አዲስ አበባ፡- የተማሪዎች ምገባ መርሀ ግብር በአዲስ አበባ ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችና የተማሪ ወላጆች የስራ እድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ።
የትምህርት ቢሮው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ኃላፊው አቶ አበበ ቸርነት በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአዲስ አበባ በሁሉም የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከመዋዕለ ሕፃናት እስከ ስምንተኛ ክፍል ለሚማሩ ከ300 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ከጥቅምት ወር ጀምሮ የተማሪዎች ምገባ ተጀምሯል። እነዚህን ተማሪዎች የሚመግቡ እናቶችን በማደራጀት የስራ እድል ለመፍጠር ተችሏል።
‹‹ምገባው ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችና የተማሪ ወላጆች የስራ እድል የፈጠረ ነው።›› ያሉት አቶ አበበ፤ ወላጆች ለልጆቻቸው ምግብ የሚያወጡትን ወጪ ከመቀነስ ባሻገር ይህንን ስራ የሚሰሩት አነስተኛ ገቢ ያላቸው አካላት የተማሪ ወላጆች መሆናቸውን እና የገቢ ምንጭ በማግኘት ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
‹‹በምገባ ሂደት ላይ በርካታ ችግሮች አሉ። ተደራጅተው የምገባ አገልግሎት የሚሰጡት እናቶች ታክስ ይከፍላሉ። ይህ ደግሞ በስራው ላይ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል።›› በማለት ተናግረው፤ እናቶቹ በተደጋጋሚ ‹‹ታክሱ ይቅርልን›› የሚል ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አመልክተዋል።
በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች የመብራት አለመኖር፤ በመጋቢ እናቶች መካከል ተቀናጅቶ ያለመስራት፤ አልፎ አልፎ ሌሎችም የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመው፤ የመመገቢያና የማብሰያ ቦታዎች በቀጣይ በሚቋቋም ኤጀንሲ ክትትል እየተደረገ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ በተዘጋጀው መመሪያ መሰረት ምገባውን ይበልጥ ለማጠናከር ራሱን የቻለ ኤጀንሲ ለማቋቋም ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ወርቅነሽ ደምሰው