- 500 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ ተገኝቷል
አዲስ አበባ፡-በ11 ከተሞች እየተተገበረ ያለውን የከተሞች የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ወደ72 ከተሞች ለማስፋፋት አስፈላጊ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑን የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት የፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ገለጸ፡፡
የከተሞች ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ዋና አስተባባሪ አቶ ደበበ ባሩድ በተለይ አዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው የከተሞች
የምግብ ዋስትና ፕሮግራም አፈጻጸሙ አበረታች በመሆኑ በሌሎች የአፍሪካ አገሮችም ተሞክሮ እየተወሰደበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡
ፕሮግራሙ ለዜጎች እያበረከተ ያለው ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ከተገመገመ በኋላ በቀጣዩ ዓመት ወደ 72 ከተሞች እንዲስፋፋ ዝግጅቶች እየተደረ መሆኑን የጠቁሙት አቶ ደበበ ለዚህ ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የሚሆን 500 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ መገኘቱንም ጠቁመዋል፡፡
ከኢትዮጵያ መንግሥት የሚያወጣው ገንዘብ ደግሞ በከተማ ልማት ሚኒስቴርና በገንዘብ ትብብር ሚኒስቴር መስሪያቤቶች በኩል ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እስኪወሰን ድረስ እየተጠበቀ ይገኛል ብለዋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከምግብ ዋስትና በተጨማሪ የወጣቶች ሥራ ፈጠራም የታከለበት በመሆኑ በፕሮግራሙ ስራ ፈላጊ ወጣቶችን ጨምሮ አንድ ሚሊዮን ዜጎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑበት ተናግረዋል ፡፡
በዓለም ባንክ በኩል ገንዘቡ ከተፈቀደ ጀምሮ አስፈላጊ ዝግጅቶችና ዝርዝር ጥናቶች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ደበበ ከሚያዝያ ጀምሮ የተጠቃሚዎች
ምልመልና መሰል ስራዎች ተሰርተው ሲጠናቀቁ በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ ፕሮግራሙ ተግባራዊ የሚደረግ ይሆናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በ2009 በጀት ዓመት የተጀመረውና በ11 ከተሞች እየተተገበረ ያለው የምግብ ዋስትና ፕሮግራም 604 ሺህ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን ለፕሮግራሙ ማስፈጸሚያ 450 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተመደበ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 300 ሚሊዮን ዶላር ከዓለም ባንክ በተገኘ ብድር ቀሪው 150 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ በመንግሥት የተሸፈነ መሆኑን ይታወቃል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ጌትነት ምህረቴ