አዲስ አበባ፡- ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ያማከለ አሰራር እንዲከተሉ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን እና የሚመለከታቸው አካላት ጥሪ አቀረቡ፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን እና የሚመለከታቸው አካላት ባደረጉት ውይይት እንደተገለፀው አካል ጉዳተኞች በተለይም ከትምህርት፣ ከጤና እና ከቴክኖሎጂ አንጻር ተጠቃሚነታቸውን መቃኘትና በክፍተቶቹ ላይ የመፍትሔ ሀሳቦችን ማስቀመጥ ይገባል።መድረኩ ትኩረት ካደረገባቸው ውጭ ያሉ ሌሎች ተቋማትም አካል ጉዳተኞችን ያካተተ አሰራር እንዲከተሉ የሚያነቃቃ መሆኑም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ እንዳስታወቁት አሁን ያለው የለውጥ አመራር ለአካል ጉዳተኞች ትኩረት የሰጠ ነው:: ይሁን እንጂ ተቋማት በተለይም በትምህርት ፣ በጤና እና በቴክኖሎጂ ዘርፍ የአካል ጉዳተኛውን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ ይገባል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።ተቋማቱ ይህን ምቹ ሁኔታ ሊጠቀሙ እንደሚገባም አስታውቀዋል ፤ አሰራራቸውን በመፈተሽ የአካል ጉዳተኞችን ጥያቄ ለመመለስ ቁርጥ አቋም መያዝ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ዲን ዶክተር ደበበ ኤሮ አካል ጉዳተኞች ከትምህርት፣ ከጤና እና ከቴክኖሎጂ አንጻር ያላቸውን ተደራሽነት አስመልክተው በውይይቱ ወቅት ባቀረቡት ጽሁፍ እንዳመለከቱት ከችግሩ መስፋት አንጻር ዋና ዋና የሚባሉ ክፍተቶችን ጠቁመዋል።ሀገሪቱ ታዳጊ እንደመሆኗ መጠን የማህበረሰቡ አመለካከት እምብዛም ያለመለወጡ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ገልጸዋል።
በጤናም ሆነ በትምህርት ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ተደራሽ ያላደረጉ አገልግሎቶች እምብዛም ላለመሰጠታቸው ምክንያቱ የግንዛቤ እጥረት ነው ብለዋል።አካል ጉዳተኞች በቴክኖሎጂ አለመጠቀማቸውና አለመደገፋቸውም ሀገሪቱ ተመጣጣኝ እድገት እንዳይኖራት ማድረጉን አስታውቀዋል።
አካል ጉዳተኞች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውም ሆነ ተጠቃሚነታቸው ከሌላው ማህበረሰብ ጋር ሲነጻጸር አናሳ ነው።
ሀገሪቱ የምትቀርጻቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የአካል ጉዳተኞችን ጥያቄና ፍላጎት ከግምት ያስገቡ አይደሉም።አንዳንዶቹ ትኩረት የሰጡ ቢመስሉም በአተገባበር መሬት ላይ ሲወርዱ አይታዩም ብለዋል።
የሚመለከተው አካልም ይሁን ማህበረሰቡ አካል ጉዳተኞችን ማብቃት ይችላሉ ብሎ ማሰብ እንደሚገባው ዶክተር ደበበ ገልጸዋል።መንግስት በትምህርት እና በተለያዩ ሰብዓዊ መብቶች ጉዳይ እነዚህን የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ የሚያደርጉ አለማቀፍ ድንጋጌዎችን ተቀብሎ በፖሊሲዎቹ መካተቱ የሚያስመሰግን ተግባር መሆኑን ጠቁመዋል።ነገር ግን ተፈጻሚነታቸውን የመከታተል፣ የመቆጣጠርና የማረጋገጥ ክፍተት መኖሩን አመልክተዋል።
በሌላ በኩል ከመድረኩ ተሳታፊዎች በተሰጠው አስተያየት በኢትዮጵያ ውስጥ የአካል ጉዳተኞችን ትክክለኛ አሀዝ የሚገልጽ መረጃ ባለመኖሩ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ አሀዞች መጠቀሳቸውን ተናግረዋል።
ይህም በቁጥራቸው ልክ አቅዶ ለመስራት እንቅፋት እንደሚሆን ገልጸዋል።ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌደራል ድረስ ባሉ ምክር ቤቶች አካል ጉዳተኞች ያለመወከላቸው ጉዳያቸው እልባት እንዳያገኝ ያደረገ ምክንያት መሆኑን ጠቅሰዋል።መንግስት በህገ-መንግስቱ ላይ ያሉ ዓለምአቀፍ ድንጋጌዎችን በማክበር የአካል ጉዳተኞች መብት እንዲጠበቅ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
አካል ጉዳተኞችን ከግንዛቤ ያላስገቡ ግንባታዎች መፈጸማቸው ለተጨማሪ ችግሮች እየዳረጋቸው እንዳለ የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ እንደ ዊልቸርና ምርኩዝ የመሳሰሉ መገልገያ ቁሶች ዋጋ መጨመርም ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን እየተፈታተነ እንዳለ ገልጸዋል።ተቋማትም ሆኑ ህብረተሰቡ አካል ጉዳተኞችን ከግምት ያስገቡ ተግባራትን እንዲያከናውኑ መክረዋል።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሄራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ከአይ ሲ አር ሲ እና ከቪ ኤስ ኦ ጋር በመተባበር ያደረገው ይህ ውይይት በርካታ ጉዳዮች እንደተዳሰሱበትና ወደፊትም እንደሚቀጥል ተመልክቷል።በውይይቱ ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት ከክልልና ከፌደራል የመንግስት መስሪያ ቤቶች የተወከሉ ባለድርሻ አካላት እና ከአካል ጉዳተኞች ማህበራት የተወጣጡ ባለጉዳዮች ተሳትፈዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ኢያሱ መሰለ