ውድ አንባቢዎቼ! የዛሬውን ጽሑፌን የምጀምረው ቀጥሎ ባለው ምሳሌ ነው። በንባብ፣ እንዝለቅ፤ ‹‹ ዛፎች አንድ ጊዜ ንጉስ በላያቸው ላይ ለማንገስ ወጡ፤ ከዚያም በለስን በላያችን ላይ ንገስ አሉት። በለስም፣ ፍሬዬን ትቼ በእናንተ ላይ አልነግስም፤ ብሎ መለሰላቸው። ወይራን በላያችን ላይ ንገስብን አሉት። ወይራም ቅባቴን ትቼ በእናንተ ላይ አልነግስም ብሎ መለሰላቸው። በሶስተኛም ደረጃ ወይንን በላያችን ላይ ንገስብን አሉት። ታላቁ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ በገሪዛን ተራራ ላይ ቆሞ፤ ይሄን የሚናገረው የአቤሜሌክ ወንድም ኢዮአታም ነው። ወይንም ሰውን የሚያስደስተውን ወይን ጠጅነቴን ትቼ በእናንተ ላይ አልነግስም፤ ብሎ ሲመልስ ዛፎችም እሾህ ዘንድ ሄደው በላያችን ላይ ንገስብን አሉት። እሾህም ሳያንገራግር እንዳላችሁት ኑ፤ ከጥላዬ በታች ተጠለሉ። እምቢ ብትሉ ግን ከእኔ እሳት ወጥቶ ይብላችሁ ብሎ አላቸው። እነርሱም ተስማሙ።ይህ ቦታ የሚያስረዳው ነገር የሴኬም ሰዎች ወንድማችን ነው፤ ብለው ስላሰቡ እንዲመራቸው አጥንት ወደ መቁጠር ስጋ ወደ መመንዘር አስተሳሰብ ስለገቡ ወንድም ያነገሱ መስሎአቸው ነው፤ እሾህ በላያቸው ላይ ያነገሱት።ወንድሜም ቢሆን ፍሬ ከሌለው፣ ወንድሜም ቢሆን ሊመራኝ የሚያበቃው የመሪነት ባህሪ ከሌለው፣ በእኔ ላይ እንዲነግስ ስለምን ፈቅዳለሁ፤ ዘሬስ ቢሆን ቅባት ከሌለውና ቁስል የሚፈውስ ካልሆነ፣ ሆድ የሚሞላ እህል ከሌለው፤ ሀገር የሚመራ ሀሳብ ካጣሁበት፣ በአጥንት ቆጠራ በስጋ መረጣ እሾህን በላዬ ላይ የማነግስበት ምክንያት ምንድነው፤ ሲሉ መጠየቅ አግባብ ነው።አንዳንዴም መሪነት ጥያቄያቸው ላልሆኑ ሰዎች፤ ልባቸውም መንፈሳቸውም ትከሻቸውም ያንን ሃላፊነት ለመቀበል ላልተዘጋጁ ሰዎች በሰጠናቸው አደራ ሚዛን ተዛብቶ ስናገኝ ለምን እንቆጫለን። ለእሾሁ እንደሰጡት አደራ ፤ በምድራችን ለዚህ ጉዳይ ላልተዘጋጁ እንደ እሾህ ለሚዋጉ ሰዎች ታላቅ ስፍራ ሰጥተናቸው ታላላቅ ጥፋት ሲፈጽሙ ታይተዋል።ጀርመኖች፣ ሂትለርን በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ነው፤ ወደስልጣን ያመጡት። በወቅቱ ዓለምን ያናወጠው የኢኮኖሚ ግሽበት ነባሮቹን ፖለቲከኞች በስልጣኑ ማማ ላይ እንዳይቆዩ የሚያደርግ እውነታ ፈጥሮ ስለነበረ ሃገራቸው ጀርመንና በጥቅሉ አውሮፓ መድሃኒት በእጃቸው ሃሳብ በልባቸው የያዙ መፍትሔ ነገር ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋቸው ነበረ።ይህንን የሐገር የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የዋጋ ግሽበትና የብሩ መጠን የመግዛት አቅም መሬት ላይ ወድቆ የተንከሻከሸበት ዘመን ሂትለር ብሔራዊ ሶሻሊዝም፣ ማህበራዊ አፍርሶ ግንባታ ያስፈልጋል፤ ሲል የራሱን፤ ማኒፌስቶ ይዞ ወጣ። ታሪክ ይህንን የኋሊዮሽ ሲመረምረው፣ በአንደኛው ኣለም ጦርነት ወቅት ሃምሳ አለቃ የነበረውንና የገዛ ልብሱ እድፍ ለራሱ ቅር ያሰኘው የነበረውን ሰው ከትንሽ የሆቴል ውስጥ ዲስኩር አቅራቢነት ወደአደባባይ የሚያወጣ ድንገቴ ተፈጠረለት።
የናዚ ፓርቲን እየመራ ወደ አደባባይ ከመውጣቱ በፊት ሁለት ሶስቴ ሰልፍ ከማድረግ አልፎ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ሞክሮ ሁሉ ከሽፎበታል። በስተመጨረሻ “ትግሌ” የሚል መጽሐፍ ጽፎ ለንባብ አበቃ። ወደምርጫም ገባ፤ አሸነፈ። የችግራቸውንም ምንጭ በደምሳሳው፣ የአይሁዳውያን አልጠግብ ባይነትና በተዛባ የሃብት ክፍፍል ሳቢያ ምርጡና ከመለኮታዊ ዘር የሚመዘዘው ጀርመናዊነት ረክሶ በአደባባይ በመጣሉ ነው ሲል ነው የገለጸው። እንደማረጋገጫም ጌታ ኢየሱስን የገደሉትም እነርሱ መሆናቸውን አትርሱ ሲል ነው፤ “የሃሳቡን ማረጋገጫ” ለማስተንተን የሞከረው።ያኔ ታዲያ፣ የጀርመን ህዝብ በአስር ጣቱ መሲሃችንና የሀገራችን የትንሳኤ አባት እነሆ ተከሰተ። ኑና አብረን እናንግሰው ብለው አደባባዩን ጢም ብለው ወጥተው መረጡት፤ እርሱም ህጋዊውን መንግስት በሃይል ሊንድ በሞከረበት እጁ ጠላቴ የሚላቸውን ሁሉ አንድ በአንድ ከመንገዱ ላይ በሰበብ አስባቡ አስወገዳቸው። ግድያውን የጀመረው በዘመኑ የነበረውን ፓርላማ (እነርሱ ቡንደስታግ ይሉታል) አፈ ጉባኤ በመኪና አደጋ ሰበብ በመግደል ነው። ከዚያም ወዲያ ጭካኔና ስቃይ የተሞላበት ግድያ በምድሪቱ በህጋዊ መልክ ሽቅብ ጋለበ።ይህ ታላቅ አጥፊም 50 ሚሊየን ሰው ያለቀበትን የ2ኛውን የዓለም ጦርነት ቀሰቀሰ፤ በተለይም በቀደመ ቅስቀሳው በአውሮፓ ውስጥ ተሰባጥረው ይኖሩ የነበሩ፣ ስድስት ሚሊዮን አይሁዳውያንን አስጨፈጨፈ/ አጠፋ። ሃብትና ንብረታቸው ዘረፈ/አስዘረፈ። በርካታ ሃገሮችንም ወረረ። የሚገርመው ቼኮዝሎቫኪያን ሲወርር ምእራብ አውሮፓውያን፣ በስጦታ መልክ፣ ዝም ያሉት በዚያ ረክቶ ያበቃል፤ ከዚያም ነገሮች ይረጋጋሉ፤ ብለውም በማሰብ ጭምር ነበረ፤ ግን ከቼክ ወደ ፖላንድ፣ ከፖላንድ ወደ ፊንላንድና ሩሲያ ሲጓዝ ማቆም አልቻሉም። ከዚያ ይልቅ የእያዳንዳቸውን በር ሲያንኳኳ ነው፤ የባነኑት።
ወደ ቀደመ ነገራችን ልመልሳችሁና፣ የኢትዮጵያ ሰዎች በዚህ ሰሞን እንደ ሴኬም ሰዎች አጥንት እየቆጠሩ ስጋ እየመረጡ እሾህ በላያቸው ላይ ሊያነግሱ ድግስ እየጣሉ ነው። በመሰረቱ ለገዛ ወንድሞቹ ያልተመለሰ አቤሜሌክ ሰባዎቹን ድንጋይ ላይ አጋድሞ በማረድና በመግደል የጀመረ ሰው እንዴት በማብላት ይጨርሳል፤ ብለው ገመቱ።በማስፈራራት የጀመረን ሰው በማግባባት ይጨርሳል፤ በትግሉ ጊዜ ያኮሰሰን ሰው በድሉ ጊዜ ያከብረናል፤ በትግሉ ጊዜ ያዋረደን ሰው እንዴት በድሉ ጊዜ ከፍ ያደርገናል፤ ብለው እንዳሰቡ ያልታወቀ ነው።
የሚገርመው ወንድሙ ኢዮአታም የተናገረው ነገር እንደዚህ የሚል ነው፤ እሾህ በላያችን ይንገስ እንዳሉ ሊነግራቸው ፈልጎ እንደዚህ አላቸው “ እሾህንም ና፣ በላያችን ላይ ንገስ አሉት፤ እሾህም ኑና ከጥላዬ በታች ተጠለሉ አላቸው።” በየትኛው ጥላው ነው፤ እሾህ የሚያስጠልለው። በመሰረቱ ያለው እኮ ይቸራል እንጂ፤ አድርጉልኝ አይልም። እሾህ ጥላ የለውምና ! ለዚያውም በገዛ እጃቸው የሰጡትን ስልጣን ብትቀበሉኝ እሳት ከእኔ ወጥቶ ይብላችሁ አላቸው። የሚገርመው አጨራረሳቸው ነው። ራሳቸው፣ ያነገሱት አቤሜሌክ ጉድጓድ ቆፍረው ራሳቸውን እስኪደብቁ ድረስ አሳደዳቸው፣ ገደላቸው፣ አስጨነቃቸው፣ አረዳቸው፣ አጎሳቆላቸው። የሚገርመው በመጨረሻ እርስበእርስ ተባሉ። እንዲያውም የሞቱትን የሰባ ሰዎችን ንጹህ ደም በሴኬም ሰዎች እና በአቤሜሌክ ላይ እንዲፈርድ እርስ በእርስ ተጨራረሱ፤ በመካከላቸው ልዩነት ገባ። የአቤሜሌክ አሟሟት መጨረሻው አያምርም ነበረ፤ አንዲት ሴት የወፍጮ ድንጋይ አናቱ ላይ ጥላበት አንገቱ ተሰብሮ ነው የሞተው።
የሀገሬ ልጆች! የሰፈሬ ሰውም ቢሆን፣ ዘሬም ቢሆን፣ የኔ አይነት ቀለም ቢኖረውም፣ የኔን አይነት ቋንቋ ቢናገርም ለቁስሌ ፈውስ ቅባት፣ ለርሃቤ ማስታገሻ እህል ከሌለው፣ ከሁሉም በላይ የሚሰራ ሀሳብ ከሌለው፤ በአጥንት ቆጠራና በስጋ መረጣ በላዬ ላይ እሾህ የማነግስበት ምንም ምክንያት አይኖርም።በህግ አምላክ እሾህ አታንግሱብን!
በመሰረቱ ሰው ሃገርን ሆነ ተቋምን፣ ለመምራት ሀሳብና ክህሎት፣ ሲያጣ አጥንት ቆጠራ ውስጥ መግባቱን በዚህች እድሜና ዘመን አይተናታል። የሚገርመው ለመምራት ሞክሮ መውደቁ ሳይሆን ለመነሳት ከመሞከር ይልቅ የወደቀውና ያልተሳካለትም “ከዚህ ብሔር በመወለዴ የዚያኛው ብሄር ሰዎች መንገዴን አጥረውት ነው፤” ሲል መገኘቱ ነው። እንዴት ሰው፣ የሚመራውን ሃገር ይራገማል፤ እንዴትስ ሆኖ የሚመራውን ህዝብ፣ ያሳንሳል። ሰው ሀገር ለመምራት ራዕይ ሲያጣ፣ መላ ሲያጣ፤ ያፈጀ እና ያረጀ ታሪክ የስህተቱን ምክንያት በማድረግ፤ እዚያ ታሪክ ውስጥ፣ ፈልጉልኝ ይላል። ይህ በቤትም ውስጥ፣ በቤተ ዘመድም መካከል እንዲሁ ነው። ሰውን የሚያስተሳስርበት ገመድ በመምዘዝ ፈንታ የሚጠልፍበትና፣ የሚያቃቅርበት ገመድ ይጥላል። በትክክል አሁን በሃገሬ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ብዙ ሰዎች የሚታመሱበት ጉዳይ እንደ ሰኬም አይነት ጉዳይ ነው።አንድ ሰው ከተወለድክበት ዘር ስለሆነ እኮ፣ በአግባቡ ይመራሃል ማለት አይደለም። የአንተን ቋንቋ ይናገራል ማለት ለአንተ ይኖርልሃል ማለት አይደለም። አቀራረቡ ሊታይ “እጅህ ከምን” ሊባል ይገባል። ወቅቱን ያልጠበቀ ጊዜውን ያላገናዘበና የማያስኬድ ሃሳብ አዝሎ ለማራመድ መሞከር ከባድ የብረት ጠረጴዛን በጎርበጥባጣ ወለል ላይ ለመጎተት መጣር ነው። ያኔ አድዋ ላይ፣ አያቶቻችን ጣሊያንን በጋሻ እና በጦር ገጥመውታልና፤ ዘንድሮ እንደዚያው እናድርግ ብሎ መወሰን አይታሰብም፤ ቢታሰብም አያስኬድም፤ ዘበት ነው። ዘንድሮም ጣሊያንን በጋሻ እና በጦር እንገጥማለን ብሎ ቀረርቶማሰማት የማይሆን ሞኝነት ነው።
ወቅቱን ያልጠበቀ አስተሳሰብ እና አካሄድ ጥሩ አይደለም። አያራምድም፤ አይለመድም፤ ቢጣሩበትም አይሰማም።እውነት ብቻውን ይገድላል እንጂ አያድንም። እውነት ብቻውን ይፋጃል፣ እንጂ አያበርድም። መጽሀፍ ቅዱስ እንደሚናገረው እውነት በፍቅር ነው፤ የሚገለጸው። በፍቅር ያልተያዘ እውነት ደግሞ ከሚገነባው የሚያፈርሰው፣ ከሚሰበስበው የሚበትነው ይበልጣል።አንድ ማኪያቶ ለመጠጣት የሚያስብ ሰው ማኪያቶውን የሚይዘው በመያዣው በኩል እንጂ በሚፋጀው በኩል አይደለም ፤ እውነትም በምህረት ነው፤ የሚያዘው። እውነትና ምህረት ካልተዋደዱም ሃገር አያቆምም፤ እውነትና ምህረት ካልተስማሙ ህይወት አይቀጥልም።ፍቅር ማለት የእኔና የባልንጀራዬ ጥቅም ሲጋጩ የምንወስደው እርምጃ፣ የምንሰጠው ሩቅ ተመልካች ውሳኔ ነው። ባስከፋን ነገር ሁሉ፣ እኔና አንተ እኮ መባባል አርቆ አለማየት ነው።
ሶስት ልጆች የነበሩት አንድ አባት ጊዜ ሞቱ፣ ደረሰና ለልጆቹ ውርስ አደረገላቸው። ሶስታችሁም ተስማማታችሁ በዚህ ሃገር ያለውን ሀብቴን ሄዳችሁ፣ ተካፈሉ ሲል ነገራቸውና ጉዞ ጀመሩ።በመንገድ ላይም ረሐብ ጠናባቸውና አንዱን ወንድማቸውን ምግብ ገዝቶ እንዲመጣ ላኩት። ምግብ ሊያመጣ የሄደው በልቡ ሸር አደረበትና ሃብቱን ሁሉ ለብቻዬ ባስቀር የበለጠ ተጠቃሚ እሆናለሁ ብሎ አሰበና በሚገዛው ምግብ ውስጥ መርዝ ጨምሮ ይዞ መጣ።እነርሱ በበኩላቸው ሶስት ሆነን ስንካፈል የሚያንሰውን ሃብት ለሁለት ብንካፈል ብዙ ይሆንልናልና ትንሹ ወንድማችንን ሲመጣ አድፍጠን እንግደለው ብለው ተማከሩና አደረጉት። እርሱ ያመጣውንም ምግብ እየተሳሳቁ በልተው ሳይጨርሱ መርዙ ገደላቸው። አባት ያለትውልድ ቀረ፤ ወንድማማቾችም ያለፍቅር ተጋደሉ። ንብረት በሜዳ ላይ ባክኖ ቀረ፤ ይባላል።በህግ አምላክ፣ ሃገሪቱ ለሁላችንም ትበቃለች፤ በተለይ ራሳችንን ለመደገፍና ለማኖር የምንፍጨረጨር ሰዎች ለሌላ ሞት የምንደግስ አንሁን። ጉድጓድ ስትቆፍር አርቀህ አትቆፍር፤ ማን እንደሚገባበት አይታወቅም ይባላልና አስቡበት። የምንሄድበትን መንገድ በማስተዋል ብናደርገው ይመረጣል፤ ታላቁ መጽሐፍ በአልጋ ላይ ሳለህ መንገድህን ሰልል፤ ይላልና። ለጉዞ የሚዘጋጅ ሰው በጉዞው አቅጣጫ ስለሚያጋጥመው ነገር ቀድሞ ዝግጁ ከሆነና በእኔ ውስጥ ያለው ጨለማ በሌሎችም ሊኖር ይችላል ብለን በሰከነ አእምሮ መነጋገር ሁሉንምና ሁላችንንም ከማሳጣት ያድነናል። በሃገር ክፉ ሲመጣ የማይጎበኘው ቤት አይኖርምና።
በብዙዎች የታወቀ ምሳሌ ቢሆንም፣ ስለሁለቱ ሩቅ ተጓዥ ወንድማማቾች ታሪክ ልነግራችሁ እወዳለሁ። ሩቅ መንገድ እየተጓዙ ሳለ ታናሽና ታላቅ ባለመግባባት ተደባደቡና ክፉኛ ሃዘን ገባባቸው። በማግስቱ ትንሹ ልጅ በመንገዳቸው ላይ “ታላቅ ወንድሜ ትናንት ክፉኛ መታኝ” ብሎ ባጋጠመው አሸዋ ላይ ጻፈና ጉዟቸውን ቀጠሉ። በእኩለ ቀን ላይም፣ በመንገዳቸውም ላይ፣ ትልቅ ወንዝ ነበረና ታላቁ ወንድም ትንሹን ወንድሙን በጀርባው አዝሎ ወንዙን አሻገረው። ልክ ማዶ ተሻግረው ሲደርሱም ትንሹ ወንድም፣ በአለት ላይ፣ “ወንድሜ አደገኛውን ወንዝ በጀርባው ተሸክሞ አሳለፈኝ “ ሲል ጻፈ፤ ይባላል። ስለ አሸዋና ድንጋዩም ነገር፣ ታላቁ ታናሹን ሲጠይቀው፣ የሚያልፈውን ክፉ በአሸዋ፤ የማይረሳውን ደግ ነገር ደግሞ በአለት ላይ ማስቀመጤ ነው፤ ሲል መለሰለት።በዚህች ሃገር የተደረገብንን ክፉ ነገር በአዋራ ላይ፤ የተደረገልንን ደጋግ ነገር በልባችን ጽላት ላይ ጽፈን ትውልድ እንዲያውቀው እናደርጋለን እንጂ ርግማንና ዕዳ ለትውልድ አናቆይም። ዘመንን እንዲህ እንሻገራለን፤ ትውልድን እንዲህ እንዋጃለን እንጂ፤ በእውነት- ሥም የተበዳይነት እሮሮ ማስተናገድ “በህግ አምላክ” ሃገር ያፈርሳል፤ “በህግ አምላክ” ሰው ያጫርሳል፤ “በህግ አምላክ” ትውልድ ያቋስላል። እያደር የሚያመረቅዝ ክፋት እንመርጋለን እንጂ አያጠራንም። የትምም አያደርሰንም፤ በበቀል አዙሪት ውስጥ ይከተናል እንጂ፤ “በህግ አምላክ” ግፍ በጨለማ ጉዞ ውስጥ ይጥለናል። ስልጡን አያደርገንም፤ ወንዝ አያሻግረንም፤ እንደተባለው ብሩህ ንጋት አያሳየንም። የማለዳ ንጋት ደግሞ እየጨመረ፣ እየፈካ እየጨመረ እያደገ የሚሄድ እንጂ ጨለማና ጭጋግ አይጋብዝም። ስለዚህ የሚሰበስበውንና የሚያንጸውን እንጂ የሚበትንና የሚያፈርሰንን አናውጅ። በትውልዱ ልብ መንገድ ላይ እሾህ አንነስንስ።ከሃዋሳ ወደ አዲስ አበባ ስንሄድ የስድስት ዓመቱ ልጄ፣ “አባባ የሲዳማና የኦሮሞ ድንበር የቱ ጋ ነው፤” አለኝ። መኪና እየነዳሁ ነው፤ ሌላ ሰው ነው ወይስ ልጄ ነው ይህን ጥያቄ የጠየቀኝ ብዬ መልሼ አየሁት ። ልጄ ጥያቄህ አልገባኝም፤ አልኩት መልሼ ። “ አባባ ያልኩህ፣ የኦሮሞና የሲዳማ ድንበር የት ጋ፣ ነው- ነው ያልኩህ አለኝ” ልብ አድርጉ ልጆች በትምህርት ቤት ድንበር በዘር እየከፈሉ ነው። ሃገርን ሳይሆን ሰፈር በዘር እየገዛንላቸው ነው፤ ህጻናቱም በትምህርት ቤት እየቀዱን ነው። እኔ ያለፍኩበትን ክፉ ሞገድ፣ ልጄ እንዲያልፍበት አልፈልግም፤ እናንተም አስቡበት እስቲ፤ የምንጥደው ክፉ ቂጣ፣ በእኩልነት ስም በመብላት ፋንታ እንዳያባላን እንጠንቀቅ። አንዱን ከሌላው በቋንቋና ዘሩ ድንበር እየሾምንለት ሃገራዊ ነገራችን እንዳይደበዝዝ ያስፈራል።አሁን አሁን በተቆርቋሪነት ስም ግዛት አይደለም ቤተሰብ ለማፍረስ ነው፤ ጥረት የሚያደርጉት። አንዳንዱ ፊደል የዘለቀው ነው፤ የሚባል ሰው ሁሉ እየተነሳ “እኛን አላራምድ ያለን፣ ይኼ ተቀላቅሎ የሚወለደው ነው” ሲል ይደመጣል። የተቀላቀልነው በማመልከቻ አለመሆኑን እንዴት እንንገራቸው። የቀላቀለንና ወደ ህይወት ያመጣን ፍቅርና የጋራ እምነታችን የሰራው ጥምረት እንጂ፣ ማመልከቻ ጽፈን አልተጣመርንም ። ….. መስፈርት አቅርበን “እኔ ከዚኛው ማንትሴ ብሔር ስሆን አንቺም ከተመሳሳይ መሆንሽን አጣርቼ ነው ያፈቀርኩሽ” ብሎ ነገር በትዳር ጥመራ አይሰራም። ምድር የሁላችንም ናት፤ በደረሱበት የምድር ጫፍ አእላፍ ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህቶቻችን በቋንቋና ባህል ከማይገጥሟቸው የሰሜን አውሮፓና፣ እስያ ሰዎች ጋር በጋብቻ ተጣምረው እየኖሩ ነው፤ ያውም በፍቅር። ሰው አልተሳካለትም እንጂ እኔንና ሚስቴን ለመለየት ከሞከሩ ቆይተዋል። ምንም ስም ይሠጠው ምን ጠባብነት በእንዶድ የማይለቅ ችኮ ምርጊት ነው፤ አንጀት ውስጥ ከገባ በኋላ ለሁሉም ጥያቄ፤ ከዚያ ቁመና እየተነሳ መልስ ለመስጠት ይሞክራል እንጂ፤ ከሳጥኑ አያስወጣም፤ እነዚህ የሳጥን እስረኞች ራሳቸው ታስረው ሌላውን በዚያው የክፋት ሳጥን ውስጥ ሰው ለማጨቅ አይፈሩምም፤ አያፍሩምም።
አቤሜሌክ ወደስልጣን የመጣበት መንገድ በወንድሞቹ ግፊት ነው፤ ቢሆንም በዚህ ግፊት ውስጥ ያሳየው ወንድምነት የቆየው ለጥቂት ጊዜ ነው። ሃይላቸው የተቀመጠበትን “ፋይል” አውጥተው ሰጡት፤ የተቀበላቸው እነዚህን ሰባ ሰዎች በማረድ ሃይላቸውን ከሀገሩ ሰዎችና ከወንድሞቹ ነጠቀና ወደ እነርሱ ዞረ። ለምንድነው ሃይላችሁን አሳልፋችሁ ለክፉ የምትሰጡት? ለማን ነው ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁን አቅማችሁን አሳልፋችሁ የሰጣችሁት ? ሳታስተውሉ ያነገሳችሁት እርሱ፣ የማትፈልጉትን ብቻ ሳይሆን የምትፈልጉትንና እናንተንም በማጥፋት ነው፤ የሚያበቃው። በመግደል የጀመረ በማብላት፣ በማዋረድ የጀመረ በማክበር አይጨርስም። በህግ አምላክ!… በሃገር ውስጥ በብዙ ጥረት በተገኘው ሃብት፣ በውጭ ደግሞ (ዳያስፖራዎቹ ወገኖቼ) በማይመቸው የባዕድ ሐገር፣ የአየር ጸባይ ውስጥ ሐሩርና ቁር እየፈጃችሁ የሰበሰባችሁትን ሃብት፤ ይቺን ሐገር ለማፍረስ ለሚውል የክፋት ሥራ እንዲሆን አታዋጡ። ሃገር በመስራት ሥም ሃገር አታፍርሱ፤ በህዝብ ተጨቋኝነት ሥም ጨካኞች እንዲነግሱብን እድል አትፍጠሩ። በህግ አምላክ እሾህ አታንግሱብን።እውነት ከፍቅር ጋር፤ እውነት ከምህረት ጋር ሐገር ይገነባል፤ ሐገር ይለውጣል። ለፍቅር ለመግባባትና ለጋራ ቤት እንጂ ለመለያየትና ለአጥር መስሪያ ላባችሁን ያፈሰሳችሁበትን ጥሪት አታዋጡ፤ አትስጡ። በመጨረሻም አንድ ነገር እላለሁ፤ እንደ ወጣት፣ እንደ መንፈሳዊና ሃገሩን በብሩህ ልብ እንደሚያይ ዜጋ፣ በመጪው ምርጫ ይህንን ጣቴን ለኢትዮጵያ ጽድቅና ፍትህ ለማምጣት እጠቀምበታለሁ። በሃገሬ በኢትዮጵያ ምድር ከቶውንም እሾህ አይነግስም፤ የምላችሁ ከልቤ ነው።
መልካም ሳምንት ለአንባቢያኑና ለማያነቡት ሁሉ!!
አዲስ ዘመን ቅዳሜ ታህሳስ 18/2012
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ