አዲስ አበባ፡- ከአርባ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የወጣበት የአምባሳደር መናፈሻ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆን የአዲስ አበባ ከተማ የተፋሰስና አረንጓዴ አካባቢዎች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ አስታወቀ::
የኤጀንሲው የልማት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሰመረ ብርሃኑ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የመናፈሻው የመልሶ ማልማት ስራ በ2010 ዓ.ም መጨረሻ ነው የተጀመረው::
ፕሮጀክቱን በስምንት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ታስቦ የነበረ ቢሆንም፣ ከዲዛይን ጋር በተያያዘ የተፈጠሩትን መጠነኛ ችግሮች ለመፍታት ግንባታው ተጨማሪ ጊዜ ጠይቋል::
ግንባታውን ለማጠናቀቅ ተጨማሪ አምስት ወራት መውሰዱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት የግንባታው 90 በመቶ የሚሆነው መጠናቀቁንና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለህዝብ ክፍት እንደሚሆን ጠቁመዋል:: መናፈሻው ውስጥ የተሰሩ ስራዎችም ጥራታቸውን የጠበቁና የመናፈሻ ስራዎችን ስታንዳርድ የሚያሟሉ መሆናቸውንም አብራርተዋል::
በመናፈሻው ግንባታ ሂደት ችግሮች ማጋጠማቸውን ጠቅሰው፣ ከእነዚህም አንዱ በመናፈሻው ይዞታ ስር የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች አለመነሳት መሆኑንም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል::
የኤጀንሲው ይዞታ ማስከበር ክፍል በተደጋጋሚ ለክፍለ ከተማውና ለከተማ አስተዳደሩ ጉዳዩን በማሳወቅ የቀበሌ ቤቶቹ ከቦታው እንዲነሱ ጥያቄ ማቅረቡንም አስታውቀው፣ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝም በኤጀንሲው በኩል አሁንም ግፊቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል::
እንደ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ተቋራጩ የገዛው ትራንስፎርመር እንዲገጠም ለማድረግ ኤጀንሲው ከኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር እየሰራ ነው:: የተዘረጋውን የውሃ መስመር አቅም ለማሳደግ ለከተማዋ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ጥያቄ ቀርቦ ምላሽ እየተጠበቀ ይገኛል::
ግንባታውን እያካሄደ የሚገኘው የናይት ቢዝነስ ግሩፕ ስራ ተቋራጭ የግንባታ ሳይት ፕሮጀክት ማናጀር አቶ አስክንድር አሰፋ እንደገለፁት ፤ፕሮጀክቱ አስራ አንድ ወራትን ወስዷል፤ የክረምት ወቅት ፣ የዲዛይን ችግሮችና የእቃዎች ግዢ ሂደት ለግንባታው መጓተት ምክንያት ናቸው::
በመናፈሻው ይዞታ ስር የሚገኙ የቀበሌ ቤቶች እስካሁን አለመነሳትም በፓርኩ መልሶ ግንባታ ሂደት ላይ ተጨማሪ መዘግየት እንዲፈጠር አድርጓል::
መናፈሻው በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ የልጆች መጫወቻ ስፍራ፣ አነስተኛ ካፌዎች፣ መጻህፍት ቤቶች፣ ልዩ ልዩ ሱቆች፣ ምግብ ቤቶችና በአንድ ጊዜ ሰባ የሚሆኑ ሰዎችን ሊያስተናግድ የሚችል የመሰበሰቢያ ቦታም እንዲኖረው ተደርጎ መገንባቱን አብራርተዋል:: ሰዎች እያነበቡ እረፍት የሚያደርጉባቸው አገልግሎቶችን ብቻ የሚሰጥ መሆኑንም ተናግረዋል::
ከኤሌክትሪክ ስራዎች ውጪ የውሃ ዝርጋታን ጨምሮ የፋውንቴንና ሌሎች የፊኒሺንግ ስራዎች መጠናቀቃቸውንም ጠቅሰው፣ አስካሁንም ግንባታው ከአርባ ሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ገንዘብ እንደፈጀም አመልክተዋል:: ቀሪ የፊኒሺንግ ስራዎች ከተጠናቀቁ በኋላ ፓርኩ በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆንም ማናጀሩ ጠቁመዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2012
አስናቀ ፀጋዬ