• የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር አነስተኛ ነው
አዲ አበባ :- የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እኤአ በ 2016/17 ያጠናው አገር አቀፍ ጥናት እንደሚያሳየው ኢትዮጵያ ለምርምር ስራ መመደብ ያለባትን ያህል በጀት እየመደበች አለመሆኑን አመላክቷል። በአገሪቱ የሴት ተመራማሪዎች ቁጥርም አነስተኛ መሆኑን ገልጿል።
በኢንስቲትዩቱ የመረጃ አደረጃጀትና እውቀት አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ቃልኪዳን ተሾመ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ህብረት አባል አገራት እአአ በ2010 ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት አንድ በመቶውን ለጥናትና ምርምር ተግባራት ፈሰስ ለማድረግ ቃል የገቡ ቢሆንም፤ ኢትዮጵያ ግን ለጥናትና ምርምር ስራ መመደብ ያለባትን በጀት እየመደበች አይደለም።
ዳይሬክተሩ እንዳብራሩት፤ ጥናቱ በአራት ሴክተሮች (በመንግስት ተቋማት፣ በዩኒቨርሲቲዎች፣ በቢዝነስ ተቋማትና ለትርፍ ባልተቋቋሙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች) ላይ በአገር አቀፍ ደረጃ ትኩረት አድርጎ በየሁለት ዓመቱ ይጠናል ፤ እአአ በ 2016/17 የተጠናው ጥናት እንደሚያሳየውም ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ ሃገራዊ ምርት አንድ በመቶ ለጥናትና ምርምር ስራ መመደብ ቢጠበቅባትም፤ መፈጸም የቻለችው 0 ነጥብ 27 በመቶ ወይም አምስት ቢሊዮን ብር ገደማ ነው።
ይህም አገሪቷ ካስቀመጠችው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ግብ እንዲሁም ለዘርፉ መመደብ ከነበረባት ግማሽ እንኳን መድረስ አለመቻሉን ጥናቱ እንዳሳየም አብራርተዋል።
አገሪቷ ለምርምርና ልማት ተግባራት ካወጣችው ወጪ 66 በመቶ የሚሆነው በመንግስት የተሸፈነ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 28 በመቶ የሚሆነውን ወጪ ያደረጉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶች ናቸው። በመሆኑም መንግስትና ሌሎች በግሉ ዘርፍ የሚገኙ ሴክተሮች በምርምር ስራ ላይ ትኩረት አድርገው እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅባት ጥናቱ ማሳሰቡን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ጥናቱ በጾታ እና በትምህርት ደረጃ ያለውን ልዩነት ሲያስቀምጥ አገሪቷ ካሏት 31ሺ 172 ተመራማሪዎች ውስጥ ስድስት ሺ 363 ወይም ደግሞ 20 በመቶ የሚሆኑት ሴት ተመራማሪዎች ሲሆኑ፤ ቀሪዎቹ 80 በመቶ ደግሞ ወንዶች ናቸው፤ ይህ ሁኔታ የሴት ተመራማሪዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ መሆኑን ያመላክታል ብለዋል።
ከሴትና ከወንድ ተመራማሪዎች ምን ያህል በምርምር ስራ ላይ ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ የሚለው በጥናቱ መዳሰሱን የተናገሩት ዳይሬክተሩ ፤በዚህም ሴቶች ከወንዶች በተሻለ ትኩረት ሰጥተው በስራው ላይ ጊዜያቸውን እንደሚያሳልፉ በጥናቱ መመላከቱን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ከመሪ እስከ ድጋፍ ሰጪዎች ድረስ ያሉት አብዛኞቹ ተመራማሪዎች እድሜያቸው ከ 25 እስከ 34 ዓመት ሲሆን፤ ከ31ሺ 172 የምርምር ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ሲሆኑ፤ከእነዚህ ውስጥ 49 በመቶ ጥናታቸውን የሚያከናውኑት በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ነው።
ለምርምር ስራ ከፍተኛ ወጪ የወጣውም በዚሁ ዘርፍ ሲሆን፤ በዘርፉ የተሰሩ የጥናትና ምርምር ስራዎች 32 በመቶው የሚሆነውን በጀት መውሰዳቸውን ጥናቱ እንደሚያሳይ ተናግረዋል።
በአጠቃላይ አገሪቷ በምርምር ስራዎችና ተያያዥ ተግባራት ላይ ምን ያህል ወጪ እያደረገች እንደሆን ለማየት የተጠናው ጥናት አጠቃላይ ሀገራዊ ምርት ባደገ ቁጥር ለምርምር ስራዎች የምታወጣውን ወጪ በዚያው መጠን በማሳደግና አንድ በመቶውን ለጥናትና ምርምር ለማዋል የገባችውን ቃል መጠበቅ እንዳለባት ጥናቱ እንደሚመክር ዳይሬክተሩ አስሳበው፤ ይህንን ማድረግ ከተቻለ የሚሰሩ ስራዎች በጥናትና በምርምር እየተደገፉ ውጤታማ ይሆናሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 22/2012
ሶሎሞን በየነ