• የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜ ጨምሯል
አዲስ አበባ፡- የገና በዓልን በላልይበላ ከተማ ለማክበር ወደ ከተማዋ የሚገቡ እንግዶችን ለመቀበል የሚያስችል በቂ ዝግጅት ማድረጉን የላልይበላ ከተማ አስተዳደር ገለጸ። የከተማዋ የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜ መጨመሩም ተጠቆመ፡፡
የከተማዋ ምክትል ከንቲባ እና የትምህርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማንደፍሮ ታደሰ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ከተማ አስተዳደሩ የገናን በዓል በሰላም ለማክበር የሚያስችል በቂ ዝግጅት አድርጓል። የኢየሱስ ክርስቶስ እና የንጉሥ ቅዱስ ላልይበላ የልደት በዓል በተመሳሳይ ቀን (ታኅሳስ 29) ተከብሮ ስለሚውል፤ የአገር ውስጥና የውጭ አገራት ጎብኚዎች በብዛት ወደ አካባቢው ይገባሉ። በመሆኑም ከተማ አስተዳደሩ በዓሉን ለማክበር የሚመጡ እንግዶቿን ተቀብሎ ፍጹም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማክበር የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት አድርጓል።
እንደእርሳቸው ገለፃ፣ የቅድመ ዝግጅት ስራው በአንድ አብይ እና በሰባት ንዑሳን ኮሚቴዎች እየተመራ ተከናውኗል፡፡ በከተማዋ እየተሰራ ባለው የመንገድ ፕሮጀክት ምክንያት መንገዶች በመቆፋፈራቸው መንገዱን ለመኪናና ለእግረኞች አመች ለማድረግ የመደልደል ስራ ተሰርቷል፡፡ እንግዶች በሚያርፉባቸው አካባቢዎች የመብራትና የውሃ አገልግሎት እንዲያገኙ የኤሌክትሪክና የቦኖ ውሃ መስመር ዝርጋታ ተከናውኗል፡፡
ከጽዳትና አካባቢ ጥበቃ ጋር በተያያዘም የመንግስት ሰራተኛውን ጨምሮ የከተማዋ ነዋሪ የተሳተፈበት የሶስት ቀናት የዘመቻ ጽዳት ስራ ተሰርቷል ያሉት ምክትል ከንቲባው፤ ከገጠራማ አካባቢዎች ለሚመጡ እንግዶችም ጊዜያዊ የመጸዳጃ ቤቶች መገንባታቸውን እንዲሁም በከተማዋ የሚገኙ የጤና ተቋማትም ለበዓሉ የ24 ሰዓት አገልግሎት እንዲሰጡና እንግዶች በሚበዙባቸው አካባቢዎች ደግሞ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ የሚሰጡ ባለሙያዎች ተዘጋጅተዋል ብለዋል።
‹‹የከተማዋ ወጣቶች ለበዓሉ የሚመጡትን እንግዶች እግር አጥበው፣ ስመውና የሚበላ ምግብ አቅርበው የመቀበል ወርቃማ ባህል አላቸው፡፡ ይህን ወርቃማ ባህል ከአሁን በፊት ወጣቶቹ በተበጣጠሰ መልኩ በየመንደሩ ያደርጉት የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ሰባት ኮሚቴዎች ያሉት የወጣት ጥምረት ተደራጅቶ በተቀናጀ መልኩ ሀብት በማፈላለግ እንግዶችን ተቀብሎ የማብላትና እግር የማጠቡን ተግባር ለመከወን ወጣቶች ዝግጅታቸውን ጨርሰዋል›› ብለዋል።
ኃላፊው የእድር ጥምረቶችም በየዓመቱ ከታህሳስ 24 ቀን ጀምሮ ለበዓሉ ታዳሚዎች ምግብ በማቅረብና በዓሉ ሲፈሰክ ደግሞ ፍሪዳ አርደው እንግዶችን ጾሙን የሚያስገድፉበት ልማድ እንዳለ ገልጸው፤ እነዚህ የእድር ጥምረቶች ዘንድሮም እንግዶችን በመልካም ሁኔታ ተቀብሎ ለመሸኘት የቅድመ ዝግጅት ስራ መስራታቸውን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ እንግዶች ክብረ በዓሉን በሰላም አክብረው እንዲመለሱ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር ውይይት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ የከተማው ነዋሪም የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት እንዲጠብቅ በየአደረጃጀቱ ውይይት እንደተደረገም ጠቁመዋል። ከዚህ በተጨማሪ ከተማ አስተዳደሩ ክብረ በዓሉ በሰላም እንዲጠናቀቅ የአድማ ብተና፣ መደበኛ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና በክብር የተመለሱ የመከላከያ ሰራዊት ተመላሽ ወታደሮች የተካተቱበት የጸጥታ አባላትን እንደሚያሰማራ ገልጸዋል፡፡
ላልይበላ ፍጹም ሰላማዊ የሆነ እንቅስቃሴ ያለባት በመሆኗ ማንኛውም ጎብኚ ያለምንም የጸጥታና የደህንነት ስጋት ወደ ከተማ መምጣት እንደሚችል የተናገሩት አቶ ማንደፍሮ፣ የእንግዶችን ደህንነት የበለጠ አስተማማኝ ለማድረግ በመግቢያና በመውጫ መንገዶች ላይ ማንኛውም ሰው ተፈትሾ እንደሚወጣና እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በከተማዋ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ፍሰት እንዲጨምር ከከተማ አስተዳደሩ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያንም ቅስቀሳ እያደረገች መሆኑን ጠቁመው፤ ዘንድሮ ከ600ሺ በላይ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ወደ ከተማዋ ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና ከተማዋም አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር ገቢ እንድታገኝ እቅድ መያዙን አቶ ማንደፍሮ ተናግረዋል።
የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ስፖርት ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሪጌታ መልካሙ አለሙ በበኩላቸው፣ የከተማዋ የቱሪስት ፍሰትና የቆይታ ጊዜ መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ ቀደም ሲል የነበረው አማካይ የቱሪስት የቆይታ ጊዜ አንድ ቀን የነበረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ግን ከሶስት እስከ አራት ቀናት እንደሆነ ጠቁመዋል።
እንደ ኃላፊው ገለፃ፣ በ2008 እና በ2009 ዓ.ም በድምሩ 60 ሺህ ቱሪስቶች ከተማዋን የጎበኙ ሲሆን፤ በ2011 ዓ.ም 55 ሺ ቱሪስቶች ከተማዋን ጎብኝተዋል። በተያዘው በጀት ዓመት 65 ሺ የውጭ ጎብኚዎች ከተማዋን ይጎበኛሉ ተብሎ የታቀደ ሲሆን፤ እስከ ታህሳስ 10 ቀን 2012 ዓ.ም ድረስ 32ሺ ቱሪስቶች ከተማዋን ጎብኝተዋል።
ከመስከረም እስከ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ዝቅተኛ የቱሪስት የፍሰት ቁጥር የሚመዘገብበት ጊዜ ቢሆንም በዚህ ወቅት የእቅዱን ግማሽ ያህሉን ማሳካት ተችሏል፡፡ ከታህሳስ እስከ ግንቦት መጨረሻ ደግሞ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የሚመዘገብበት ወቅት ስለሆነ የጎብኚዎች ቁጥር ከተያዘው እቅድ በላይ ሊጨምር እንደሚችል አመልክተዋል።
የከተማዋ የቱሪስት ፍሰትና የጎብኚዎች የቆይታ ጊዜ እንደጨመረ የሚናገሩት መሪጌታ መልካሙ፤ ይህም ለወጣቱ የስራ እድል እየተፈጠረለት እንደሆነ ገልጸዋል። የአብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ የሆቴሎችና በቱሪዝም ዘርፍ የተሰማሩ አካላት ገቢ እየጨመረ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012
ሶሎሞን በየነ