አዲስ አበባ፡- ለ70 ሺ 748 የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አዲሱ የዲጂታል መታወቂያ እንደተሰጣቸው የወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ አስታወቀ።
በወሳኝ ኩነት ምዝገባና መረጃ ኤጀንሲ የነዋሪዎች አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ዳዊት በቀለ፤ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ከተማ በአስሩም ክፍለ ከተሞች እና በ60 ወረዳዎች የነዋሪዎች ምዝገባና አዲስ የዲጂታል መታወቂያ መስጠት ተጀምሯል።
በምዝገባ ሂደት የሲስተም (የኔትወርክ)ና የመብራት መቆራረጥ እንዲሁም በወረዳ ደረጃ ከፍተኛ የሰው ሀይል እጥረት በመኖሩ የተቀላጣፈ አገልግሎት መስጠት አልተቻለም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ አገልግሎቱን በሁሉም ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ለማዳረስ የግብዓት ዕጥረት፣ ምቹ አገልግሎት መስጫ ቦታ እንዲሁም ባለሙያዎች ባልተሟላባቸው ወረዳዎች ስራ አለመጀመሩን ገልጸዋል፡፡
ባለሙያዎች ባልተሟሉባቸው ወረዳዎችና ክፍለ ከተሞችም አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ እንዲቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጨምረው አብራርተዋል።
ወሳኝ ኩነት ምዝገባና ማስረጃ እንዲሁም የነዋሪዎች አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ከማዕከል እስከ ወረዳ እንዲወርድ በመደረጉ አገልግሎቱ በየደረጃው በማዕከል፣ በክፍለ ከተማና በወረዳ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ጽህፈት ቤት የሚሰጥ መሆኑ ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 20/2012
ወርቅነሽ ደምሰው