አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ኮርፖሬሽን የቀላል ባቡር ጥገናና እድሳት ማዕከል ለመገንባት ከቻይና መንግስት ጋር መስማማቱን ገለፀ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን አሰፋ በተለይ ለ”ዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ” እንደገለፁት በከተማዋ ቀደም ሲል ሁለት የጥገና ማዕከላት ቢኖሩም የጥገና አገልግሎት ቀላል ለሆኑ ብልሽቶች ብቻ በመሆኑ ባቡሮች ሲበላሹ ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ወደ ቻይና በመላክ ሲያስጠግን ቆይቷል።ይህ ደግሞ በትራንስፖርት አገልግሎቱ ላይ ከሚፈጥረው ጫና ጋር ተዳምሮ ከፍተኛ ችግር ሆኖ ቆይቷል።
የተበላሹት የባቡር እቃዎች ወደ ቻይና ተልከውና ተጠግነው እስኪመጡ በትንሹ ከሁለት እስከ ሶስት ወራት ድረስ ይቆያል የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጁ ይህ እዚህ የሚቋቋመው የባቡር ጥገና ማእከል (ወርክሾፕ) ይህንንና መሰል ችግሮችን እንደሚያቃልልም ተናግረዋል።
የኮርፖሬሽኑ የጥገና ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ታመነ ሽመልስ እንደተናገሩት አሁን ባለው አቅም የተለያዩና ወሳኝ የሆኑ የባቡሩን የውስጥ አካላት (wheels እና bogies የመሳሰሉትን) እዚህ አገር ውስጥ መጠገንና ወደ ስራ መመለስ አይቻልም። ከዚህ በኋላ ግን በቻይና መንግስት ድጋፍና ትብብር እዚህ አዲስ አበባ በሚገነባው የጥገና ማዕከል አማካይነት ይህ ችግር ይቀረፋል ተብሎ ይጠበቃል። በመሆኑም ቶሎ ወደ ስራ ለመግባት እንዲቻል በአሁኑ ሰአት የግንባታ ቦታ መረጣና ቅድመ ዲዛይን ስራዎች በመካሄድ ላይ ይገኛሉ።
በአሁኑ ሰአት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት አመራር ስራውን ሙሉ ለሙሉ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ተረክቦ እያስተዳደረው እንደሚገኝም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት እስካሁን ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንም ሆነ ሌላ ገለልተኛ አካል የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ያላገኘ ሲሆን፤ ለዚህም ምክንያቶቹና ችግሮች ተለይተው እንዲታወቁ ከኮንትራክተሩ ጋር ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን ከተገኘው መረጃ ለማወቅ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ግርማ መንግስቴ