● የመረዋ – ሶሞዶ – ሶቃ – ሶሞዶ – ሊሙ መንገድ ግንባታ ተጀመረ
ጅማ፡- መስጊድና ቤተክርስቲያን ማቃጠል የጅማ ህዝብ ባህልም ሆነ ተግባር አይደለም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለጹ።የመረዋ – ሶሞዶ – ሶቃ እና ሶሞዶ – ሊሙ መገንጠያ መንገድ ግንባታንም አስጀምረዋል።
የመንገድ ግንባታውን ትናንት በጅማ ባስጀመሩበት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ እንደተናገሩት፤ መስጊድና ቤተክርስቲያን ማቃጠል የጅማ ህዝብ ባህልም ሆነ ተግባር አይደለም ።ስለሆነም የጥፋት ሀይሎች ተጨማሪ ጉልበት ባለመሆን የልማትና የአንድነት ተምሳሌት መሆን ያስፈልጋል ብለዋል።
አባ ጅፋር ከሌላ ብሔር ጋር ተዋልደው የኖሩ ናቸው፤ በመሆኑም ወጣቱ ይህን አርአያነታቸውን በመከተል በአካባቢው ከሚኖሩ የተለያዩ ብሔሮች እና ሀይማኖቶች ጋር በጋራ መስራት እንዳለበት መክረዋል። አካባቢው ውብና በልምላሜ የበለፀገው የታላቁና የብልሁን መሪ የአባ ጅፋር መርህና የሥራ ውጤቶች በመታየታቸው ነው።ስለሆነም
የአካባቢው ህዝብ ይህንን የልማትና የአንድነት ተምሳሌት የሆኑትን መሪ አርዓያነት ሊከተል እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመረዋ – ሶሞዶ – ሶቃ እና ሶሞዶ – ሊሙ መገንጠያ መንገዱ በጅማ አባ ጅፋር ቤተ መንግስት አቅራቢያ የሚያልፍ በመሆኑ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ፍሰት ለማሳደግ እንደሚያግዝ የተናገሩት ዶክተር አብይ ፤ የመንገዱ መገንባት በአካባቢው የሚመረተውን የቡና ምርት በዓለም አቀፍ ገበያ በተሻለ ፍጥነት ለማቅረብ ያስችላል ብለዋል ።
በተጨማሪም የአካባቢው ነዋሪ የተጀመረውን ልማት ከዳር ለማድረስ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር በመተባበር የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ፤የመንገዱ ግንባታ በግብርና ማቀነባበር ለተሰማሩ ባለሃብቶች ምርታቸውን ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል።
ለመንገድ ፕሮጀክቱ ከሁለት ቢሊዬን ብር በላይ ወጪ የሚደረግ መሆኑን የጠቀሱት ሚንስትሯ፤ የቁጥጥር ስራውን ጨምሮ ሙሉ ወጪው በኢትዮጵያ መንግስት ይሸፍናል።የመረዋ፣ ሊሙ ኮሳ እና ሊሙ ሰቃ ወረዳዎችን የሚያቋርጠው መንገድ 94 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በአራት ዓመት ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ገልጸዋል።
በመንገድ ግንባታ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልሉና የዞን ከፍተኛ አመራሮች ተገኝተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2012
ይበል ካሳ