አዲስ አበባ፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአልፉርሳን ወርቅ አምራች ሕብረት ማህበር አባላት በባህላዊ መንገድ በዓመት እስከ አራት ኪሎ ግራም ወርቅ በማምረት ላይ መሆናቸውን ገለፁ።
የማህበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጀላል መሐመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳሉት፤ ማህበሩ በአካባቢው ያሉ 21 ሥራ አጥ ወጣቶችን በማደራጀት እና 21 ሺህ ብር ካፒታል ይዞ በ2005 ዓ.ም ወደሥራ የገባ ሲሆን ከአምስት ሄክታር በማይበልጥ መሬት ላይ በባህላዊ መሳሪያዎችና በባህላዊ አሠራር በመጠቀም በዓመት እስከ አራት ኪሎ ግራም የወርቅ ዱቄት በማም ረት ላይ ይገኛል ።
ወርቅ የሚያመርቱት ወምበራ እና ያሶ በሚባሉ ወረዳዎች እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ጀላል፤ ከአካባቢው የሰላም ሁኔታ ጋር ተያይዞ ከፍና ዝቅ የማለት ሁኔታዎች ቢኖሩም ማህበሩ ከ60 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠሩንም ተናግረዋል። አጠቃላይ ካፒታሉም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ መድረሱን ተናግረዋል።
ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት፤ ይህ ሥራ ለችግሮችና ለሚገጥሙ ፈተናዎች የማይንበረከክ ቆራጥ ወጣት ካለ በባህላዊ መሣሪያዎችም ቢሆን ሰርቶ ከመለወጥ የሚያግደው ፈተና እንደማይኖር ማሳያ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት የአካባቢው የሰላም ሁኔታ እንደልብ የሚያሠራ ባለመሆኑ የምርት መቀነስ አጋጥሞ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጀላል፤ ያም ሆኖ በውጤታማነት ደረጃ ከሌሎች ማህበራት የተሻሉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። አሁን ላይ የተሻለ ለማምረት ጠንክረው በመስራት ላይ ሲሆኑ ፈተናዎች የማይገጥሙት አንዳችም የለውጥ መንገድ አለመኖሩንም አስረድተዋል።
የወርቅ ማውጫው ጉድጓድ ጥልቀት እየራቀ በመሄዱ እና ያሉዋቸው መሳሪዎች ከአንድ ሜትር በላይ ወደመሬት የማይገቡ ኋላ ቀር በመሆናቸው በሚፈልጉት ደረጃ ምርታቸውን ማሳደግ ባያስችላቸውም በከፍተኛ ልፋት ወርቅ ከመጨበጥ እንደማይመለሱ አቶ ጀላል ተናግረዋል።
አቶ ጀላል እንደተናገሩት፤ የሙያና የማቴሪያል ድጋፍ ለማህበሩ እንደሚደረግለት በተለያዩ መድረኮች ቃል የገቡ አካላት ቢኖሩም እስከአሁን ድረስ አንዳችም ድጋፍ እንዳላደረጉ ተናግረዋል። እነዚህ ድጋፎች አለመደረጋቸው ማህበሩን ከሥራ ሊያስተጓጉሉትም ሆነ ተስፋ ሊያስቆርጡት ባይችልም ዘመናዊ መሳሪያዎቹ ከዚህ በብዙ እጥፍ ማምረት የሚቻልባቸውን እድሎች እንደሚፈጥሩ አይካድም ብለዋል።
አቶ በሽር አብዱራሂም የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ በበኩላቸው፤ በመድረክ ደረጃ ብዙ ነገሮች ሊነሱ እንደሚችሉ ገምተው ሂደቱን ጠብቀው የቀረቡ የድጋፍ ጥያቄዎች ግን እስካሁን ድረስ አለመኖራቸውንና በእነሱ ቢሮ በኩልም የገቡት የድጋፍ ቃል እንደሌለ ገልጸው፤ አሁንም አልረፈደም ብለዋል።
በዘርፉ የተደራጁ ማህበራት እስከአሁን ድረስ ወርቅ የሚያመርቱት በባህላዊ መንገድ ነው የሚሉት አቶ በሽር በቀጣይ ይሄን በዘመናዊ አሠራር በመተካት በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችን ሥራ ለማስያዝ አልመው እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸው ለዚህም ተዘዋዋሪ ብድር መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አካሻ እስማዒል እንደገለጹት፤ በማህበራት የሚደራጁ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶችን መደገፍ ተገቢ እንደሆነ አንስተው፤ ጥያቄያቸውን በተገቢው መንገድ ለሚያቀርቡ ማህበራት የሚመለከተው የመንግስት አካል አቅም በፈቀደ መጠን ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ አስረድተዋል።
አልፉርሳንን ጨምሮ ሌሎች ወርቅ አምራች ማህበራት በተሻለ ደረጃ በማምረት ራሳቸውን፣ ክልላቸውን እና አገራቸውን መጥቀም እንዲችሉ ክፍተታቸው ተለይቶ አስፈላጊው ድጋፍ ይደረግላቸዋልም ነው ያሉት።
ወጣቶች በእንደዚህ አይነት የማዕድን ስራዎች ላይ መሰማራት ቢችሉ ራሳቸውንም ሆነ አገራቸውን ለመለወጥ ሰፊ እድል አላቸው የሚሉት አቶ አካሻ፤ ነገር ግን ስራው ከባድ ውጣ ውረድ ያለው፣ አድካሚ እና ጉልበት የሚጠይቅ በመሆኑ እነዚህን ፈተናዎች ተቋቁመው በማለፍ መለወጥ መቻልን ወጣቶች ሊለምዱ ይገባል ሲሉም መክረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ሙሐመድ ሁሴን