ነቀምት፡-የምስራቅ ወለጋ ዞን ወጣቶችን በተለይ ህዝቡን በአጠቃላይ በላቀ ሁኔታ ይጠቅማሉ በሚል ተስፋ የተጣለባቸው በፌዴራል መንግስትና በክልል ደረጃ ሊሰሩ የታቀዱ ፕሮጀክቶች ግንባታ መጓተት በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን የዞኑ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አስታወቁ::
ምክትል ዋና አስተዳዳሪው አቶ አስመራ ኢጃራ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ፕሮጀክቶቹ በርካታ ሲሆኑ፣ ከእነዚህም መካከል የማንጎ መጭመቂያ ፋብሪካ፣ የብረት ማቅለጫ ፋብሪካ፣ የኢንዱስትሪ ፓርክና የመንገድ ፕሮጀክቶች ተጠቃሾች ናቸው::
ለስራ አጥ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠሪያ እንዲሆን ታስቦ በክልል ደረጃ በ2009 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የማንጎ መጭመቂያ ፋብሪካ እስካሁን ግንባታው እንዳልተጀመረ ጠቅሰው፣ወደ 90 የሚጠጉ ስራ አጥ ወጣቶች የቢዝነስ እቅድና የንግድ ፈቃድ ጭምር አውጥተው የፋብሪካውን ግንባታ ቢጠባበቁም ጠብ ያለ ነገር እንዳላገኙ ተናግረዋል::
በሜቴክ ግንባታው የተጀመረው የብረት ማቅለጫ ፋብሪካም የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠለት ከአስር ዓመት በላይ እንደሆነው አቶ አስመራ አስታውቀዋል:: በየጊዜው እየመጡ የሆነች ነገር ሰርቶ ከመመለስ በስተቀር ግንባታው በየዓመቱ ምንም ያሳየው ለውጥ አለመኖሩን አመልክተዋል::የዚህም ግንባታ አንድም ታሳቢ ያደረገው የስራ አጡን ቁጥር መቀነስ እንደሆነ አብራርተዋል::
ምክትል ዋና አስተዳዳሪው እንዳሉት፤250 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ የኢንዱስትሪ ፓርክ ይገነባል ተብሎ ሂደቱ በ2009 ዓ.ም ተጀምሯል፤ግንባታው ከሚካሄደበት ቦታ ላይም አርሶአደሮች ካሳ ተከፍሏቸው እንዲነሱ ቢደረግም፣እስከ አሁን ግን የታየ ለውጥ የለም::
አካባቢው ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ግብዓት የሚሆን ሰብልም ሆነ የአልባሳት ጥሬ እቃ፣ በቂ መሬት እንዲሁም ምቹ የአየር ፀባይ አለ:: ኢንዱስትሪው ቢገነባ ወለጋን ብቻ ሳይሆን ቤኒሻንጉልንም ጨምሮ የምዕራቡን ኮሪደር ተጠቃሚ ማድረግ የሚችል ሲሆን፣ መንግስትም በዚህ መልኩ አቅዶ ነው ወደ ስራው የገባው::
የኢንዱስትሪ ፓርኩ መዘግየት እንደታየበት አቶ አስመራ ተናግረው፣ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ በ2011 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ላይ በአካባቢው ተገኝተው ከህዝቡ ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ‹ግንባታውን እናፋጥናል› ሲሉ በሰጡት ምላሽ መሰረት ለውጥ ይኖራል በሚል ህዝቡ አሁንም እየጠበቀ እንደሚገኝ አስታውቀዋል::
ግንባታቸው ከተጓተተው ፕሮጀክቶች መካከል በፌዴራልም ሆነ በክልል ደረጃ የሚሰሩ መንገዶችም ይገኙበታል ያሉት ምክትል አስተዳዳሪው፣በተለይ በፌዴራል መንግስት የሚሰሩ መንገዶች በጣም የሚዘገዩ መሆናቸው በጥናት መረጋገጡን አስታውቀዋል::ለእዚህም በ2008 ዓ.ም መጨረሻ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠለት የቡሬ ነቀምት መንገድ ግንባታን ለአብነት ጠቅሰዋል::
አቶ አስመራ እንደተናገሩት፤በክልል ደረጃ የሚሰራና በ2004 ዓ.ም የተጀመረ ወደ ዘጠና ኪሎ ሜትር የሚሆን ቢላ ዘንጊ ማለትም ከጉደያ-ቢላ-ጉተን የሚወስድ የመንገድ ፕሮጀክት አንድ ኪሎ ሜትር እንኳ እንዳልተሰራም ተናግረዋል::
በግንባታው መጓተት ዙሪያ በተከታታይ ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱን ጠቅሰው፣ ምላሽ ግን እንዳልተገኘ ገልጸዋል:: በፌዴራል ደረጃም የሚሰራው የነቀምት ከማሺ ዲዚያ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ጨረታ ወጥቷል ቢባልም እስካሁን ምንም አይነት ሂደት እንደሌለም ተናግረዋል::
ብዙዎቹ ፕሮጀክቶች አስርና አስራ አምስት ዓመት ያስቆጠሩና ምላሽም ያልተሰጣቸው መሆናቸውን ገልጸዋል:: በተለይ ከ2006 ዓ.ም ወደዚህ ያሉት በጣም የተጓተቱና በህዝቡ አቅም ሊሰሩ የማይችሉ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ክልሉም ተመልሶ ሊያየው እንደማይፈልግ እና የሕዝብና የመንግስት ሀብት የባከነባቸው ፕሮጀክቶች መሆናቸውን አብራርተዋል::
የኦሮሚያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው፤ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ የፈጠረው በመሰረተ ልማት ስም በየቦታው የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አለመጠናቀቃቸው እንደሆነ ተናግረዋል:: በመሆኑም መንግስት በተያዘው በጀት ዓመት የተጓተቱ እንደ መንገድ፣ ውሃ፣ መብራትና የመስኖ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 21/2012
አስቴር ኤልያስ