት በሞት ምክንያት የቀረቡ ክሶች ሲሆኑ፤ 27 የሚሆኑት ደግሞ በአካል ጉዳት ምክንያት ክስ የቀረበባቸው ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ በተለያየ ዓይነት የሥነ ምግባር ጉድለት የተከሰሱ መሆናቸውንም ነው የጠቆሙት፤ 27 የሚሆኑት የሥነ ምግባር ጉድለት መፈጸማቸው በመረጋገጡ እርምት እንዲወሰድ ውሳኔ መተላለፉን ገልጸው፤ ከተከሳሾቹ መካከል 89 የሚሆኑት የሥነ ምግባር ጉድለት እንዳልተገኘባቸው ጠቁመዋል፡፡
አራት የሚደርሱ ተከሳሾችን ጉዳይ ለመመልከት ባለመቻሉ ወደ ጤና ቢሮ መመለሳቸውንና አምስት ተከሳሾች ጉዳይ ደግሞ ከወንጀል ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ ወደ ዐቃቤ ህግ ማስተላለፋቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከፍቃድ መሰረዝ በጊዜያዊነት ፍቃዳቸው እስከማገድ ቅጣት መተላለፉንም ገልጸዋል፡፡
የፌዴራልና ሥነምግባር ጸረሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ አታክልቲ ግደይ፤ ሙስና ኢ-ሥነምግባራዊና ራስን የማስቀደም ግለኝነት መገለጫ መሆኑን ተናግረዋል:: አገርን የሚጎዳ ድርጊት ነው ብለዋል፡፡ ድርጊቱ ከሞራል ዝቅጠት፣ ከሥነ ምግባር ጉድለት ጋር ጥብቅ ቁርኝነት ያለው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ባብዛኛው በመንግስት የሚቀርብ አገልግሎትን ባልተገባ መንገድ በመወሰን ህዝብን የማንገላታት ተግባር ነው ብለዋል፡፡ የህዝብን መሰረታዊ ጥያቄዎችንና ጥቅሞችን በመጉዳት ለችግር የመዳረግ ድርጊት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ ድርጊቱ ልማትን፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታንና ሰላም ማስፈንን የሚያደናቅፍና በመንግስትና በህዝብ መካከል አመኔታን የሚያሳጣ በመሆኑ በአጭር መቀጨት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የሥነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ከበደ፤ ስራውን አክባሪ የጤና ባለሙያ ለማፍራት የሚያስችል የግንኙነት መድረክ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የህክምና መሳሪያዎችና የመድሃኒት ችግርን ለመቅረፍ ዓለም አቀፍ ጨረታ ተደርጎ ከአሸናፊው ድርጅት ጋር የአንድ ዓመት ውል ተፈርሞ ወደ ተግባር መገባቱን አመልክተዋል፡፡ ህሙማን ያላግባብ የአልጋ ወረፋ እንዲጠብቁ የሚደረግበትን ሁኔታ ለመፍታት ከአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012
ዘላለም ግዛው