አዲስ አበባ፡- ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ የግድቡ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡
የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሮማን ገብረሥላሴ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በግድቡ ግንባታ በሚኖራቸው ሚና ላይ ያተኮረ ውይይት ትናንት ሲካሄድ የሕዳሴው ግድብ የመላ ኢትዮጵያውያን የጋራ ፕሮጀክት በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባላቸው እውቀትና ገንዘብ አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው በግድቡ ግንባታ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል፡፡
በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያሉ ፖለቲካዊ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው የዓባይን ጉዳይ የአገርና የልማት አጀንዳ አድርጎ መያዝና ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
እንደርሳቸው ገለፃ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች ኢትዮጵያ ግድቡን ለጋራ ተጠቃሚነት እየገነባች እንደሆነና የግድቡ ግንባታም ሌሎች አገራትን እንደማይጎዳ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም የግድቡን ግንባታ በልዩ ልዩ መልኮች ሲደግፉ እንደነበር አስታውሰው፣ ወደፊትም ድጋፋቸውን አጠናክረው መቀጠል እንደሚገባቸውም አሳስበዋል፡፡
በ2012 ዓ.ም እስካሁን ድረስ ለግድቡ ግንባታ 168 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማሰባሰብ እንደተቻለም ወይዘሮ ሮማን ጠቁመዋል፡፡
የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር ዶክተር አረጋዊ በርሔ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለግድቡ ግንባታ እስካሁን ያበረከቱት አስተዋፅዖ በሚፈለገው ልክ ነው ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን በማንቀሳቀስ ለግድቡ ግንባታ ትልቅ አስተዋፅዖ ማበርከት እንሚችሉ ገልጸው፣ ከዚህ በኋላ ፓርቲዎቹ በተደራጀ መንገድ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ግድቡን በተመለከተ የሚደረጉ ድርድሮች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲካሄዱም አሳስበዋል፡፡
ግንባታው በ2003 ዓ.ም የተጀመረው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአሁኑ ወቅት አጠቃላይ ግንባታው 70 ነጥብ አምስት በመቶ ደርሷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012 አንተነህ ቸሬ