አዲስ አበባ፡- በህገ-መንግስቱ ላይ የፌዴራልና የክልል የዳኝነት አካላት ስልጣን ተጋርተው በውክልና እንዲሰሩ ቢደነገግም የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ተቀራርበው ባለመስራታቸው የዳኝነት ስርዓቱ ላይ ክፍተት መፍጠሩ ተገለፀ፡፡
የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ነዋይ በተለይም ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤትን ስልጣን በውክልና የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤቶች፣ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ስልጣን ደግሞ የክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ወይም የዞን ፍርድ ቤቶች በውክልና እንዲሰሩ ህገ- መንግስቱ ያዛል። ነገር ግን በዚህ መንገድ ተቀራርቦ ባለመሰራቱ የዳኝነት ስርዓቱ ላይ ክፍተት ፈጥሯል፡፡
የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች በየዓመቱ እየተገናኙ ክልሎች የፌዴራል ጉዳዮችን እንዴት እያስተናገዱ እንደሆነ እና ያጋጠሙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫ መቀመጥ እንዳለበት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 ውስጥ መካተቱን ተናግረዋል፡፡ በአዋጁ መሰረት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች ላለፉት 20 ዓመታት ተቀራርበው ባለመስራታቸው በዳኝነት አካሉ ላይ ሰፊ ክፍተት መፈጠሩንም አመልክተዋል።
እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለፃ፤ ክልሎች በውክልና ከሚሰሩት የዳኝነት አገልግሎት አንፃር በርካታ ችግሮች ነበሩ። ለአብነትም የፌዴራል ስልጣንን ክልሎች በውክልና ወስደው በሚሰሩበት ወቅት ክልል ላይ ያለው የዳኝነት አካል ተቀራራቢ የሆነ የህግ አተረጓጎም እንዲኖረው ይጠበቃል።
ነገር ግን ተከታታይነት ያለው ግንኝነት ባለመኖሩ በክልሎችም ሆነ በፌዴራል የዳኝነት አካላት መካከል ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርጓል። በተጨማሪም በዳኝነት ነፃነትና ገለልተኝነት ላይ የተለያዩ ተፅዕኖዎች ይደርሱ ነበር፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ፍሬህይወት አወቀ