አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርምና የለውጥ መሳሪያዎች አተገባበር በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳልሆነ በጥናት አስደግፎ ይፋ አደረገ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ደሳለኝ ‹‹የፐብሊክ ሰርቪስ ተቋማት የአቅም ግንባታ የትግበራ ሂደትና የወደፊት አቅጣጫዎች›› በሚል ትናንት በግቢው በተካሄደ አውደ ጥናት እንደገለጹት፤ የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርምና መተግበሪያ የሆኑት የለውጥ መሳሪያዎች የአሰራር፣የአደረጃጀትና የሰው ሃይል አቅምን በማሳደግ እምርታዊ ለውጥ ያመጣሉ የሚል እምነት የተጣለባቸው ቢሆንም በተገቢው ተግባራዊ ሊደረጉ ባለመቻላቸው በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን እንዳልቻሉ በተካሄደ ዳሰሳዊ ጥናት መረጋገጡን ተናግረዋል።
ሪፎርሙና የለውጥ መሳሪያዎቹ የተቋማትን አቅም በማሳደግና የሰራተኛውን አቅም በመገንባት በኩል ዘርፈ ብዙ ለውጥ ማስመዝገብ እንደሚያስችሉ የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች በግልጽ ያረጋገጡት ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታም ለውጥ መፍጠር የሚስችሉ ነበሩ ብለዋል። ነገር ግን መሬት ላይ በሚወርዱበት ወቅት አላማና ግባቸውን በሚፈለገው ደረጃ ማሳካት እንዳልቻሉ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ሰርቪስ አቅም ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ገብረ ትንሳኤ ተስፋዬ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፉ እንዳነሱት፤ የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርምና የለውጥ መሳሪያዎች አተገባበር በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ አለመሆኑን አስረድተዋል።
ዳይሬክተሩ እንዳሉት፤ለዚህ ችግር በየደረጃው የሚገኙ አካላት የየራሳቸው ድርሻ እንደነበራቸው ገልጸው፤ የአመራሩ ድርሻ ቅድሚያውን እንደሚይዝም አንስተዋል።
የብቃት ችግር፣ተግባሩን በተገቢው ተረድቶ አለመምራት፣ሰዎች በተደጋጋሚ በአንድ ጉዳይ ላይ እንዲሰለጥኑ በማድረግ፣ የሰለጠኑ ሰዎች ተግባሩን በትክክል ለሚመለከተው ማድረሳቸውን ባለመከታተል፣ የተፈጠሩ አደረጃጀቶችን ባለማጠናከር እና መሰል በርካታ ችግሮች በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች እንደሚስተዋሉባቸው ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው በኩልም የሰልጣኙን ብቃት ከማሻሻል፣ የስልጠናውን ተገቢነት ከመለየት እና ከስልጠና አቀራረጽና አሰጣጥ ጋር የተያያዙ ችግሮች በጥናቱ መለየታቸውን ዳይሬክተሩ ዘርዝረዋል።
በየደረጃው ለሪፎርምና ለለውጥ መሳሪያዎች ስልጠና ተሳታፊ የሚሆነው አካልም ይሁነኝ ብሎ ለለውጥ ቁርጠኝነት ከመሰነቅ ይልቅ የሚሰጡ ስልጠናዎችን እንደመዝናኛ መቁጠርና ተመልሶም ተግባሩን መፈጸምም ሆነ ማስፈጸም የሚችልበት ቁመና ላይ አለመድረስ ጥናቱ ካመላከታቸው ችግሮች መካከል እንደሚጠቀሱ ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ጥናቱን መሰረት በማድረግ የሲቪል ሰርቪሱ ሪፎርም እና የለውጥ መሳሪያዎቹ ውጤታማ መሆን እንዲችሉ በጥናቱ ከተመላከቱ የመፍትሄ አቅጣጫዎች መካከልም በቀጣይ በሚሰጡ ስልጠናዎች ዙሪያ ጥብቅ ክትትል ማድረግ፣ ቅድመ ስልጠና፣ በስልጠናው አጋማሽ እና ድህረ ስልጠና ውጤት አዘል ፈተናዎች መስጠት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዩኒቨርስቲው ጥናቱን ያካሄደው በስድስት የፌዴራል መስሪያ ቤቶችና በአዲስ አበባ ከተማ ሶስት መስሪያ ቤቶች ሲሆን በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ዙሪያ በቀጣይ ዘላቂ ማሻሻያዎች ለማድረግ ያለመ እንደሆነም ተመላክቷል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ሙሐመድ ሁሴን