• የመምህራንና የአስተዳደር አካላት ተሳትፎ እንዳለበት ተጠቆመ
አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ የአገራችን ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታዩ አለመረጋጋቶችን ለፖለቲካ ፍጆታቸው የሚያውሉ ኃይሎች ጠንክረው እየሠሩ መሆኑን የሣይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ገለፀ:: የመምህራንና የአስተዳደር አካላት ተሳትፎ እንዳለበትም ተጠቆመ፡፡
በሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደቻሳ ጉርሙ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በዩኒቨርሲቲዎች ካለው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ይዘው በተቋማቱ የሚንቀሳቀሱ ተማሪዎች፣ የሠው ሕይወት ያጠፉና በተመሳሳይ ድርጊት ተጠርጣሪ የሆኑ አካላት በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ የፌዴራል ፖሊስም ጉዳዩን እየመረመረና መረጃዎችን እያደራጀ በመሆኑ በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ይሆናል።
ዳይሬክተሩ ፤ ያለመረጋጋትና ችግሮች እየተስተዋሉ ያሉት በአማራ፣ ኦሮሚያና ድሬዳዋ አስተዳደር በሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ መሆኑን ገልጸው፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በከፊል፤ ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል፡፡ ‹‹በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ላይ ችግር አለመፈጠሩ መልካም ቢሆንም ለምን በሁለቱ ክልሎች ላይ ብቻ አለመረጋጋቱ ሊነግስ ቻለ?›› የሚለው ጉዳይ ጥያቄንም ያጭራል ብለዋል፡፡
ተማሪው በአገሪቱ ፖለቲካ ላይ ተገቢውን ጥያቄ ማንሳቱ ትክክል መሆኑ ባይካድም በተቋማቱ የሚፈጠሩ ግጭቶች ግን የብሔርን ብሎም የሃይማኖትን መልክ እንዲይዙ መደረጋቸው ከጀርባ ሌላ አካል እንዳለ አመላካች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ስውር አጀንዳን ለተማሪዎቹ አስይዞ የሚልከው ኃይል ማንነት ለመጥቀስ አዳጋች ነው፤ በአንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ግን በእኩይ ድርጊቱ ተሣታፊ የሆኑ መምህራንና የአስተዳደር አካላት መኖራቸው ለችግሩ መባባስ ተጠቃሽ ምክንያት ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
መንግስት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶችን ቢያደርግም፣ የመፍትሔ እርምጃዎችን ቢወስድም የሚጠበቀው ለውጥ አልመጣም፡፡ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በ 22 ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ላይ ባጋጠመ አለመረጋጋት የ10 ሠዎች ሕይወት አልፏል፤ በአካልና በንብረት ላይም ውድመት ደርሷል ሲሉም ሃላፊው ተናግረዋል፡፡
በተቋማቱ የሚስተዋለው ችግር የመለወጥን ተስፋ አንግበው የሚንቀሳቀሱ ትውልዶችን የቀጠፈ፣ ለአካል ጉዳት የዳረገ ብሎም ቤተሰብና አገር የለውጥ መሠረት ያደረጓቸውን ተማሪዎች ወደ የመኖሪያ ቀያቸው ሻንጣቸውን አስይዞ የመለሰ በመሆኑ ሁሉም በትኩረት ሊያጤነው ይገባል፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም በአሁኑ ወቅት ተቋማቱ ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸው እንዲመለሱ በተለይም ችግሮቹ በሚስተዋልባቸው የአማራና ኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን ጠቁመዋል ፡፡
የተረጋጋ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማምጣት የተማሪዎችን፣ የተቋማቱ አስተዳደርን፣ የአካባቢውን ማህበረሰብና በአጠቃላይ የትምህርት ዘርፉን ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንደሚጠይቅ ዳይሬክተሩ አመላክተዋል::
ከሕዳር 29 እስከ ታኅሳስ ስድስት ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ በአገሪቱ የሚገኙ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በፌዴራል ፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግላቸው፤ የተማሪዎች መግቢያና መውጪያ ሰዓት ገደብ እንዲጣልበት መደረጉ ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012
ፍዮሪ ተወልደ