አዲስ አበባ፡- በምልክት ቋንቋ አገልግሎት ለመስጠት የሚሰየመው ችሎት በባለሙያ የሚመራና የፍትህ ሥርዓቱን የተከተለ ባለመሆኑ አካል ጉዳተኞች ትክክለኛ ፍትህ እያገኙ እንዳልሆነ የኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር አስታወቀ።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ ወይዘሪት ትዕግስት አለማየሁ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ የፍርድ ሥርዓቱ የምልክት ቋንቋን ባህሪ በተረዳ መልኩ አይከናወንም። ዳኞችና ጠበቆችም በቋንቋው ተግባብተው እየሠሩ አይደለም። በዚህም ምክንያት መስማትና መናገር የማይችሉ ድምጹን ከፍ አድርጎ የማይናገር ሰው ምስክር አምጣ ይባላል። ይሄ ደግሞ አካል ጉዳተኛው ተገቢውን ፍትህ እንዳያገኝ አድርጓል።
ከሳሾች ሀሳባቸውን በአጭሩ አስረዱ፤ አትወራጩ በመባላቸው በምልክት ቋንቋ ሀሳባቸውን በግልጽ ለማስረዳት እንዳላስቻላቸው የሚናገሩት ሥራ አስኪያጇ፤ ሀሳባቸውን በጥልቀት ተረድቶና መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥ አካል እያገኙ እንዳልሆነና ችሎቱም ድንገተኛ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ከችሎቱ ተገቢውን ፍትህ እያገኙ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ዳኞች የሚረዱት አስተርጓሚ ማስፈለጉን እንጂ አገልግሎቱ እንዴት እንደሚሰጥ ባለመሆኑ መስማትና መናገር የተሳናቸው ዜጎች ጉዳያቸውን በአግባቡ ተረድተው አያስተናገዷቸው እንዳልሆነ አስረድተዋል።
በምልክት ቋንቋ በሚሰጠው የፍትህ መዛባት ለከባድ ችግር እየተዳረጉ ያሉት ክልሎች ላይ የሚገኙ አካል ጉዳተኞች መሆናቸውንም ገልጸዋል። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት የአስተርጓሚ ድጋፍ አለመጠየቁና በምልክት ቋንቋ የሚደረግ ችሎት ባለመኖሩ ነው። ስለሆነም መንግሥት ወሳኝ የሆኑ መብቶቻቸውን ማስጠበቅ እንደሚገባው አሳስበዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህርና ጠበቃ ረዳት ፕሮፌሰር አስቻለው አሻግሬ እንዳሉት፤ መስማትና መናገር የተሳናቸው ወገኖች የምልክት ቋንቋ የሚችል ባለሙያ ባለመኖሩ ያልተገባ ፍትህ ሊሰጣቸው አይገባም።
እስካሁን ትልቁ ችግር ያለው በምልክት ቋንቋ ፍትህ የሚፈልጉ ላይ ነው። ፍርድ ቤቶች በምልክት ቋንቋ አገልግሎት ስለማይሰጡ አካል ጉዳተኞች ተገቢውን ፍትህ እያገኙ አይደለም። በመሆኑም የሰለጠኑ ጠበቆችና ዳኞችን ማፍራት አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
“ሰው በፈለገበት ቋንቋ ሀሳቡን አስረድቶ ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያገኝ ህጉ ያዛል” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ሆኖም የምልክት ቋንቋን የሚጠቀሙ ዜጎች የዚህ መብት ተጠቃሚ አይደሉም። ስለሆነም መስማትና መናገር የተሳናቸው ዜጎች የራሳቸው ችሎት ሊሰየምላቸው ይገባል። ፍርድቤቶችም የምልክት ቋንቋን አሰልጥነው የፍርድ ስርዓቱን ማዘመን እንዳለባቸውም ተናግረዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የሬጅስትራር ተወካይ አቶ ሀብቴ ፍቻላ በበኩላቸው ፤መስማትና መናገር የተሳናቸው ወገኖችን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ሆኖም ግን በሁሉም ደረጃ ተሰርቶበታል ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል። በመሆኑም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል። በቀጣይ ህጉ ሲሻሻል ጉዳዩ የሚካተት ይሆናል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው