● ሥራ ለማስጀመር ከ30ሺህ ዶላር በላይ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፡- ለቀድሞ ጣና በለስ ፕሮጀክት በ2007 ዓ.ም ለደለል ማውጫ የተገዛው ማሽን
ያለስራ ለአምስት ዓመታት ተቀምጦ ለብልሽት እየተዳረገ መሆኑን የጣና ባህር ትራንስፖርት ድርጅት ገለጸ። ማሽኑን ወደ ሥራ ለማስገባት ከ30ሺህ ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የጣና ሀይቅ ትራንስፖርት ድርጅት የጎርጎራ ወደብ የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ውበቱ ወርቅነህ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለፁት፤ የደለል ማውጫ ማሽኑን በ2007 ዓ.ም ከውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአደራ መልክ ቢቀበሉም እስካሁን ድረስ ሥራ ሳይጀምር ጸሀይና ዝናብ እየተፈራረቀበት ተቀምጧል። በወቅቱ ባለሙያዎችን የሚያሰለጥን አካል ልከን እንድትጠቀሙበት እናደርጋለን ቢባሉም እስካሁን ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳይደረግ ማሽኑ እየተበላሸ የተቀመጠበትን ወደብም እያፈራረሰ ይገኛል ብለዋል።
በከፍተኛ ወጪ የተገዛው የደለል ማውጫ ማሽን በባለሙያ ሲፈተሽ ማሽኑን ሊያንቀሳቅሰው የሚያስችሉ በርካታ መሰረታዊ እቃዎች የጎደሉት መሆኑን ለማረጋገጥ መቻላቸውን ጠቅሰዋል።እስካሁን ድረስም ምንም አይነት ሥራ ባለመስራቱና በየጊዜው እየተፈታ ባለመጠረጉ ለከፍተኛ ብልሽት እየተዳረገ መሆኑ እንዳሳሰባቸው ተናግረዋል። አሁንም ጉዳዩ የሚመለከተው የመንግሥት አካል እልባት እንዲሰጠው ሲሉ ገልጸዋል።
የቀድሞው የጣና በለስ ፕሮጀክት ሥራ አስተባባሪ የነበሩት እና በአሁኑ ወቅት በውሀ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ባዮ ጋዝ ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት የእቅድ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ አቶ ዳንኤል እሸቴ በቀረበው ቅሬታ ዙሪያ በሰጡት ምላሽ ለማሽኑ ግዥ አንድ ሚሊዮን ዶላርና ለተጓደሉ እቃዎች ማሟያ ግዥ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን ገልጸው ሆኖም ግን አሁንም ማሽኑን ሥራ ለማስጀመር ተጨማሪ ከ30 ሺህ ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የደለል ማውጫ ማሽኑ የተገዛው ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶበት ካሸነፈው የጣሊያን ድርጅት መሆኑን የተናገሩት አቶ ዳንኤል ሆኖም ግን ጨረታው በባለሙያና በእውቀት ያልተመራ በመሆኑ ችግሮቹ መፈጠራቸውን አስረድተዋል።
ድርጅቱ ኢትዮጵያ በዘርፉ እውቀት ያለው ባለሙያ እንደሌላት ስለተገነዘበና ተጨማሪ ቴክኒካል ክፍተቶችን ተጠቅሞ ያልተፈለገ እና ያልተሟላ ማሽን ማስገባቱን ጠቅሰዋል።በዋናነት ደግሞ ማሽኑ ደለሉን እየበጠበጠ ወደ ውጭ የሚስያተፋበት ፓምፕ የለውም ያሉት አቶ ዳንኤል ለመግዛት የተፈለገው በራሱ በመንሳፈፍ ስራ መስራት የሚችል ቢሆንም ድርጅቱ ያቀረበው በመርከብ እየተጎተተ የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተናግረዋል።ይህም ለተጨማሪ ሰባት ሚሊዮን ብር ወጪ ዳርጎናል ብለዋል።
ከግዥው ጀምሮ በርካታ ችግሮች እንደነበሩት ተናግረው፤ እንደዛም ሆኖ ማሽኑ ከመጣ በኋላ በቀጥታ ወደ ሥራ አለመግባቱ ትልቅ ኪሳራ መሆኑን ጠቅሰዋል።አሁን ማሽኑን ፈትሾና ባለሙያዎችን አሰልጥኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ተጨማሪ ከሰላሳ ሺ ዶላር በላይ ተጠይቋል።በዚህም የተነሳ ማሽኑ በጎርጎራ ወደብ ላይ ያለ ሥራ መቀመጡን አረጋግጠዋል።
አቶ ዳንኤል እንዳሉት በወቅቱ ያልፈለግነው ማሽኑ የመጣው በጨረታው ወቅት በዝርዝር መጠቀስ ያለበትን ዕቃ መግለጽ ባለመቻላችን መሆኑን በመገንዘባችን ድርጅቱን ከመክሰስ ይልቅ በድርድር ለመፍታት መርጠናል ብለዋል።በቀጣይ በጀት ዓመት ለሚመለከታቸው አካል በማሳወቅ ችግሩ እንዲፈታ በማድረግ ወደ ሥራ እንዲገባ ለማድረግ እየሰራን ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የጣና በለስ ፕሮጀክት ከተቋረጠ በኋላ የደለል ማውጫ ማሽኑን የጣና ባህር ትራንስፖርት ድርጅት ቴክኒካል ጉዳዩን እየተቆጣጠረው፤ የአባይ ተፋሰስ ፅህፈት ቤት ደግሞ እያስተዳደረው ይገኛል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2012
ሞገስ ፀጋዬ