አዲስ አበባ፤- ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸውን 46 የማዕድን አለኝታ ቦታዎች ለመለየት እየሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ታምሩ መርሻ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት በ2012 በጀት ዓመት የሚለዩት የማዕድን አለኝታ ቦታዎችን ሰላሳ የደለል ወርቅ፣ አራት የብረት ማዕድን፤ ሰባት የኢንዱስትሪ ማዕድናት፤ አራት የጀምስቶን ማዕድናትና አንድ የድንጋይ ከሰል ማዕድን አለኝታ ቦታዎች ናቸው።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፤ ማዕድናቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚለዩ ሲሆን ይህም በዘርፉ በኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች መረጃ በመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል። ለሥራ ዕድል ፈጠራና ለውጭ ምንዛሬ ግኝት እንዲሁም የተቀዛቀዘውን የማዕድን ዘርፍ ለማነቃቃት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ጠቀሜታ ያላቸውን የማዕድናት የአለኝታ ቦታዎች በመለየት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ መሆኑም ጠቁመዋል።
የምርምር ፍቃድ ወስደው ጥናት ከሚያደርጉ ከአስራ አምስት ብረትና ብረት ነክ ማዕድናት፤ ከስድስት ኢንዱስትሪ ማዕድናት፤ ከአንድ የጌጣጌጥ እና ከአስራ ሦስት የድንጋይ ከሰል የግል ተቋማት ጋር በትብብር መሰራት ተጀምሯል።
የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በ2011 በጀት ዓመትም አስራ አንድ የደለል ወርቅ፣ አምስት ኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ አራት የብረት ማዕድን፣ አምስት የጀምስቶን ማዕድን እና አንድ የድንጋይ ከሰል በድምሩ 26 ማዕድናት የአልኝታ ቦታዎች ለይቶ ለፌዴራል መንግሥት እና ለክልሎች መረጃ መሰጠቱን አቶ ታምሩ አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 19/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ